ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሐሙስ እና ዓርብ መከናከናቸው ይታወሳል። እጅግ የተቀዛቀዙ ጨዋታዎች በተስተናገዱበት በዚህ ሳምንት በአንፃራዊነት ጥሩ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉትን 11 ተጫዋቾችን በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል። 

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት ነጥብ መነሻነት ነው። 

* ምርጫው ተጫዋቾች በዕለቱ በተሰለፉበት ጨዋታ ላይ ባሳዩት ብቃት ላይ የተመረኮዘ ነው።

* ፎርሜሽኖች እና የተጫዋቾች ቦታዎች ምርጫውን ባማከለ መልኩ በየጊዜው ሊቀያየሩ ይችላሉ። 

አሰላለፍ ፡ 4-2-3-1


ሀሪስተን ሄሱ (ባህር ዳር ከተማ)

በዚህ ሳምንት ምርጥ ጨዋታ ካሳለፉ ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ ነው። ቡድኑ ባህር ዳር ከሜዳው ውጭ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ በርካታ ጎል የሚሆኑ ያለቀላቸው ሙከራዎች አድኗል። ግብጠባቂው በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባ የመጀመርያው ነው።


ወንድማገኝ ማርቆስ (ጅማ አባ ጅፋር)

ሁለገቡ ተጫዋች ጅማ አባ ጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ላይ ወንድማገኝ በግሉ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። በመልሶ ማጥቃት ሲጫወት በነበረው ቡድን ውስጥ የቡናን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ የተሳካ ቀን ያሳለፈው ተጫዋቹ ለማጥቃት ሽግግሩም የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። ወንድማገኝ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ሲካተት የመጀመርያው ነው።


አዲስ ተስፋዬ (ሰበታ ከተማ)

ጠንካራው ተከላካይ አዲስ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ይጣሉ የነበሩ ረጃጅም ኳሶችን በማቋረጥም ሆነ ወደ መሐል ከተጠጋው የሰበታ የተከላካይ መስመር ጀርባ ይጣሉ የነበሩ ኳሶችን በፍጥነት በማገገም ያቋረጥበት የነበረው መንገድ አስደናቂ ነበር። በተጨማሪም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ኋላ ባፈገፈገው የቡድን የተከላካይ መስመርን ከአንተነህ ጋር በመናበብ ይመራበት የነበረው መንገድ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በሳምንቱ ምርጥ እንዲካተት አስችሎታል።


መናፍ ዐወል (አዳማ ከተማ)

እጅግ ፈጣን አጥቂዎች ባለቤት የሆኑት የወልቂጤ ከተማዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ውስጥ የመናፍ ዐወል ድርሻ እጅግ ከፍ ያለ ነበር። በተለይም አህመድ ሁሴንን የተቆጣጠረበት መንገድ አስደናቂ ነበር። ተጫዋቹ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የነበረው የማሸነፍ ንፃሬ እና ስኬታማ የነበሩት ታክሎቹ ፍጥነት ላይ የተመረኮዘውን የወልቂጤ ከተማዎች እንቅስቃሴ መና ማስቀረት ችሏል። በዚህሕም ለሁለተኛ ጊዜ በሳምንቱ ምርጥ ተካቷል።


ሄኖክ መርሹ (ወልዋሎ)

ወጣቱ ተከላካይ ወልዋሎ ከሜዳው ውጪ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ ጥሩ እንቅስቃሴ ከታደረጉ ተጫዋቾች አንዱ ነው። የወላይታ ድቻን ፈጣን የመስመር አጨዋወት በመቆጣጠር ረገድ የተሳካ እንቅስቃሴ ያደረገው ሄኖክ ወደፊት ለማጥቃት የሚያደርገው እንቅስቃሴም መልካም የሚባል ነበር። በዚህም ለመጀመርያ ጊዜ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት ችሏል።


ዳዊት እስጢፋኖስ (ሰበታ ከተማ)

በርከት ያሉ ሳምንታትን በጉዳት ሳቢያ ቡድኑን ማገልገል ያልቻለው ተጫዋቹ በሁለተኛው ዙርን ግን ከፍ ባለ ብቃት በመጀመር ላይ ይገኛል። ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት ግሩም የቅጣት ምት ግቦችን በማስቆጠር ለቡድኑ ወሳኝ ሚናን የተወጣው ዳዊት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አስቻለው ግርማ ላስቆጠራት የማሸነፊያ ግብን በግሩም ሁኔታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በተጨማሪም ኳስን ከኋላ ያደራጅ እና ያሰራጭበት የነበረው መንገድ አስገራሚ ነበር። በዚህም ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።


ይሁን እንዳሻው (ሀዲያ ሆሳዕና)

ሀዋሳ ከሆሳዕና ነጥብ የተጋሩበት ጨዋታ ምንም እንኳን እጅግ ደካማ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም ይህ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በግሉ ያደረገው ጥረት ግን አመርቂ ነበር፡፡ ወደ ማጥቃት ወረዳ የሚላኩ ኳሶች መነሻ የነበረው ይሁን አፈወርቅ ኃይሉ ላስቆጠራት ግብም ከማዕዘን በማሻማቱ ረገድ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ያደረገው እንቅስቃሴም በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲካተት አስችሎታል።


ዮናስ ገረመው (መቐለ 70 እንደርታ)

በዚህ የውድድር ዓመት በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች እንደተፈለገው መንቀሳቀስ ያልቻለው ዮናስ ገረመው በዚህ ሳምንት ቡድኑ መቐለ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ ጥሩ ተንቀሳቅሶ ለበርካታ የግብ ዕድሎች መፈጠር ቀጥተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። ሁለቱም የቡድኑ አጥቂዎች ለሞከሯቸው ሙከራዎች በርካታ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለው አማካዩ ምንም እንኳ ጥረቱ ፍሬ ባያፈራም በግሉ ጥሩ ቀን አሳልፏል። በዚህም የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ተካቷል።


ያስር ሙገርዋ (ስሑል ሽረ)

በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳው ተመልሶ የሁለተኛውን ዙር የሜዳው ላይ ጨዋታን በድል ለተወጣው ስሑል ሽረ የዚህ ዩጋንዳዊ አማካይ አስተዋጽኦ እጅጉን ከፍ ያለ ነበር፡፡ የመሐል ሜዳውን በሚገባ ተቆጣጥሮ የማጥቃት ሚዛኑን አስጠብቆ ከመውጣት አንስቶ ለቡድኑ ተነሳሽነትን ሲፈጥር የታየው ተጫዋቹ የመጀመሪያዋን የቡድኑን ግብ ከመረብ ከማሳረፉ በዘለለ ለሁለተኛው ግብ በማመቻቸትም ደረንቅ ቀን አሳልፏል። ለመጀመርያ ጊዜም በሳምንቱ ምርጥ ተካቷል።


ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)

ፋሲል ወደ ድሬዳዋ አምርቶ ያለ ጎል አቻ በተለያየበት ጨዋታ ቡድኑ እምብዛም አመርቂ ነገር ባያሳይም ሱራፌል መነሻውን ከመስመር እና ከመሐል በማድረግ የፋሲልን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማሳመር በግሉ ሲታትር ታይቷል። ቡድኑ የፈጠራቸው ጥቂት አጋጣሚዎች መነሻም ነበር። በዚህም በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ሊካተት ችሏል።


አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

ቡና ወደ ጅማ አምርቶ አቻ በተለያየበት ጨዋታ አቡበከር እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የፊት መስመሩን በትጋት ሲመራ የዋለ ሲሆን ጥሩ ጥሩ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር በመጨረሻ ደቂቃም ቡድኑን ሦስት ነጥብ ለማስገኘት ያቃረበውን ጎል ማስቆጠር ችሎ የነበረ ቢሆንም በቅፅበት ጎል አስተናግደው አቻ ተለያይተዋል። በዚህም ወጣቱ አጥቂ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ሲገባ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሆኗል።


ተጠባባቂዎች

ፋሲል ገ/ሚካኤል (ሰበታ ከተማ)
ሰለሞን ወዴሳ (ባህር ዳር ከተማ)
ዐወት ገብረሚካኤል (ስሑል ሽረ)
ኤልያስ ማሞ (ድሬዳዋ ከተማ)
ኤርሚያስ ኃይሉ (ጅማ አባ ጅፋር)
ሀብታሙ ገዛኸኝ (ሲዳማ ቡና)
መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ)


©ሶከር ኢትዮጵያ