ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ሴንት ሚሼል ዩናይትድ ፡ ታክቲካዊ ምልከታ

የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ በመሆን ሀገራችንን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የመወከል ዕድል ያገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በትላንትናው ዕለት የሲሼልሱን ሴንት ሚሼል ዩናይትድን በውድድሩ ቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን በእጅጉ አስፍቷል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ጨዋታውን ተንተርሶ የታዩ ታክቲካዊ ነጥቦችን እንደሚከተለው አቅርባላችኋለች፡፡

የጨዋታ አቀራረብ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለመደው የ4-3-3 የተጨዋቾች አደራደር (formation) ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ በዚህ አቀራረብ በመሀል ሜዳ ላይ በዋናነት ምንተስኖት አዳነን ከተከላካዮቹ ፊት በማድረግ ኳስ የማጨናገፉን ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ሁለቱ አማካዮች ናትናኤል ዘለቀ እና ምንያህል ተሾመ በአመዛኙ የፈጠራውን ሥራ በመሥራት ከፊት ከሚገኙት አጥቂዎች በተለይም ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር በመሆን የተጋጣሚያቸውን ተከላካዮች በሜዳው ስፋት ወደጎን በመለጠጥ በሚገኙ ክፍተቶች የጎል ዕድሉን በመፍጠርና ከሁዋላ በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች በመታገዝ የሲሼልሱን ክለብ አሸንፎ ለመውጣት ያቀደ ይመስል ነበር፡፡

እንግዳው ቡድን ሴንትሚሼል ዩናይትድ አጠቃላይ የጨዋታ አቀራረቡ በመከላከል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ አጥቂያቸውን ከፊት በማድረግ በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ላይ ወደኋላ በጥልቀት በመሳብና በመከላከል የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጅሙ ወደፊት ለብቸኛውና ፈጣኑ አጥቂያቸው በመጣል የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ያስቡ ይመስሉ ነበር፡፡ ቡድኑ በሚከላከልበት ወቅት ከኋላ ያሉት አራቱ ተከላካዮች የቅዱስ ጊዮርጊስን ሦስቱን አጥቂዎች እንቅስቃሴ የመቆጣጠር እንዲሁም ከተከላካዮቹ ፊት የነበሩት ሁለት ተጨዋቾች የምንያህልንና የናትናኤልን ኳስ የማደራጀት ሥራ ለማቋረጥ ጥረት ሲያረጉ ሁለቱ የመስመር አማካዮቻቸው በበኩላቸው የቅዱስ ጊዮርጊስን የመስመር እንቅስቃሴ ለመግታት ያሰቡ ይመስሉ ነበር፡፡

(ምስል 2)

im 2

የሴንትሚሼል ደካማ የመከላከል አደረጃጀት (Defensive organization)

በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው ግማሽ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የኋላ መስመር በእንቅስቃሴ ክፍተት ሲፈጥር እንዲሁም ተደጋጋሚ የግል ስህተቶችን ሲሰራ ታይቷል፡፡ በተለይም በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች የሲሼልሱ ቡድን ተከላካዮች ኳስን ከግባቸው ለማራቅ በሚያደርጉት ሙከራ ስህተቶችን ሲሰሩ ታይቷል፡፡  ስህተቶቹን ይፈጥሩ የነበሩት ተከላካዮቹ በቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት አጥቂዎች ያን ያህል አስቸጋሪ ጫና (pressing) ሳይፈጠርባቸው ነው፡፡

በመከላከል አደረጃጀቱ ላይ ይስተዋል የነበረው መሠረታዊ ችግር በሜዳው ቁመት በተከላካዮቹና በተከላከይ አማካዮቹ መሀከል በተደጋጋሚ ይታይ የነበረው ሰፊ ክፍተት ነው (ምስል 2 በሰማያዊ መስመሮቹ እንደተመለከተው) ፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የምንያህልና የናትናኤል አጨዋወት ለዚህ ክፍተት አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ በተለይ ምንያህልወደኋላ በመመለስ ኳስን ተቀብሎ ወደሜዳው ሦስተኛ አጋማሽ በሚደርስባቸው አጋጣሚዎች ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች በአንድላይ ወደሱ መሳብ በተመሳሳይ ጊዜ ሦስቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ረጅም ኳስ ለመቀበል ወደፊት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ መስመር ይበልጥ በጥልቀት እንዲመለስ ማድረጉ ሴንትሚሼል ከተከላካዮቹ ፊት ያለው ቦታ እንዲጋለጥበት ምክንያት ሆኗል፡፡ በነዚህ አጋጣሚዎች ረጅም ኳሶችን ወደአጥቂዎች ከመጣል ይልቅ ቀሪው የአጥቂ አማካይ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ኳስን በመቀበል ለአጥቂዎቹ እንዲያደርስ ቢደረግ ይበልጥ የተሻለ ውጤት ያስገኛል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚው ላይ ለነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ብልጫ በሜዳው ስፋትም የተጋጣሚውን ተከላካዮች እንቅስቃሴ መለጠጥ መቻሉ የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሀገር ውስጥ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ እንደምናየው ትላንትም ራምኬል ሎክ እና በኃይሉ አሰፋ በተደጋጋሚ በግራና በቀኝ ቦታ እየተቀያየሩ ተጫውተዋል፡፡ የሁለቱ ተጨዋቾች በሜዳው ሁለት ጥጐችን ይዘው መንቀሳቀስ ለተጋጣሚያቸው ለመከላከል አስቸጋሪ አድርገዋቸው ነበር፡፡ በመጀመሪያው ግማሽ የተገኙት የቅዱስ ጊዮግጊስ ጎሎችም የዚህ እንቅስቃሴው ውጤቶች ነበሩ ሁለቱ የመስመር አጥቂዎችም ራምኬሎክ በግራ መስመር በኩል የተቀበለውን ኳስ ለአዳነ አመቻችቶ በማቀበል እንዲሁም በኃይሉ አሰፋ በአዳነ ግርማ በጭንቅላት የተጨረፈለትን ኳስ በማስቆጠር በሁለቱም ጎሎች ላይ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡

 

የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ግማሽ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ

ከቅድስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ፊት በመገኘት የተከላካይ አማካይነቱን ሚና ይዞ የነበረው ምንተስኖት በጨዋታው አብዛኛውን ጊዜያት የለጫና ተንቀሳቅሷል፡፡ ምንተስኖት ከፊቱ ከሚገኙት ሁለቱ አማካዮች በአንዳቸው /በአብዛኛው በምንያህል/ ወደመከላከል በሚደረግ ሽግግር ወቅት እየታገዘ የተጋጣሚውን ጨዋታ አቀጣጣይ ትሪቮር (ቁ.8) እንቅስቃሴም ሆነ የመስመር አማካዮቹ ወደ መሀል በመግባት ኳስን ለማሻገር የሚያደርጉትን ጥረት በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡  ሁለቱ አማካዮች ናትናኤልና ምንያህልም በተወሰነ መልኩ ኳስን በማንሸራሸርና ክፍተትን በመፈለግ አጥቂዎቹ በተደጋጋሚ ከኳስ ጋር እንዲገናኙ ያደረጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፡፡ በተለይም ምንያህል ቡድኑ ኳስ በሚነጠቅበት ፣ ተጋጣሚ ኳስ ከጎል በሚጀመርበት ፣ እንዲሁም ኳስን ከኋላ መስርቶ ወደተጋጣሚ ሜዳ ለመድረስ ጥረት በሚደረግባቸው ጊዜያት ከምንተስኖት ጎን በመገኘት ሽፋን የሚሰጥበትን የጨዋታ ሂደት ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ወደ አጥቂዎቹ ተጠግቶ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ሚዛኑን ለመጠበቅ ሞክሯል፡፡

im 3

የሁለተኛው ግማሽ የቅዱስ ጊዮርጊስ አቀራረብ

በመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚው ላይ ካሳየው የጎልም ሆነ የጨዋታ የበላይነት አኳያ በሁለተኛው አጋማሽ ባልተጠበቀ መልኩ የተለየ አቅራረብ ይዞ ታይቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ ምንያህል በአብዛኛው ጊዜውን ከምንተስኖት ጎን በመሆን ሲያሳልፍ ናትናኤል ከአጥቂዎቺ ጀርባ የሚገኝ ብቸኛው አማካይ ሆኖ ነበር (ምስል 3) ፡፡ ይህም በቀላሉ በተጋጣሚ ተጨዋቾች እንዲያዙ አድርጎታል፡፡ የመጀመሪያው 45 ያየነውን የተሻለ የኳስ ፍሰትም ቀንሶታል፡፡ የምንያህል ሚና በሜዳው አጋማሽ መገደቡ የሴንት ሚሼሉ ካኒር በተሻለ ወደፊት ተጠግቶ እንዲጫወት ዕድል ሰጥቶት ነበር፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጥቂዎቹና በተከላካዮቹ መካከል በሜዳው ቁመት ያለው ርቀት ሰፍቶ ኳስ ከኋላ ወደ አጥቂዎቹ በረጅሙ መጣል ብቸኛው አማራጭ መስሎ ታይቷል፡፡ የዚህ ምክንያትም የምንያህል ወደፊት ተጠግቶ የመጫወት ሚና (Advanced role) መገደቡ አንድ ምክንያት ነው፡፡ ምናልባትም ይህ ያልተጠበቀ አቀራረብ ውጤትን ከማስጠበቅ አንፃር የተደረገ የሚያስመስለው አስቻለው ታመነ በምንያህል ተቀይሮ ገብቶ የቀኝ መስመር ተከላካይነትን ቦታ ሲይዝና አሉላ ወደመሀል ሜዳ ሲመጣ ነው፡፡ ይህም ቅያሪ በተፈጥሮ የተከላካይነት ባህሪ ያለውን አሉላን ከምንተስኖት ጋር ማጣመሩ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን በማንሸራሸር ሦስተኛው የሜዳው ክፍል የመድረስንና ተከላካዮችን የመረበሹ ነገር በሁለተኛው አጋማሽ በረጃጅም ኳሶች ለመተካቱ ሌላ ምልክት ነበር፡፡

ነገር ግን የ75ኛው ደቂቃ ቅያሪ ቡድኑ በመጠኑ ወደመጀመሪያው አቀራረብ የመለሰው ይመስል ነበር፡፡ የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ናይጄሪያዊው ጎድዊን ቻካ ናትናኤልን ቀይሮ በገባበት ሰዐት የፊት አጥቂነቱን ቦታ ሲይዝ አዳነ ከሱ ጀርባ በመሆን ምንያህል በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረውን ኳስ የማደራጀቱን ሚና ወደመሸፈኑ መቷል፡፡ ይህ የሚና ለውጥም ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡

 

የሴንት ሚሼል የተጨዋቾችና የሚና ለውጦች

የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ጫና መቀነስ ካኒር (ቁ.13) ወደፊት ተጠግቶ እንዲጫወት ነፃነት ሰቶታል፡፡ ተጨዋቹ የቀኝ መስመር ተሰላፊው ገርቫይስ (ቁ. 11) በ 2015 የአመቱ የሲሸልሽ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠው ካርል ሀል (ቁ. 27) ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ወደፊት ተጠግቶ በመጨዋቱ ቀጥሎበት ነበር፡፡ ከተጠቀሰው ቅያሪ በኋላ ግን ካኒር እራሱ ተቀይሮ እከወጣበት ጊዜ ድረስ በቀኝ መስመር አማካይነት ሚና ተጫውቷል፡፡ ካርል (ቁ.27) በቀሪው ሰአት ትሪቮር (ቁ.8) መሸፈን ያልቻለውን የፈጣሪ አማካይነት ሚና ለመወጣት ሞክሯል፡፡ ትሪቮር (ቁ.8) በዚህ ጊዜ መጀመሪያ ካኒር ይጫውትበት ወደነበረው የተከላካይ አማካይነት ሚና ላይ ታይቷል፡፡  በተጨማሪም ቡድኑ በግራ መስመር ጨዋታውን የጀመረውንና በጨዋታው አብዛኛው ሰዓት በዛው መስመር ላይ የነበረውን ሊሮይ (ቁ10) ከብቸኛው የፊት አጥቂ ጃኮት (ቁ 14) ጋር በመቀየር የፊት መስመራቸውን ለወጥ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ነገርግን እነዚህ የሚናና የቦታ ለውጦች ግን ይህ ነው የሚባልና የሚታይ ውጤት ሊቀይር የሚያስችል የግብ ዕድል ሳይፈጥሩላቸው ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

im 4

በጥቅሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተገጣሚው በመጀመሪያው አጋማሽ ካሳየው የወረደ አቋም አንፃር በሁለተኛው አጋማሽ ቁጥራቸው የበዙ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ውጤቱን ከዚህም በላይ ማድረግ ይችል ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ቢሆንም ቡድኑ ከመረጠው የጥንቃቄ ጨዋታ አንፃር ግብ ሳይቆጠርበት ሁለተኛውን 45 ማጠናቀቁ ለመልሱ ጨዋታ የተሻለ ዕድል እንዲኖረው የሚረዳ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *