ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ምዓም አናብስት ላይ ጣፋጭ ድል ተቀዳጁ

አምስት ግቦች የተቆጠሩበት የባህር ዳር ከተማ እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የተከናወነው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ለመቐለ 70 እንደርታ ክለብ፣ ለመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ማኅበር እና ለቀድሞ ተጨዋቻቸው አስናቀ ሞገስ ስጦታ አበርክተዋል።

ለሜዳዎ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር የተስተዋለበት ነበር። ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ሲንቀሳቀሱ በተቃራኒው ተጋባዦቹ መቐለ 70 እንደርታዎች በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተሽለው ተጫውተዋል።

የጣና ሞገዶቹ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ አዳማ ላይ ነጥብ ከተጋሩበት የጅማ ጨዋታ እንዲሁም የመቐለ 70 እንድርታ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በሜዳቸው ሃዲያ ሆሳናን ካሸነፉበት ጨዋታ አንድ አንድ ለውጦችን አድርገው ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም ፋሲል ተካልኝ የአማካይ መስመር ተጨዋቹን ዳንኤል ኃይሉን በሳምሶን ጥላሁን ሲለውጡ ገብረመድን ኃይሌ ደግሞ ኤፍሬም አሻሞን በኦኪኪ አፎላቢ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በፈጣን የኳሰ ቅብብሎች የተጀመረው የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ያስተናገደው በ4ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃ የባለሜዳዎቹ የመስመር ተጨዋቹ ዜናው ፈረደ በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው አጋድለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መግባት ተስኖቸው የኳስ ቅብብሎሻቸውን ገድበው ተንቀሳቅሰዋል። ተጋጣሚያቸው መቐለ 70 እንደርታዎች ደግሞ በይበልጥ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ተጫውተዋል።

ምዓብ አናብስቶች በጨዋታው በ10ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ በቅብብል ስህተት የተገኘውን ኳስ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ ለኦኪኪ አፎላቢ አቀብሎት ኦኪኪ ወደ ግብ መቶት የነበረ ሲሆን ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። አጀማመራቸውን ያሳመሩት የጣናው ሞገዶቹ በ15ኛው እና በ19ኛው ደቂቃ ዜናው በሞከራቸው ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች መሪ ለመሆን ተቃርበው መክኖባቸዋል። መልሶ ማጥቃትን አንደ ዋነኛ ግብ ይዘው በዚህ አጋማሽ የተጫወቱት የገብረመድን ተጨዋቾች በ20ኛው ደቂቃ በፍጥነት የባህር ዳር የግብ ክልል በአማኑኤል ገ/ሚካኤል አማካኝነት ደርሰው ሙከራ አድርገዋል።

የጨዋታ ብልጫውን በግብ ለማጀብ ጥረት ያደረጉት ባህር ዳሮች በ23ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን አዋህደው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ደቂቃ ዜናው ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት አዳማ ሲሶኮ በግምባሩ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመጠኑ የተነቃቁ የሚመስሉት ተጋባዦቹ በ30ኛው ደቂቃ አቻ የሚሆኑበትን እድል ከመዓዘን ምት ፈጥረው ነበር። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ዳግም የአቻነት ግልፅ እድል ያገኙት መቐለዎች አጋጣሚውን በፈጣኑ አጥቂያቸው አማኑኤል ገ/ሚካኤል አማካኝነት ተጠቅመው አቻ ሆነዋል።

አቻ ከሆኑ ከአንድ ደቂቃ በኋላም ቡድኑ ግልፅ የግብ ማግባት እድል በአማኑኤል አማካኝነት ፈጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው መቐለዎች በድጋሚ ከርቀት የተላከን ረጅም ኳስ ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት 1ለ1 ተጠናቋል።

የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ ባለሜዳዎቹ በግዙፉ አጥቂያቸው ማማዱ ሲዲቤ የግንባር ኳስ መሪ ሆነዋል። በ48ኛው ደቂቃ የተገኘውን የመዓዘን ምት ወሰኑ ዓሊ አሻምቶት ረጅሙ አጥቂ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

በዜናው ተቀይሮ የገባው ግርማ ዲሳሳ በ52ኛው ደቂቃ ከአምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቶት የነበ ሲሆን ፍሊፕ ኦቮኖ አድኖበታል። በመጀመሪያው አጋማሽ እና በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ተዳክመው የነበሩት መቐለዎች ሁለተኛ ጎል ካስተናገዱ በኋላ ተሽለው ተንቀሳቅሰዋል። በዚህ አጋማሽ ቡድኑ ምንም እንኳን በአንፃራዊነት ተሽሎ ለመንቀሳቀስ ቢጥርም ከባህር ዳር በኩል ሲደረጉ የነበሩ ጥቃቶችን ለመመከት ተቸግሮ ታይቷል። በ60ኛው ደቂቃ በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ፍፁም ዓለሙ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያገኘውን እድል ወደ ጎል በመቀየር የቡድኑን መሪነት አስፍቷል።

በጥሩ መንገድ ሲነቃቁ የነበሩት ተጋባዦቹ ከዚህች ግብ በኋላ የተከላካይ መስመራቸውን ወደ ፊት በመግፋት ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጥረዋል። ይህንን የመቐለ አጨዋወት እንደ መልካም አጋጣሚ የተመለከቱት ባህር ዳሮች የትኩረት ችግር የነበረበትን የመቐለ የተከላካይ ጀርባን በመጠቀም ተጨማሪ ግቦች ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህም ሲዲቤ፣ ወሰኑ፣ ግርማ እና ፍፁም ጥሩ ጥሩ እድሎችን ፈጥረው መከኖባቸዋል።

በ76ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ያመሩት ምዓብ አናብስት በመስመር ተከላካያቸው ሥዩም ተስፋዬ የመሬት ለመሬት ኳስ መሪነቱን አጥብበዋል። ከዚህች ግብ በኋላ አጨዋወታቸውን የገደቡት ባህር ዳሮች አጋጣሚዎችን ከቆሙ ኳሶች ብቻ በመፍጠር ጨዋታቸውን ቀጥለዋል። በተቃራኒው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የጨዋታውን የኃይል ሚዛን በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉት መቐለዎች ወደ ግብ ለመድረስ ቢጥሩም ፍሬ ማፍራት አልቻሉም። ቡድኑ በ90ኛው ደቂቃ የመጨረሻ ሙከራ በአስናቀ ሞገስ አማካኝነት አድርጎ መክኖበታል። ጨዋታውም በባለሜዳዎቹ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ