የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ወላይታ ድቻ

በተከታዩ መሰናዷችን ከመጥፎ አጀማመር በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጥሩ አቋም በመምጣት በ21 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ አጋማሹን ያጠናቀቀው ወላይታ ድቻን እንመለከታለን።

የውድድር ዘመን ጉዞ

ቡድኑን ለረጅም ዓመታት ከመሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር ከተለያየ በኋላ በአሰልጣኝ ቅጥር ዙርያ መረጋጋት የተሳነው ወላይታ ድቻ ዓምና ዘነበ ፍስሀን በውጤት ማጣት የተነሳ የመጀመርያው ዙር መገባደጃ ላይ ከኃላፊነት ካነሳ በኋላ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመቅጠር መሻሻል አሳይተው በሊጉ መቆየት የቻሉ ሲሆን አሸናፊ በቀለ ወደ አዳማ ማምራታቸውን ተከትሎ በክረምቱ ገብረክርስቶስ ቢራራን በመቅጠር እና ከከፍተኛ ሊጉ ቡድኖች ጥቂት ተጫዋቸችን በማስፈረም ነበር የውድድር ዘመኑን የጀመረው።

የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታውን ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ ከጥሩ ድባብ ጋር 2-0 በማሸነፍ ሊጉን በድል የጀመረው የገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን የአጀማመሩን ያህል መዝለቅ ተስኖት ለቀጣይ ሁለት ወራት ከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ ገብቷል። በሁለተኛ ሳምንት ወደ መቐለ ተጉዞ በወልዋሎ 2-1 ከተሸነፈ በኋላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ (በሜዳው) እና ከአዳማ ከተማ (ውጪ) አቻ ተለያይቶ በወልቂጤ ከተማ (በሜዳው) እና ሰበታ ከተማ (ውጪ) ሽንፈት አስተናግዷል። በመቀጠልም በተከታታይ ከፋሲል (አቻ) እና ስሑል ሽረ (ሽንፈት) በሜዳው ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ከደጋፊዎች ጠንከር ያለ ተቃውሞ የገጠመው ቡድኑ በመጨረሻም ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ጋር ለመለያየት ተገዷል።

ቡድኑ ከአሰልጣኙ ስንብት በኋላ በ2011 አንድ ጨዋታ በጊዜያዊነት መርቶ የነበረው ደለለኝ ደቻሳን በጊዜያዊነት ሲሾም የውጤት መሻሻልም በፍጥነት ማምጣት ችሏል። ከሹመቱ ጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ጅማ ያመሩት ድቻዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ከመመራት ተነስተው 2-1 በማሸነፍ ከ7 ጨዋታ በኋላ ወደ ድል መመለስ ሲችሉ በመቀጠል መቐለ 70 እንደርታን 1-0 አሸንፈው ይበልጥ አንሰራርተዋል። በ10ኛው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ጎል ተሸንፈው ቢወጡም በቀጣይ ባደረጓቸው 3 ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፈው በ15ኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ተሸንፈው ነበር የመጀመርያውን ዙር ያጠናቀቁት።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ድቻ ዐምና በዚህ ወቅት የወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የነበረ ሲሆን ከ15 ጨዋታዎች 15 ነጥብ ሰብስቦ በ13ኛ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር። ዘንድሮ በአንፃሩ ከዓምናው በ6 የበለጡ ነጥቦችን የሰበሰበው ቡድኑ በ4 የበለጡ ጎሎችን አስቆጥሮ እንዲሁም በአንድ ያነሰ ጎል አስተናግዶ 7ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ደረጃውን መሻሻል ችሏል።

የቡድኑ አቀራረብ

የውድድር ዘመኑን አጋማሽ በሁለት አሰልጣኞች ሥር የነበረው ቡድኑ ከማሸነፍ ፍላጎት መነሳሳት በቀር ይህ ነው የሚባል ጉልህ የአቀራረብ ልዩነት አልተመለትንበትም። ወደ 4-2-1-3 በቀረበ አደራደር ወደ ሜዳ የሚገባው ቡድኑ በመሰረታዊነት ማጥቃቱን ከፊት ለሚገኙት አራት ተጫዋቾች እንዲሁም የመከላከል ሥራውን ደግሞ በተቀሩት ስድስት ተጫዋቾች የሚከወን ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይስተዋላል። በመጀመርያዎቹ ሳምንታት 4-1-4-1 እና 4-3-3 እያፈራረቀ ሲጠቀም የነበረው ቡድኑ ከደለለኝ መምጣት በኋላ 4-3-3 አሰላለፍን ቀዳሚ ምርጫው አድርጓል። በአማካይ ሥፍራ የሚያሰልፋቸው ተጫዋቾች ባህርይ (ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች እና አንድ የአጥቂ አማካይ) ምክንያትም በእንቅስቃሴ ወደ 4-2-3-1 / 4-2-1-3 ሲለዋወጥ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።

በግብጠባቂ ስፍራ ላይ መክብብ ደገፉ እና መኳንንት አሸናፊን ሲጠቀም የሚስተዋለው ቡድኑ በተለይ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ የማሰልጠን ወቅት በተወሰነ መልኩ ከኋላ ለመመስረት በሚያደርጉት ጥረት የሁለቱ ግብ ጠባቂዎች በእግር ኳስ የመጫወት አቅም በእጅጉ ሲፈተንና ሲቸገር የተስተዋለበት ሒደት የሚታወስ ነው።

በመሐል ተከላካይነት በዋነኝነት አንተነህ ጉግሳ እና ደጉ ደበበን የሚጠቀመው ቡድን ሁለቱም ተከላካዮች ካላቸው የተሻለ የቦታ አረዳድ እና ደካማ የማፈትለክ አቅም አንፃር ለራሳቸው ግብ ክልል ቀርበው የመከላከላቸው ነገር የተለመደ ሒደት ሲሆን ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ፀጋዬ አበራ እና ያሬድ ዳዊት/እዮብ ዓለማየሁ ከመሐል ተከላካዮቹ ትይዩ በመቆሞ በዝርግ የኃላ አራት የተከላካይ መስመር ሲጫወቱ ይስተዋላል። በአሰልጣኝ ደለለኝ ስር እዮብ ወደ መስመር አጥቂነት ተሸጋግሮ ውብሸት ደሳለኝ ወደ መሐል ተከላካይ በመውሰድ አንተነህ ጉግሳን በመስመር ተከላካይነት ሲጠቀም የተስተዋለው ቡድኑ በአንፃራዊነት ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት እንዲኖረው አድርጓል።

ከተከላካዮቹ ፊት ምንም እንኳን በአሁኑ የዝውውር መስኮት ክለቡን ይልቀቅ እንጂ ተስፋዬ አለባቸው እና የውድድር ዓመቱን በጉዳት የጀመረውና አገግሞ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው በረከት ወልዴ የቡድኑን የመከላከል ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ወደር የማይገኝለትን ሚና ተወጥተዋል። በተለይ በረከት ወልዴ ተጋጣሚ ተጫዋቾች መሐል ሜዳ ላይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማቋረጥ ድፍረት የተሞላባቸውን ውሳኔዎች በመወሰን በመከላከል ሽግግር ወቅት መገኘት በሚገባው ቦታ መገኘት ሳይችል በመቀረቱ ቡድኑ ላይ አደጋ ቢጋብዝም ጥቃቶችን በማቋረጥና ቦታው የሚፈልገውን “አስቀያሚ ተግባር” በመወከወን ረገድ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ይስተዋላል።

ከሁለቱ ተጫዋቾች ፊት በብዛት የሚሰለፈው እድሪስ ሰዒድ ምንም እንኳን ከሳምንት ሳምንት በሚጠበቅበት ልክ በወጥነት ቡድኑን ባያገለግልም በተለይ ድቻን ለማጥቃት ከሚፈልጉ ተጋጣሚዎች ጋር በሚኖሩ ግጥሚያዎች ይበልጥ ሲጎላ ይስተዋላል። የተሻለ የቴክኒክ አቅም ያለው ተጫዋቹ 90 ደቂቃ በብርታት ለመጫወት ግን እንደሚቸገር የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ያሳየን ሌላው እውነታ ነው።

የፊት መስመሩ በጉዳት ቢታመስም ሁለቱ ወጣት የመስመር ተጫዋቾች ቸርነት ጉግሳ እና እዮብ ዓለማየሁ ሙሉ ጤንነታቸው ላይ ሆኖ ሲያገኝ እጅግ አስፈሪ መልክ ይላበሳል። በዓመቱ መጀመርያ በጉዳተ እና በቦታ ሽግሽግ እምብዛም ሚና ያልነበራቸው ሁለቱ ተጫዋቾች በቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ስልት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ተጫዋቾች ሲሆኑ ፍጥነታቸውን በመጠቀም የተጋጣሚ ቡድን የተከለላካይ መስመር ሲበታትኑ ይስተዋላል። በፊት መስመር የሚሰለፈው አጣማሪያቸው ባዬ ገዛኸኝ የፊት መስመሩ ተጨማሪ ሞገስ ነው። የቡድኑን የጎል ማስቆጠር ኃላፊነት ለብቻው በመሸከም በወጥነት ከፍተኛ ግልጋሎት አበርክቷል።

ጠንካራ ጎን

ከጨዋታ ጨዋታ እያሳየ የሚገኘው መሻሻል እና (ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ) በተነሳሽነት መጫወት የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። በተለያየ የውጤት ፅንፍ ላይ የሚገኙ ሁለት ዓይነት አጋማሽ ያሳለፈው ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሁለት ወራት በቀላሉ ስህተት የሚሰራ እና ለማሸነፍ የሚቸገር ሲሆን ከለውጥ በኋላ በብዙ ቡድኖች እንደሚታየው እና አሰልጣኝ ደለለኝ በተደጋጋሚ የድኅረ ጨዋታ ቃለምልልስ ወቅት እንደሚገልፁት በከፍተኛ ተነሳሽነት የሚጫወት ቡድን መሆኑ በጉልህ ይታያል።

የመከላከል ጥንካሬው ሌላው የሚጠቀስ ጎን ነው። ቡድኑ በመጥፎ የውጤት ጎዳና በሚጓዝበት ውቅትም ያስተናገደው የጎል መጠን መጥፎ የሚባል አልነበረም። (በ8 ጨዋታ 9 ጎሎች አስተናግዷል) ይበልጡኑ ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ ደግሞ ጎል በቀላሉ የማይቆጠርበት ቡድን ሲሆን (በ7 ጨዋታ 6 ጎሎች ተቆጥሮበታል) ከ7 ጨዋታዎች በአራቱ ጎል ሳያስተናግድ መውጣት ችሏል።

የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ተጫዋች በቡድኑ ውስጥ የሌለው ቡድን በቋሚነት ከሚጠቀምባቸው ተጫዋቾች ወደ ግማሽ የሚጠጉት በቅርብ ዓመታት ከክለቡ የእድሜ እርከን ቡድኖች ያደጉ ናቸው። ይህም ቡድኑ በወጣት ተጫዋቾች ላይ ያለውን የፀና እምነት የሚያሳይ ሲሆን በተጨማሪም ከጥቂት ተጫዋቾች ውጪ በዝቅተኛ ወጪ ከከፍተኛ ሊግ ቡድኖች የሰበሰባቸው ተጫዋቾች ቡድኑን አዋቅሮ ተፎካካሪ ለመሆን መሞከሩ ለሌሎች ክለቦች እንደ አርዓያ የሚታይ ተግባር ነው።

ደካማ ጎን

በመጀመሪያው ዙር የቡድኑ ዋነኛ ድክመት ሆኖ የተስዋለው እንደ ቡድን መንቀሳቀስ ችግር ነው። ይህም ቡድኑ በበርካታ የጨዋታ ቅፅበቶች ላይ ወደ ሁለት ተከፍሎ በሚያጠቃውና በሚከላከለው የቡድኑ ክፍል መሀል ሰፋፊ ክፍተቶች ሲተዉ ይስተዋላል። እነዚህን ክፍተቶች ተገንዝቦ ለማጥቃት የሚደረገው ጥረት አናሳ ሆነ እንጂ አደገኝነታቸው የሚያጠያይቅ አይደለም።

በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት የሚታመሰው ቡድኑ ተጫዋቾች ለመተካት ሲቸገር ይስተዋላል። በተከላካይ ስፍራ እንደልብ አማራጭ የሌለው ቡድኑ በአማካይ ስፍራም የተስፋዬ አለባቸው መልቀቅ ተጨምሮበት ቦታው ላይ ክፍተት መፈጠሩ አይቀሬ ነው። በአጥቂ ስፍራ ላይም የባዬ ገዛኸኝ ጥገኛ የሆነ ሲሆን ተጫዋቹ በማይኖርባቸው ወቅቶች ቡድኑ ምን ያህል እንደተቸገረ ተስተውሏል።

ይህን የቡድን ጥልቀት ችግር ለመቅረፍ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት እንቅስቃሴን እያደረገ የሚገኘው ቡድኑ በርከት ባሉ ቦታዎች ላይ የአማራጭ ተጫዋቾች እጥረት እንዳለበት በመጀመሪያው አጋማሽ የተስተዋለ ሀቅ ነው።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ከለውጦች በኋላ የሚኖረውና በወላይታ ድቻ ላይም ባለፈው ወር የታየው ከፍተኛ መነሳሳትን ማስቀጠል የመጀመርያው የአሰልጣኙ የቤት ሥራ ነው። አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ከጊዜያዊነት ወደ ዋና አሰልጣኝነት በመሸጋገራቸው ሙሉ ትኩረታቸውን የተረጋጋ ጊዜ አሳልፎ የውድድር ዘመኑን እንዲጨርስ ማድረግ ይሆናል። በትልቅ ደረጃ የማሰልጠን ልምድ የሌላቸው አሰልጣኙ በውጥረት በሚሞላው ሁለተኛው ዙር በሚኖሩ የውጤት ከፍታ እና ዝቅታ የቡድኑን መንፈስ መጠበቅ ከፍተኛ የቤተ ስራ ይጠብቃቸዋል።

ባለው የዝውውር መስኮት ተጠቅመውም ሆነ እድል ላላገኙ ተጫዋቾች እድል በመስጠት የስብስብ አማራጭ ማስፋት ሌላው ከቡድኑ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በየሳምንቱ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የተጫዋቾች ምርጫ የሚጠቀመው ቡድኑ ሌሎቹን ተጫዋቾች አዕምሯቸውን ለጨዋታ ዝግጁ በማድረግ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። እስካሁን መሐመድ ናስር (አጥቂ)፣ አበባው ቡታቆ (ተከላካይ) እና ሚካኤል ለማ (አማካይ) ያስፈረመው ቡድኑ የመሐል ተከላካይ እና የተከላካይ አማካይ አማራጮቹን በዝውውር መስኮቱ ማሰረፋት ይኖርበታል።

የመጀመሪያው ዙር ኮከብ ተጫዋች

እድሪስ ሰዒድ፡ በከፍተኛ ሊጉ ለረጅም ጊዜ የተጫወተውና ዘንድሮ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አማካኝነት ወደ ክለቡ የመጣው እድሪስ መልካም ግማሽ ዓመት አሳልፏል። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በዋነኝነት የሚመራ ሲሆን የሚታይበትት የወጥነት ችግር መቅረፍ ከቻለ ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር ከተጫዋቹ ብዙ እንደሚያገኝ እርግጥ ነው።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ታምራት ሥላስ፡ በ20 ዓመት በታች ቡድኑ ጥሩ ጊዜ አሳልፎ ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ታምራት በመጀመርያው ዙር ጥቂት ጨዋታዎች ያደረገው ታምራት በሁለተኛው ዙር የተሻለ የመሰለፍ እድል የሚያገኝ ከሆነ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሊያሳይ የሚችል ወጣት ነው። በፊት አጥቂነት የሚጫወተው ታምራት ጥቂት ተጫዋች ባለው የፊት መስመር ላይ በሁለተኛው ዙር አማራጭ እንደሚፈጥር ተስፋ የሚጣልበት ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ