የፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ሁለተኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል።

👉 አዲስ ታሪክ ከ41 ሳምንታት በኋላ

በዚህ ሳምንት የተደረጉት ስምንት ጨዋታዎች በሙሉ በመሸናነፍ ተጠናቀዋል። ይህም በፕሪምየር ሊጉ ከ41 የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተከሰተ መሆኑ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ ሁሉም የሳምንቱ ጨዋታዎች በመሸናነፍ የተጠናቀቁት በሐምሌ ወር 2010 (30ኛ ሳምንት ላይ) ነበር።

👉 በ107 ሳምንታት ውስጥ የተከሰተ አዲስ ክስተት

በዚህ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ ሁሉም ባለሜዳ ቡድንም ድል አስመዝግቧል። በተለምዶ “ባለሜዳ ሁልጊዜ ያሸንፋል” በሚባልበት ሊጋችን ላይ ይህን ክስተት ለመመልከት ግን 107 የጨዋታ ሳምንታትን ማሳለፍ ግድ ይላል። በ2008 የውድድር ዘመን 20ኛ ሳምንት ሁሉም ባለሜዳ ቡድኖች ካሸነፉ በኋላ ከሁለት ዓመታት በላይ ይህን ሳንመለከት ቆይተናል። 

👉 ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአስራ ሁለተኛው ሳምንት 24 ጎሎች ተቆጥረዋል። ባለፈው ሳምንት ከተቆጠረው የጎል ብዛት በአራት ከፍ ማለት ሲችል በአጠቃላይ በ9ኛው ሳምንት ከተቆጠረው 25 ጎል ቀጥሎ ሁለተኛው ነው ። 

– በዚህ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና መካከል የተደረገው ጨዋታ ከአጠቃላይ ጎሎች 1/3 የሚሆኑት ተቆጥሮበታል።

– በዚህ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ብዛት እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ስድስት ሆኗል። ሁሉም (ስድስቱም) ጎል ያላስቆጠሩ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ የተጫወቱ ናቸው።

– በዚህ ሳምንት 20 ተጫዋቾች (በራስ ላይ የተቆጠረ ጨምሮ) ጎል በማስቆጠር ተሳትፈዋል። ጌታነህ ከበደ፣ አህመድ ሁሴን፣ እዮብ ዓለማየሁ እና አቤል ያለው ሁለት ጎሎች ማስቆጠር ሲችሉ ቀሪዎቹ 13 ተጫዋቾች (እና አንድ ራስ ላይ) አንድ አንድ ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ከተቆጠሩት 24 ጎሎች መካከል 18 ጎሎች በአጥቂ (የመሐል እና የመስመር) ተጫዋቾች ሲቆጠሩ 2 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 2 ጎል (በራስ ላይ ጨምሮ) ደግሞ ከተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተገኝቷል።

– ከ24 ጎሎች መካከል 21 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ 1 ጎል ከቅጣት ምት ተሻምቶ ተቆጥሯል። ሁለት ጎሎች ደግሞ ከፍፁም ቅጣት ምት ተቆጥረዋል።

– ከዚህ ሳምንት 24 ጎሎች መካከል ሰባት ጎሎች በግንባር ተገጭተው ተቆጥረዋል። ይህም ከባለፈው ሳምንት ጋር በጋራ የዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ነው። የተቀሩት 17 ጎሎች የተቆጠሩት በእግር ተመትተው ነው።

– ከ24 ጎሎች መካከል 21 ጎሎች ሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 3 ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ጎል ሆነዋል።

👉 ካርዶች በዚህ ሳምንት

– ይህ ሳምንት ምንም ቀይ ካርድ ያልተመዘዘት ሆኖ አልፏል። 

– ጅማ አባ ጅፋር ከ መቐለ 70 እንደርታ ያደረጉት ጨዋታ ምንም ካርድ ያልተመዘዘበት ብቸኛ የሳምንቱ መርሐ ግብር ነበር። 

– እንደ 11ኛው ሳምንት ሁሉ በዚህ ሳምንት አምስት ቡድኖች ማስጠንቀቂያ ካርድ ሳይመለከቱ ወጥተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ምንም የማስጠንቀቂያ ካርድ ያልተመለከቱ ቡድኖች ናቸው። ስሑል ሽረ ደግሞ በ3 ቢጫ ከፍተኛውን የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተ ቡድን ሆኗል።

👉 የዓመቱ ፈጣን ጎል 

በዚህ ሳምንት ወላይታ ድቻ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን 3-0 ሲያሸንፍ እዮብ ዓለማየሁ ያስቆጠራት የመጀመርያ ጎል የውድድር ዓመቱ ፈጣን ጎል ሆና ተመዝግባለች። በ40 ሰከንድ ውስጥ በመቆጠር…

👉 የአቤል ያለው የጎል ተሳትፎ

– በዚህ ሳምንት እንደ አቤል ያለው የደመቀ ተጫዋች አልተገኘም። ሁለት ኳሶች ከመረብ ሲያገናኝ ሁለት ኳሶችን ደግሞ ከግብ አስቆጣሪዎች ጋር አገናኝቷል።

👉 የወላይታ ድቻ ታሪካዊ ድል

በርካታ አዳዲስ ታሪኮች በተመዘገቡበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ማሸነፉን ተከትሎ የጦና ንቦቹ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ብርቱካናማዎቹን ያሸነፉበት ሆኖ ተመዝግቧል።

👉 የድቻ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ከተሰናባቹ አሰልጣኝ ስምዖን ጋር መገጣጠም

ሶዶ ላይ የተደረገውን ጨዋታ ተከትሎ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል። አሰልጣኙ ከአንድ ዓመት በፊት በረዳትነት ሲያገለግሉ የነበረውን ቡድን የተረከቡት ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ስንብት በኋላ ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታቸውን በዋና አሰልጣኝነት የመሩትም ወላይታ ድቻን ሶዶ ላይ ገጥመው 1-1 በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ነበር።

👉 ባኑ ዲያዋራ እና ሳሊፍ ፎፋና 

ሁለቱ የውጪ ዜጎች በዚህ ሳምንት ከአቤል ያለው በመቀጠል ጎል በማስቆጠር ተሳትፎ ያደረጉ ተጫዋቾች ናቸው። ባኑ አንድ አስቆጥሮ ለፍፁም ሲያመቻች ፎፋናም አንድ አስቆጥሮ ለአብዱለጢፍ መሐመድ አመቻችቷል። 

👉 ቸርነት ጉግሳ 

– ወጣቱ የመስመር አጥቂ በዚህ ሳምንት ቡድኑ ድሬዳዋን 3-0 ሲያሸንፍ ሁለቱን በማመቻቸት ጥሩ ቀን አሳልፏል። ተጫዋቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ጎሎች ላይ መሳተፍ ችሏል። 

👉 ድሬዳዋ ከተማ 

– በሊጉ መጥፎ ከሜዳ ውጪ ሪከርድ ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ በዚህ ሳምንት ወደ ሶዶ ተጉዞ 3-0 መሸነፉ ይታወሳል። በዚህ ጨዋታ ጎሎች ማስተናገዱን ተከትሎም ለ15ኛ ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታ መረቡን አስደፍሮ ተመልሷል። 

👉 በዚህ ሳምንት…

– በዚህ ሳምንት ሰባት ተጫዋቾች ዘንድሮ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ከጎል ጋር ተገናኝተዋል። አቡበከር ሳኒ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አሕመድ ሁሴን (ወልቂጤ ከተማ)፣ እዮብ ዓለማየሁ ( ወላይታ ድቻ)፣ ባኑ ዲያዋራ (ሰበታ ከተማ)፣ ነፃነት ገብረመድህን (ስሑል ሽረ)፣ ሱሌይማን ሰሚድ (አዳማ ከተማ)፣ ዮሴፍ ዮሐንስ (ሲዳማ ቡና) ለመጀመርያ ጊዜ ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

በሶከር ኢትዮጵያ የሚወጡትን ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች በቀጥታም ሆነ በግብዓትነት ሲጠቀሙ ምንጭ ይጥቀሱ።