ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ወላይታ ድቻ

በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚደረገውን የጅማ አባጅፋር እና የወላይታ ድቻን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በተከታታይ ሁለት የሜዳቸው ላይ ጨዋታዎች ድል የተቀዳጁት ጅማ አባ ጅፋሮች የሜዳ ላይ ጥንካሬያቸውን ለማስቀጠል እና ባሳለፍነው ሳምንት ከደረሰባቸው የሰበታ ከተማ ሽንፈት ለማገገም 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ አቻ

የተጋጣሚን አጨዋወት በማጨናገፍ እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቶችን በመተግበር ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ጅማዎች በነገውም ጨዋታ ተቆጥበው እንደሚጫወቱ ይገመታል። በተለይ ወደ ኋላ አፈግፍጎ የሚጫወተው ቡድኑ ረጃጅም ኳሶችን እንደ ዋነኛ የግብ ማስቆጠሪያ ምንጭ በመጠቀም ይንቀሳቀሳል ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ የኤሊያስ አህመድን የፈጠራ ብቃት እጅግ ሲፈልግ ይታያል። በነገው ጨዋታም ይህ ታታሪ ተጨጫዋች የቡድኑን ሚዛን ከመጠበቅ ባሻገር ወደ ፊት የሚልካቸው ቁልፍ ኳሶች ቡድኑን እንደሚጠቅሙ ይገመታል።

በሊጉ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ጅማ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ካሉ 3 ክለቦች ያነሰ ግቦችን ተጋጣሚዎቹ ላይ አስቆጥሯል። ይህ የሚያሳየው ቡድኑ ምንያህል የግብ ማስቆጠር ችግር እንዳለበት ነው። በነገውም ጨዋታ ይህንን የግብ ማስቆጠር ችግሩን ካልቀረፈ ሊቸገር ይችላል።

ጅማዎች ብሩክ ገብረዓብ፣ ሄኖክ ገምቴሳ እና ሰዒድ ሀብታሙ ወደ ልምምድ ቢመለሱላቸውም የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ጋናዊው ተከላካይ አሌክስ አሙዙ አሁንም የወረቀት ጉዳዮች ባለማለቃቸው ለጨዋታው ብቁ አይደለም።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ

ከቀናት በፊት ከዋና አሰልጣኙ (ገብረክርስቶስ ቢራራ) ጋር የተለያየው ወላይታ ድቻ በጊዜያዊ አሰልጣኙ ደለለኝ ደቻሳ እየተመራ ከገባበት የውጤት ቀውስ ለመውጣት እና ኅዳር 21 ያሳካውን ብቸኛ የዓመቱ ድሉን (ሲዳማ ቡናን 2-0) ለመድገም ወደ ጅማ አቅንቷል።

በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ቡድኑ እንቅስቃሴውን ውጤታማ የማድረግ ከፍተኛ ችግር ይስተዋልበታል። በተለይ ከወገብ በላይ ያሉት የቡድኑ ተጨዋቾች ፍሬያማ የሆነ እና ቡድኑን የሚጠቅም ሥራዎችን ለመስራት ሲቸገሩ ይስተዋላል። ምናልባት ይህ ጉዳይ በነገው ጨዋታ ተስተካክሎ የሚቀርብ ከሆነ ድቻዎች ከሜዳቸው ውጪ በጎ ነገር ይዘው ሊመለሱ ይችላሉ።

በሊጉ 3 ጎሎችን (የቡድኑን 50% ጎል) ለክለቡ ያስቆጠረው ባዬ በነገው ጨዋታም የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች እንደሚሆን ይጠበቃል። ከባዬ በተጨማሪ ከመስመር እየተነሱ ጥቃቶዎችን ለመሰንዘር የሚሞክሩ የመስመር አማካይ ተጨዋቾች ጥረት የጅማን ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ለመሰባበር ወሳኝ ነው። ስለዚህም በነገው ጨዋታ ቡድኑ የመስመር ላይ አጨዋወቱን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አጠናክሮ እንደሚገባ ይታሰባል።

ቦታቸውን ለቀው የሚጫወቱት የድቻ ተጫዋቾች በተለየ በመከላከል ቅርፅ የሚሰራቸውን የቦታ አጠባበቅ ስህተቶች ቡድኑን ነገ ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋል። ይህ ጉዳይ በይበልጥ በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ለሆነው የጳውሎስ ቡድን ምቹ አጋጣሚን ሊፈጥር ስለሚችል ቡድኑ መጠንቀቅ ይኖርበታል።

መኳንንት አሸናፊ እና ነጋሽ ታደሰ ጉዳት ላይ በመሆናቸው ወደ ጅማ እንዳልተጓዙ ሲጠቆም በጉዳት ላይ የሰነበተው ያሬድ ዳዊት ካጋጠመው ጉዳት በማገገሙ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ታውቋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው ወላይታ ድቻ (አንድ ፎርፌ ጨምሮ) ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ወጥተው ጅማ አባ ጅፋር አንድ አሸንፏል።

– በአራቱ ግንኙነት ስምንት ጎሎች (የድቻ ሦስት የፎርፌ ጎሎችን ጨምሮ) ሲቆጠሩ እኩል አራት አራት አስቆጥረዋል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)

መሐመድ ሙንታሪ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ

ኤፍሬም ጌታቸው – ንጋቱ ገ/ሥላሴ

ሱራፌል ዐወል – ኤልያስ አህመድ – አምረላ ደልታታ

ያኩቡ መሐመድ

ወላይታ ድቻ (4-3-3 / 4-1-4-1)

መክብብ ደገፉ

ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – እዮብ ዓለማየሁ

በረከት ወልዴ – ተስፋዬ አለባቸው – ኢድሪስ ሰዒድ

ፀጋዬ ብርሀኑ – ባዬ ገዛኸኝ – ቸርነት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ