ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት እሁድ እና ሰኞ መደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በርካታ ተጫዋቾች ምርጥ ብቃታቸውን ያሳዩበት ሳምንትም ሆኖ አልፏል። እኛም እንደተለመደው በሳምንቱ አንፃራዊ ብቃታቸው ከፍ ያሉትን መርጠን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው። 

አሰላለፍ፡ 3-4-3


ግብ ጠባቂ 

ሰዒድ ሀብታሙ (ጅማ አባ ጅፋር)

ሰዒድ በዚህ ሳምንት ጅማ ጠንካራው መቐለ 70 እንደርታን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ለቡድኑ ድል ከፍተኛ ሚና ከተወጡት ተጫዋቾች መካከል ነበር። በጨዋታው ሰዒድ ወደ ጎልነት ሊቀየሩ የሚችሉ አራት መልካም አጋጣሚዎችን ያመከነ ከመሆኑ በተጨማሪ ከቆሙ ኳሶች በረጅሙ ወደ ግብ ክልሉ ሲደርሱ የነበሩ ተደጋጋሚ ኳሶችን ቀድሞ በመውጣት አደጋ እንዳይፈጥሩ ያደረገበት ጥረት በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲካተት አስችሎታል።


ተከላካዮች 

ደስታ ደሙ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ በመስመር ላይ ትኩረቱን ላደረገው የማጥቃት መንገዳቸው በቀኝ መስመር በኩል ትክክለኛውን ሰው ያገኙ ይመስላሉ። ከተመራጭ የመሐል ተከላካይነት ቦታው ሽግሽግ በማድረግ የቀኝ ተከላካይነት ቦታ ላይ እየተጫወተ የሚገኘው ደስታ ሲዳማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከመከላከሉ ባሻገር በማጥቃት ሽግግሩ ላይ በነበረው ሚና ጉልህ ነበር። አቤል ያለው ላስቆጠረው የመጀመርያ ጎልም ኳሱን አመቻችቶ በማቀበል እገዛ አድርጓል። ቦታውን እየተላመደ የሚገኘው ደስታ ደሙ በሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ተመርጧል።


መሐመድ ዐወል (ወልቂጤ ከተማ)

ቡድኑን በቶሎ የተላመደው መሐመድ አወል በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ ውስጥ ቀድሞ ስሙ የሚጠራ ምሶሶ መሆኑን ቀጥሏል። በ12ኛው ሳምንት ወልቂጤ የጣና ሞገዶቹን 2-0 በረታበት ጨዋታ የባህር ዳርን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከማቋረጥ አንስቶ በአየር ላይ ኳሶች እና አንድ ለአንድ በነበረው ግንኙነት የነበረው የበላይነት ስኬታማ ቀን እንዲያሳልፍ ረድቶታል። በተለይም በአጥቂ ስፍራ ላይ የነበረው ስንታየሁ ከተቀረው ቡድን እንዲነጠል በማድረግ አይነተኛ ሚናን ተውጥቷል።


ኤድዊን ፍሪምፖንግ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ባለፉትን ሁለት ዓመታት በርከት ያሉ የውጭ ተጫዋቾች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢመጡም እንደ ፍሪምፖንግ የተሳካለት ተጫዋች አልተገኝም። በትኩረት የመከላከል ብቃቱን እየተወጣ ያለው ታታሪው ተከላካይ ፈረሰኞቹ ሲዳማ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ የአዲስ ግደይ እና የይገዙ ቦጋለን ፈጣን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ረገድ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል። ፍሪምፖንግ በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የነበረው ስኬት እና የሸርቴዎቹ ውጤታማነት በሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል።


አማካዮች

እዮብ ዓለማየሁ (ወላይታ ድቻ)

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ወጥ አቋም እያሳዩ ካሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነውና ረዘም ካለ ጉዳት ከተመለሰ በኋላ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ወደ ሜዳ ተመልሶ ወላይታ ድቻን በሚገባ እያገለገለ የሚገኘው እዮብ በዚህ ሳምንት በሜዳው ድሬዳዋን 3ለ0 ሲረታ ፈጣኗን የዓመቱን ጎል ጨምሮ ሁለት ግቦችን ለቡድኑ በማስቆጠር በደጋፊው ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ያገኘ ሲሆን በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያደረገው እንቅስቃሴም አስገራሚ ነበር።

ነፃነት ገብረመድህን (ስሑል ሽረ)

ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ መሻሻሉን የቀጠለው ወጣቱ የተከላካይ አማካይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ አንድ ግብ አስቆጥሮ ጥሩ እንቅስቃሴም አድርጓል። ተጫዋቹ ከዚ በፊት እንደ ድክመት ይቆጠርበት የነበረው በርካታ የሜዳ ክፍል አካሎ የመጫወት ብቃት በዚህ ጨዋታ በብዙ መልክ ማሻሻሉ ተጫዋቹ በጥሩ እድገት እንደሚገኝ ማሳያ ነው። ተጫዋቹ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ፉዓድ ፈረጃ (አዳማ ከተማ)

አዳማ ከተማዎች ድንቅ በነበሩበትና ኢትዮጵያ ቡናን በረቱበት የእሁዱ ጨዋታ ላይ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴን በዋና ተዋናይነት በመምራት ምርጥ ቀን አሳልፏል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ለተከተሉት ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን ላይ አይተኬ ሚናን ሲወጣ የነበረው ወጣቱ አማካይ በጨዋታው የነበረው ዕይታና እርጋታም እጅግ የተለየ ነበር።

ዓብዱልለጢፍ መሐመድ (ስሑል ሽረ)

በተከታታይ ጨዋታዎች በወጥነት ጥሩ ብቃት በማሳየት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆን የቻለው ይህ ጋናዊ የመስመር አማካይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ጥሩ በመንቀሳቀስ አንድ ግብ አስቆጥሮ ለበርካታ የግብ ዕድሎች መፈጠርም ምክንያት ሆኗል። በስሑል ሽረ የማጥቃት አጨዋወት የማይተካ ሚና ያለው ይህ ፈጣን አማካይ በመስመር በሚያደርጋቸው ፈጣን የመልሶ ማጥቃቶች የሀይቆቹን የተከላካይ መስመር ሲፈትን ውሏል።  ተጫዋቹ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባም ለሁለተኛ ጊዜው ነው።


አጥቂዎች

አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ፈረሰኞቹ የዓመቱን ከፍተኛ የጎል መጠን ባስቆጠሩበት የሲዳማ ቡና ጨዋታ የፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው እንቅስቃሴ አስገራሚ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ካስቆጠራቸው ስድስት ግቦች በአራቱ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው በዚህ ሳምንት እንደርሱ ጎልቶ የወጣ ተጫዋች የለም ለማለት ያስደፍራል። በሶከር የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ሲገባም ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

አህመድ ሁሴን  (ወልቂጤ ከተማ)

ተከታታይ ድል እያስመዘገበው የመጣው ወልቂጤ ከተማ በዚህ ሳምንት ጎል ማስቆጠር ባስፈለገው ሰዓት የደረሰለት አህመድ ሁሴን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የጨዋታው ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን ሁለቱንም የድል ጎሎች ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ለባህር ዳር የተከላካይ ክፍል ራስ ምታት ሆኖ ውሏል። በተለይም ሁለተኛ ግብ ሲያስቆጥር በግሉ ኳሱን ይዞ ወደ አደጋ ክልል የገባበትና የግብ ጠባቂውን አቋቋም በማሳት ያስቆጠረበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነበር።

ጌታነህ ከበደ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ጌታነህ ከበደ ወደ ሙሉ ጤንነቱ ተመልሶ ባለፈው ዓመት ብዙ ተጠብቆበት የታሰበውን ያህል የላስደሰተውን ደጋፊም ሆነ ክለቡን እየካሰ ይገኛል። በዘንድሮ ዓመት ፈረሰኞቹ ወደናፈቁት ዋንጫ ለመጓዝ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ልምዱን፣ የአጨራረስ ብቃቱን እና ቡድኑን አጋሮቹን በመልበሻ ክፍልም በሜዳ ላይም የሚያነቃቃበት መንገድ ጌታነህ ትክክለኛ ብቃቱ ላይ መመለሱን ማረጋገጫ ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡና ላይ የጎል ናዳ ሲያዘንብም የተጠቀሱትን ሁሉ በሜዳ ላይ ሲያሳይ ውሏል። ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ወደ አስፈሪነቱ መመለሱን እያስመሰከረ የመጣው ጌታነህ ከበደ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ መካተት ችሏል።


ተጠባባቂዎች

ወንድወሰን አሸናፊ (ስሑል ሽረ)

መላኩ ወልዴ (ጅማ አባ ጅፋር)

ሄኖክ አዱኛ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

እድሪስ ሰዒድ (ወላይታ ድቻ)

ከነዓን ማርክነህ (አዳማ ከተማ)

ባኑ ዲያዋራ (ሰበታ ከተማ)

ሳሊፍ ፎፋና (ስሑል ሽረ)© ሶከር ኢትዮጵያ