የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት እና እግርኳስ

በፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ በተለይም በከተማዋ ከሚገኘው የባህር እንስሳት ገበያ ሰራተኞች ላይ ያልተለመደ የሳምባ ምች በሽታ እንደተከሰተ የሃገሪቱ መንግስት ለዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ። በጥር ወር ላይም የጥቃቅን ህዋስያን ተመራማሪዎች በሽታውን የሚያመጣውን አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መለየታቸውን አስታወቁ፤ የቫይረሱ ስያሜ 2019-nCov (ኖቬል ኮሮና ቫይረስ – 2019) ሲባል የሚያስከትለው በሽታም COVID-2019 (ኮቪድ-2019) የሚል ስያሜ ተሰጠው።

በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚኖር ቅርብ ግንኙነት እና ንክኪ እንዲሁም ታማሚው በሚስልበት ወቅት በአየር ላይ በሚለቀቁ ጠብታዎች (droplets) አማካኝነት የሚተላለፈውን ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ወደተለያዩ ሃገራት እንዳይዛመት ለመከላከል አልተቻለም። በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥም ኢትዮጵያን ጨምሮ 133 ሃገራትን ሲያዳርስ ከ138,000 በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ለ5000 ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። የዓለም የጤና ድርጅት በመጀመሪያ በዓለምአቀፍ የጤና ስጋት ደረጃ ያስቀመጠው በሽታም ወደ ዓለምአቀፍ ወረርሺኝነት (Pandemic) ተቀይሯል።

ከዓለማችን ህዝብ ከግማሹ በላይ የሚከታተለው እግርኳስም እንደማንኛውም የህይወት ክፍል የዚህ ወረርሺኝ ተፅዕኖ እንዲያርፍበት ሆኗል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በየስታዲየሙ እየተገኙ የሚከታተሏቸው ጨዋታዎችም ለቫይረሱ ስርጭት የተመቸ ሁኔታን ሊፈጥሩ የሚችሉ እንደመሆናቸው የየሃገራቱ የጤና ጥበቃ ተቋማትና ውሳኔ ሰጪ ሰዎችን ትኩረት መሳባቸው አልቀረም። ወረርሺኙ ከተነሳባት ቻይና ጀምሮ የተለያዩ ሃገራት ክለቦች፣ ሊጎች፣ የእግርኳስ ማህበሮች፣ ብሎም እስከ ዓለምአቀፉ የእግርኳስ ማህበር ፊፋ ድረስ ከጤና ተቋማቱ ጋር በመተባበር ስርጭቱን ለመከላከል እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።

የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ቻይና በየካቲት ወር ጀምሮ ታህሳስ ላይ የሚጠናቀቀውን የቻይና ሱፐርሊግ የሚጀመርበትን ቀን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝማለች። ሃገሪቱ የቫይረሱን ስርጭትና የአዳዲስ ተጠቂዎችን ቁጥር በተወሰነ መልኩ ለመቆጣጠር ብትችልም ውድድሩ ግን እስካሁን ድረስ አልተጀመረም። ከእግርኳስ ሊጉ በተጨማሪም በቻይና ሊደረጉ የታሰቡ የእስያ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ የሴቶች እግርኳስ የኦሎምፒክ ማጣሪያ፣ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የፒጂኤ የጎልፍ ውድድር፣ የፌድካፕ የቴኒስ ውድድር፣ የቻይና ግራንድ ፕሪ የሞተርስፖርት ውድድር እና የተለያዩ የቶክዮ ኦሎምፒክ የማጣርያ ውድድሮችን ጨምሮ በርካታ ስፖርታዊ ኩነቶች ተሰርዘዋል፣ ተሸጋግረዋል፣ ወይንም ወደ ሌላ አዘጋጅ ሃገር ተቀይረዋል። ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታም ባለፉት ሶስት ወራት ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች በቻይና እንዳይከናወኑ ተደርጓል።

የእግርኳስ ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ሃገራት በሚገኙባት አውሮፓም የእግርኳሱ ባለድርሻ አካላት የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል እና የእግርኳስ ካሌንደሩን ለመጠበቅ፣ ውድድሮች የሚያመነጩት ገቢም እንዳይነጥፍ በማድረግ ተፃራሪ ምርጫዎች ውስጥ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ቆይተዋል። የአውሮፓ እግርኳስ ማህበርም የቻምፒዮንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ ውድድሮች የሚጠናቀቁበትን ሂደት እና የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ዕጣፈንታን ለመወሰን አባል ሃገራቱን በመሰብሰብ በመወያየት ላይ ይገኛል። የአውሮፓ ዋንጫን ከማራዘም፣ የውድድሩን አዘገጃጀት እና ቅርፅ መቀየር፣ አልፎም የቻምፒዮንስ እና ዩሮፓ ሊግ ውድድሮችን እስከመሠረዝ ድረስ ያሉ እርምጃዎችም ሊወሰዱ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

ከአውሮፓ ሃገራት ውስጥ በወረርሺኙ ክፉኛ የተጠቃችው ጣሊያን የእግርኳስ ውድድሮቿ በዝግ ስታዲየም እንዲደረጉ የወሰነችው ቀደም ብላ ነበር። ከጣሊያን በመቀጠልም ፈረንሳይ ከ1000 ሰዎች በላይ የሚገኙባቸው ስፖርታዊ ኩነቶች በዝግ እንዲሆኑ ስታደርግ ስፔን፣ ቤልጂየም፣ ጀርመን እና ሌሎች ሃገራትም ይህንኑ ለመተግበር ወስነዋል። የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር እና ፕሪምየር ሊጉ ግን ውድድሮችን እንደቀድሞው ለማስኬድ በመወሰን መርሃግብሮችን ሲያስቀጥሉ ተስተውሏል። በነዚህ ሃገራት ክለቦች የሚጫወቱ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞች እና የክለብ አመራሮች በቫይረሱ መያዝ፣ የበርካታ ክለቦች አባላትም በከፊልም ሆነ በሙሉ በመለያ ክፍሎች (Isolation Rooms) እና በቤት ውስጥ ራስን በመለየት (Self Isolation) ላይ መሆናቸው ግን ሃገራቱ ሊጎቻቸውን በጊዜያዊነት ቢያንስ እስከ ሚያዝያ ወር ድረስ እንዲያቋርጡ አስገድዷቸዋል።

የሃኖቨር 96ቱ ተከላካይ ቲሞ ሁበርስ፣ የቼልሲው አማካይ ካለም ሃድሰን-ኦዶይ፣ የሳምፕዶሪያው አጥቂ ማኖሎ ጋቢያዲኒ፣ የጁቬንቱሱ ዳኔሌ ሩጋኒ፣ የአርሰናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ፣ የኦሊምፒያኮስ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ክለቦች ባለቤት ኢቫንጀሎስ ማሪናኪስ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ከተረጋገጡ የእግርኳስ ሰዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በሃገረ አሜሪካ የእግርኳስ ውድድሩ ሜጀር ሊግ ሶከር ለአንድ ወር ያህል እንዲቆም ሲደረግ ከቅርጫት ኳስ እና አሜሪካን ፉትቦል ጀምሮ የቴኒስ እና የጎልፍ ውድድሮች፣ የቦክስ ግጥሚያዎች፣ የሞተር ሬሲንግ፣ ቤዝቦል፣ የፈረስ ውድድር፣ የኮሌጅ ፉትቦል እና ሌሎች በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮች፤ ከዚህም አልፎ እንደ WWE ሬሲሊንግ ያሉ ስፖርታዊ የመዝናኛ ዝግጅቶች በከፊል እንዲቆሙ ሆኗል።

ዓለምአቀፍ ስፖርታዊ ዝግጅቶችን ስንመለከት ደግሞ የ2020ው የቶክዮ ኦሊምሊክ እስካሁን 701 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች እና 10 ከበሽታው ጋር የተያያዙ ሞቶች በተመዘገቡባት ጃፓን እንደመካሄዱ በርካታ አካላት ስጋታቸውን እየገለፁ ቢሆንም ዓለምአቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ግን ውድድሩን ቀድሞ በተቀመጠው መርሃግብር ለማድረግ እንደተዘጋጀ ገልጿል። ኮሚቴው በመግለጫው “የ2020ው ቶክዮ ኦሊምፒክ የመክፈቻ ስነስርዓት ሊደረግ ገና 19 ሳምንት እንደመቅረቱ እና በዓለምአቀፍ ደረጃም ውርሺኙን ለማቆም በርካታ አመርቂ ስራዎች እየተደረጉ በመሆናቸው ውድድሩን በተቀመተለት የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንደምንችል እንድናምን አድርጎናል፤” ብሏል።

በአውሮፓ የሚገኙ ክለቦች ባለፉት ሳምንታት በደጋፊ ፊትም ሆነ በዝግ ስታዲየም ውድድሮችን እያከናወኑ ሲቆዩ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ይከላከላል ብለው ያሰቧቸውን ልምዶች ሲተገብሩ ቆይተዋል። አብዛኛዎቹ ክለቦች ተጫዋቾቻቸው ከደጋፊዎች ጋር ፎቶ ለመነሳትም ሆነ ፊርማቸውን ማኖር እንዳይገናኙ የከለከሉ ሲሆን በርካታዎቹም ከእግርኳሳዊ ኩነቶች (ልምምዶች እና ጨዋታዎች) ውጪ ሌሎች የቡድኑ አባላትን ከህብረተሰቡ ጋር የሚያገናኙ ዝግጅቶችን እና የስታዲየም ጉብኝቶችን አግደዋል፤ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ሰራተኞች ውጪ ሌሎች ሰዎች በስታዲየሞች እና የልምምድ እና ቴክኒካል ስፍራዎች ላይ እንዳይገኙም አድርገዋል። እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ያሉ ውድድሮች ደግሞ ከጨዋታ በፊት የሚደረገውን የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች እጅ መጨባበጥ የከለከለ ሲሆን ተጫዋቾችን አጅበው ወደ ሜዳ የሚገቡ ህፃናቶች ልምድም ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ሆኗል። ክለቦችም የሊጉን መሪነት በመከተል በልምምድ ሜዳዎች እና በክለብ ቢሮዎች ዙሪያ እጅ መጨባበጥ እንዳይኖር አድርገዋል።

ስለ ኮቪድ-2019 ወረርሽኝ መረጃ የሚሰጡ ፖስተሮችን በስታዲየም በመለጠፍ፣ በስታዲየም ስክሪኖች ላይም ትምህርታዊ የሆኑ ምስሎች እንዲተላለፉ በማድረግ ተመልካቾች ስለ በሽታው እንዲያውቁ እና ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥረት ያደረጉ ክለቦችም ነበሩ። በስታዲየም እና የልምምድ ስፍራዎች የፀረ-ቫይረስ እና ፀረ-ባክቴሪያ ኬሚካል ርጭት ማከናወን እና የእጅ ማጠብያ አልኮሎችን በእነዚህ ቦታዎች በማስቀመጥ ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ማድረግ በሽታውን ለመከላከል በክለቦች የተወሰዱ እርምጃዎች ነበሩ። ክለቦቹ ማንም ደጋፊ እንደ ሳል፣ ትኩሳት፣ የጉሮሮ ህመም እና ትንፋሽ ማጠር አይነት ምልክቶችን የሚያሳይ ከሆነ ጨዋታዎችን ለመመልከት ወደ ስታዲየሞች እንዳይመጣ ሲማፀኑም ተስተውሏል።

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዳይመጡ ለማገድ እንቅስቃሴ እያደረገም እንደነበር ተሰምቷል። ይህም የሆነው እነዚህ አረጋውያን በበሽታው የመያዝ እና ከተያዙም በኋላ ወደ ከፍተኛ ህመም፣ አልፎም እስከ ሞት የመድረሳቸው ዕድል ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል አንፃር ከፍተኛ በመሆኑ ነው። በእንግሊዝ በተለይም ለአርሴናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ለቫይረሱ መጋለጥ ተጠያቂ ነው የተባሉትን ከጨዋታ በፊት እና በኋላ የሚደረጉ ፕሬስ ኮንፈረንሶችንም ላልተወሰነ ጊዜ ለማቆም በዕቅድ ደረጃ ተይዟል።

ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት በሃገራችን የመጀመሪያውን በላብራቶሪ የተረጋገጠ የኮቪድ-2019 ተጠቂ ይፋ አድርጓል። ይህ ታካሚው ከሳምንት በፊት ከቡርኪና ፋሶ ወደ ሃገራችን የገባ የ48 ዓመት ጃፓናዊ ዜጋ እንደሆነ እና በለይቶ ማከሚያ ማዕከልም በህክምና እየተረዳ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ጨምሮ አስታውቋል።

በሃገራችን የሚኖረው ትክክለኛ የቫይረሱ የስርጭት መጠን ምናልባትም በቀጣይ ሳምንታት ግልፅ እየሆነ የሚመጣ ይሆናል። የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ስጋት ላይ የሚጥል ከሆነም ህብረተሰቡን ከህመሙ ለመጠበቅ ሲባል በርካታ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ። በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ በሜዳ ተገኝቶ ይከታተላቸዋል ከሚባሉ ውድድሮች የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ሆነ በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙት ሊጎቻችን የእነዚህ እርምጃዎች አንድ አካል ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። ከላይ የገለፅናቸው የዓለማችን ክለቦች፣ ሊጎች እና የእግርኳስ ማህበራት በሽታውን ለመከላከል የወሰዷቸው እርምጃዎች በአመዛኙ በሃገራችን ተግባራዊ ለመሆን ቢችሉም ከነባራዊ ሁኔታችን አንፃር ከአቅም በላይ የሚሆኑ እንደሚኖሩም ግልፅ ነው።

በቂ መፀዳጃ ቤት እና እጅ መታጠቢያ እና ንፁህ የአየር ዝውውር እንኳን የሌላቸው የሃገራችን ስታዲየሞች ዋነኛ የቫይረሱ ስርጭት ማዕከሎች እንዳይሆኑ ቅድመ-ጥንቃቄዎችን ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በቂ የጤና መሰረተ ልማት እና ጠንካራ የፋይናንስ ክንድ ያላቸውን ሃገራት ተሞክሮ ከሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብም ጨዋታዎችን በዝግ ስታዲየም ከማድረግ አንስቶ እግርኳሳዊ ውድድሮችን እስከማቋረጥ ድረስ የተለያዩ አስፈላጊ እርምጃዎችን የምንወስድባቸው የራሳችን ልኬቶች (thresholds) ያስፈልጉናል። ክለቦች፣ አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጋራ ኩባንያ እና ፌዴሬሽኑም ከጤና ተቋማቶቻችን ጋር በመወያየት ሊከሰት ለሚችል ማንኛውም የጤና ስጋት ተገቢውን ውሳኔ እንዲያስተላልፉበት የሚረዳቸውን ቅድመ-ዝግጅት ቢያደርጉ እንመክራለን።