ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዓርብ እና ቅዳሜ ተከናውነዋል። በስምንቱ ጨዋታዎች በንፅፅር ጥሩ አቋም ያሳዩ 11 ተጫዋቾችንም እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። 

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው።

አሰላለፍ፡ 3-4-3


ግብ ጠባቂ

ዳንኤል አጃይ (ሰበታ ከተማ)

የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በነበረው ጨዋታ ምንም እንኳ ሁለት ግቦች ቢያስተናግድም በግሉ ጥሩ ቀን አሳልፏል። በጨዋታው ፍፁም ቅጣት ምት ያመከነው ይህ ጋናዊ ግብ ጠባቂ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ሦስት ያለቀላቸው ጎል የሚሆኑ ኳሶች በማዳን ውጤቱ ከዚ በላይ እንዳይሰፋ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።


ሥዩም ተስፋዬ (መቐለ 70 እንደርታ)

በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው አንጋፋው ሥዩም ተስፋዬ የቡድኑ ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ የሆነው የመስመር እና ቀጥተኛ አጨዋወት ላይ ድርሻ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። ከሰበታ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታም ጥሩ ከመንቀሳቀስ አልፎ ኦኪኪ ኦፎላቢ ላስቆጥረው ግብ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን በጨዋታውን ለበርካታ የግብ ዕድሎች መፈጠር ምክንያት ነበር። ተጫዋቹ የቀኝ መስመር ተከላካይ ቢሆንም ለመጀመርያ ጊዜ በተካተተበት የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን ከሦስቱ ተከላካዮች ጋር አካተነዋል።


ወንድሜነህ ደረጄ (ኢትዮጵያ ቡና)

እጅግ የተረጋጋው የኢትዮጵያ ቡናው የመሐል ተከላካይ ወንድሜነህ በፈጣን ሽግግሮች ለመጫወት የሚጥሩት የሲዳማ ቡና ፈጣን አጥቂዎች ኳሶቹን እንዳይጠቀሙ ወሳኝ የሆኑ ኳሶችን ከማቋረጥ በዘለለ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ለመጫወት ጥረት የሚያደርጉት የሲዳማ አጥቂዎችን ተቋቋሞ የግል ጥረቱን በመጠቀም ያልፍበት የነበረው መንገድ በጣም ስኬታማ ነበር። በሶከር ኢትዮጵየመ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥም ለሦስተኛ ጊዜ ተካቷል።


ዮናስ ግርማይ (ስሑል ሽረ)

በእግር ኳስ ህይወቱ ምርጥ ብቃት ላይ የሚገኘው የስሑል ሽረ አምበል በዓመቱ መጀመርያ በጉዳት ጨዋታዎች ቢያልፉትም ከጉዳት መልስ በጥሩ ሁኔታ ቡድኑን በማገልገል ይገኛል። ተጫዋቹ ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ የግዙፉን አጥቂ ሙጂብ ቃሲምን እንቅስቃሴ በመግታት እና የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት በመምራት ረገድ ጥሩ ቀን አሳልፏል። በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባ የመጀመርያው የሆነው ዮናስ ግርማይ ቡድኑ መረቡን ሳያስደፍር እንዲወጣም ጉልህ ድርሻ ነበረው።


አማካዮች

አብዱለጢፍ መሐመድ (ስሑል ሽረ)

በስሑል ሽረ የማጥቃት አጨዋወት እጅግ ወሳኝ ሚና ያለው ይህ ታታሪ ተጫዋች ቡድኑ ፋሲል ከነማን በረታበት ጨዋታ አንድ ግብ ከማስቆጠርም ባለፈ የጨዋታው ኮከብ የሚያስብለው እንቅስቃሴ አድርጓል። በሊጉ ፈጣን ከሚባሉ ተጫዋቾች ተርታ የሚመደው ይህ ተጫዋች የቡድኑ መልሶ ማጥቃት በመምራት ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ተጫዋቹ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባ የመጀመርያው ነው።


እድሪስ ሰዒድ (ወላይታ ድቻ)

በቴክኒኩ ረገድ የላቀ ብቃት ያለው መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ተስፈኛው አማካይ መሐል ለመሐል የፈጠራ አቅሙ ደካማ ለነበረው ወላይታ ድቻ አዲስ የማጥቃት አማራጭ እየሰጠ ይገኛል። በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተካተተው እድሪስ የግብ እድሎችን ከመፍጠር በዘለለ ከመሀል ሜዳ እየተነሳ ግቦችን እያስቆጠረም ይገኛል። በዚህ ሳምንትም የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ድል እንዲያስመዘግብ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ከመምራት ባሻገር የማሸነፍያዋን ጎል አስቆጥሯል።


ዘላለም ኢሳይያስ (ሀዋሳ ከተማ)

ሀዋሳ ከተማ ወልቂጤን 3-1 በረታበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የዳንኤል ደርቤን ጉዳት ተከትሎ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዘላለም ኢሳይያስ በፍጥነት ጨዋታው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል። ከአለልኝ አዘነና ሄኖክ ድልቢ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ጥሩ የተንቀሳቀሰው ዘላለም ሀዋሳ ከተማ ከአቻነት ወደ መሪነት የተሸጋገረበት ሁለተኛ ግብ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።


ግርማ ዲሳሳ (ባህር ዳር ከተማ)

ይህ ፈጣን የመስመር ተጨዋች በትላንቱ የባህር ዳር ከተማ እና ወልዋሎ ጨዋታ ላይ ልዩነት ፈጣሪ ነበር። ቡድኑ ላስቆጠራቸውም 3 ጎሎች የተጫዋቹ ቀጥተኛ ሚና ጉልህ ነበር (2 ጎል እና 1 አሲስት)። በተለይ ፍጥነቱን እና ክፍሎቱን ተጠቅሞ የሚያደረጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ቡድኑን ሲጠቅም ተስተውሏል። ከዚህ የተነሳም ተጨዋቹ ለ2ኛ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።


አጥቂዎች 

ሀብታሙ ታደሰ (ኢትዮጵያ ቡና)

በአጥቂ ተጫዋቾች ጉዳት ሳቢያ በቅርቡ ወደ መጀመርያ ተሰላፊነት የመጣው ሀብታሙ እያገኘ የሚገኘውን እድል በአግባቡ እየተጠቀመበት ይገኛል። ጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ሀብታሙ በትላንቱ ጨዋታ ከቀኝ መስመር እየተነሳ በጥልቅ ወደ ኋላ እየተሳበ ኳሶችን ከማስጀመር በዘለለ ለሲዳማ ቡና የቀኝ መስመር ተከላካይ ፈተና ሆኖ ውሏል። በፍፁም ቅጣት ምት ለተቆጠረችው ጎል ምክንያት ሲሆን የማሸነፍያዋን ግብ ደግሞ በግንባሩ ማስቆጠር ችሏል።ኦኪኪ አፎላቢ (መቐለ 70 እንደርታ)

በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረግ አልፎ ኳስ እና መረብ ማገናኘት ተስኖት የነበረው ይህ ግዙፍ አጥቂ ከሰበታ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ሁለት ግቦች ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። በጨዋታው በርካታ ሙከራዎች ያደረገው ይህ ናይጀርያዊ አጥቂ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባ የመጀመርያው ነው።


ብሩክ በየነ (ሀዋሳ ከተማ)

በዘንድሮው የሀዋሳ ከተማ ስብስብ ውስጥ ነጥሮ እየወጣ ያለው ብሩክ የቀድሞ ክለቡን በገጠመበት የእሁዱ ጨዋታ ሀዋሳ ወደ ድል እንዲመለስ ከፍተኛውን ሚና ተወጥቷል። ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በ6 ግቦች ከሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ አስቆጣሪዎች ተርታ መመደብ ከመቻሉም በተጨማሪ ለማሳረጊያዋ ግብም ኳሱን አመቻችቶ በማቀበል ድንቅ ቀን አሳልፏል።


ተጠባባቂዎች

ምንተስኖት አሎ (ስሑል ሽረ)

ዓወት ገብረሚካኤል (ስሑል ሽረ)

ምንተስኖት አዳነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ያስር ሙገርዋ (ስሑል ሽረ)

ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)

ቢስማርክ አፒያ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ሙኅዲን ሙሳ (ድሬዳዋ ከተማ)

© ሶከር ኢትዮጰያ