ሃገራችንን ወክሎ በ2016 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ ቻምፒዮኑ መከላከያ በመጪው ቅዳሜ ከግብፁ ምስር አል-ማቃሳ ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ጃንሜዳ አካባቢ በሚገኘው የክለቡ የልምምድ ሜዳ ተገኝታ ፣ የክለቡን ዝግጅት ተመልክታለች፡፡ የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾችን አስተያየት ተቀብላለች፡፡
‹‹ በየጨዋታው መስራት የሚገባንን እያደረግን ወደ ፊት እንጓዛለን ›› ሚካኤል ደስታ
ጦሩ በ3 አመታት ውስጥ ለ2ኛ ጊዜ በሚካፈልበት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የተሸለ ጉዞ ለማድረግ አልሟል፡፡ የክለቡ አምበል ሚካኤል ደስታም ካለፈው ስህተት እንደተማሩ ይናገራል፡፡
‹‹ በዚህኛው የመከላከያ ስብስብ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ስንሳተፍ ሁለተኛ ጊዜያችን ነው፡፡ በ2006 በሊዮፓርድስ ተሸንፈን ከቅድመ ማጣርያው ተሰናብተናል፡፡ ከዛ ጨዋታ ስህተታችን ተምረን የተሻለ ጉዞ ለማድረግ ተዘጋጅተናል›› ብሏል፡፡
ሚካኤል አሰልጣኛቸው የተጋጣሚያቸውን አጨዋወት የተመረኮዘ ልምምድ ሲያሰሩዋቸው እንደቆዩም ተናግሯል ‹‹ አሰልጣኛችን የተጋጣሚያችንን እንቅስቃሴ የያዘ ቪድዮ ሲያሳየንና ምን ማድረግ እንደሚገባን አስረድቶናል፡፡ የሜዳችንን አድቫንቴጅ እንዴት መጠቀም እንዳለብንም ተነጋግረናል፡፡››
ለረጅም አመታት ከአፍሪካ ውድድር ርቆ የቆየው የቀድሞው ሃያል ክለብ መከላከያ (በቀድሞ አጠራር መቻል ፣ ምድር ጦር እና ጦር ሰራዊት) በ1997 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ በኋላ ወደ ቀድሞ ዝናው ለመመለስ እየተጋ ይገኛል፡፡ በ10 አመታት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ለማድረግም ተዘጋጅቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ሙከራዎች በጊዜ የተሰናበተው ክለብ ዘንድሮ የተሻለ መጓዝ እንደሚችልም ሚካኤል ያምናል፡፡
‹‹ ውድድሩ ጥሎ ማለፍ ስለሆነ የሚከሰተውን ቀድሞ መናገር አይቻልም፡፡ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ስናሸንፍ ከፊታችን የሚገኙ ተጋጣሚዎችን እያሸነፍን ነበር፡፡ አሁንም ከፊታችን ያለውን ተጋጣሚ አሸንፈን ማለፍ የሚጠበቅብን በመሆኑ ምስር አል ማቅሳን አሸንፈን ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ አላማችን ነው፡፡ በየጨዋታው መስራት የሚገባንን እያደረግን ወደ ፊት እንጓዛለን፡፡ ››
‹‹ አሁን የቅዳሜውን ጨዋታ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ›› በኃይሉ ግርማ
የጦሩ የመሃል ሜዳ መሪ በኃይሉ ግርማ ክለቡ በዘንድሮው ውድድር የተሸለ ጉዞ ለማድረግ ቀደም ብሎ ዝግጅት ማድረግ እንደጀመረ ተናግሯል፡፡ ‹‹ ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ያደረገግነው ዝግጅት ጥሩ ነበር፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ ለዚህ ውድድር ትኩረት ሰጥተን እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡ አሁን የቅዳሜውን ጨዋታ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡››
በኃይሉ ግርማ በ2006 ክረምት ሙገር ሲሚንቶን ለቆ መከላከያን ከተቀላቀለ በኋላ የክለቡ ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡ በክለብ ደረጃ የመጀመርያ ኢንተርናሽናል ውድድሩን ለማድረግ እየተዘጋጀ የሚገኘው በኃይሉ በብሄራዊ ቡድን መጫወቱ ጫና እንዳይሰማው እንደሚያደርገው ተናግሯል፡፡
‹‹ በክለብ ደረጃ ይህ የመጀመርያ ኢንተርናሽናል ውድድሬ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ሴካፋ ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡ ከክለብ የበለጠ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ጨዋታ ቀለል አድርገነው እንዲሁም በጥሩ ሁኔታ ተጫውተን ውጤት እናስመዘግባለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ›› ብሏል፡፡