ተሰፋኛው አጥቂ ታምራት ስላስ

በወላይታ ድቻ በታዳጊ ቡድን ውስጥ የነበረው አቅም ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን እንዲያድግ አስችሎታል፤ ወደፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው አጥቂዎች አንዱ የሆነው ታምራት ስላስ የዛሬ ተስፈኛ አምዳችን ላይ ይዘን ቀርበናል።

ለ2008 ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሰልጣኞች አባላት ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ በመጓዝ ሁለት ተጫዋቾችን መልምሎ ለመውሰድ 900 ታዳጊዎች ለፈተና እንዲቀርቡ አድርጎ በመጨረሻ ምርጫ ይህ ተስፈኛ አጥቂ ታምራት ተመርጦ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ለአንድ ዓመት እንዲጫወት ሆኗል። ታምራት ተወልዶ ያደገው በወላይታ ሶዶ ከተማ ነው። በንግድ ባንክ በነበረው ቆይታ ጥሩ ጊዜ ቢያሳልፍም ልጅ በመሆኑ ከቤተሰብ ርቆ ለመኖር በመቸገሩ ኮንትራት እያለው ከክለቡ ጋር ተስማምቶ በ2009 ለወላይታ ድቻ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሐ ጋር በመሆን የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት ችሏል።

በ2010-11 ለወላይታ ድቻ ከ20 ዓመት በታች ቡድንን የተቀላቀለው ይህ ተስፈኛ አጥቂ ባቱ ከተማ ላይ በተካሄደውም ሆነ በዓምና አዳማ ከተማ ላይ በተደረገው የማጠቃለያ ውድድር ወላይታ ድቻ ለተከታታይ ሁለት ዓመት ባለ ድል የሆነ የመጀመርያው ቡድን ሲሆን የዚህ ተስፈኛ አጥቂ ሚና ከፍተኛ ነበር። በ2011 ላይ በግሉ የውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። ፈጣን፣ ጉልበት ያለው ይህ ታዳጊ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በነበረው ቆይታም ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ዋንጫ ማንሳትም ችሎ እንደነበረ ይታወሳል።

በዘንድሮ ዓመት ወደ ዋናው ቡድን በማደግ በተለይ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ወላይታ ድቻ በቆየበት ወራት ውስጥ ይህ ተስፈኛ አጥቂ ተቀይሮ በመግባት በስድስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በመጫወት ተሰፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። በመቐለ በተጀረገው የትግራይ ዋንጫ ላይ ከደደቢት ጋር በነበረው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ተቀይሮ ባገባው ጎል ወላይታ ድቻ ለፍፃሜ ጨዋታ ከሲዳማ ቡና ጋር እንዲጫወት ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትውታ ነው። ይህ አጥቂ ዓምና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ እየተመራ ዩጋንዳ ላይ በተካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ውድድር ላይ በሦስቱም የምድብ ጨዋታ ላይ የመጨመርያ ተሰላፊ በመሆን መጫወት ችሏል።

” በእግርኳሱ ትልቅ ደረጃ መድረስ እፈልጋለው። የጌታነህ ከበደ በጣም አድናቂ ነኝ። የእሱን ጨዋታዎች በፊልም እያየሁ ነው ያደኩት። በሁለቱም የእድሜ እርከን በቆየሁበት ዓመታት ብዙ ልምዶችን አግኝቻለው። በታዳጊዎች ላይ ከፍተኛ እምነት ያለው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ በስድስት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ላይ ሠላሳ፣ አርባም ደቂቃ ቀይሮ እያስገባኝ ጥሩ ያጫውተኝ ነበር። እኔን በደንብ እየተረዳኝ እና በእኔ እንቅስቃሴ ደስተኛ ሆኖ ወደ ቋሚ አስተላለፍ ውስጥ ሁሉ ሊያስገባኝ ይፈልግ ነበር። ሆኖም እርሱ ሳይቆይ በመሄዱ ለእኛ ታዳጊዎች ይሰጠን የነበረውን እድል አጥተናል። ይህ ትንሽ አሳስቦኝ ነበር። አሁን ያለንበት በተለይ በኮሮና ምክንያት የውድድሩ መቋረጥ ለእኔ ጠቅሞኛል ነው የምለው። ያው ሶዶ ከተማ ዳገታማ በመሆኗ እየሮጥኩ እንዲሁም በጂም እየሰራው እራሴን በሚገባ እያዘጋጀው ነው። ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች የመሆን ሀሳቤን ጠንክሬ እገፋበታለው።”

ይህ ታዳጊ ወጣት ትኩረት ተሰጥቶት ራሱን እንዲያሳድግ እድሎች የሚመቻቹለት ከሆነ ነገ ትልቅ ተጫዋች የመሆን አቅም እንዳለው ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ዓመታት መመልከት ችለናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ