የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን በስሩ ያሉትን ውድድሮች ዘንድሮ እንደማያከናውን ገለፀ

በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስር የሚደረጉ 5 የመዲናይቱ ውድድሮች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ቀሪዎቹ መርሃ ግብሮች ዘንድሮ እንደማያከናውኑ ተገልጿል።

ይህ ፌደሬሽን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) በዓመቱ መጀመሪያ ከማድረጉ ጎን ለጎን ዓመታዊ ውድድሮችን በየጊዜው እያከናወነ ይገኛል። በዚህም ፌደሬሽኑ በከፍተኛ የወንዶች እና ሴቶች ዲቪዚዮን፣ በአንደኛ ዲቪዚዮን፣ ከ17 ዓመት በታች ኤም አራ አይ ያለው እንዲሁም የሌለው፣ ከ15 ዓመት በታች እና ከ13 ዓመት በታች እየተደረጉ የነበሩ ውድድሮቹን በወረርሽኙ እና በሃገሪቱ በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነት ማገዱ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎ ትላንት ስለ ውድድሩ ቀጣይ እጣ ፈንታ ውይይት ያደረጉት የፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት ውድድሩ በዚህ ዓመት እንደማይመለስ ተነጋግረው ውሳኔ አሳልፈዋል። ሶከር ኢትዮጵያ ከስራ አስፈፃሚዎቹ ባገኘው መረጃ ውድድሮቹ ዘንድሮ ባይደረጉም ቀጣይ ዓመት ላይ በሚኖረው የወረርሽኙ ሁኔታ መነሻነት ቀጣይ ውሳኔዎች እንደሚሰጡ ተገልጿል። በዚህም የውድድሮቹ አሸናፊዎች በቀጣይ ከወረርሽኙ ጋር በሚመጡ የሃገር ሁኔታዎች ታሳቢነት ስራ አስፈፃሚዎች ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፉ ተነግሯል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ