አሸናፊ ግርማ በኢትዮጵያ ቡና አብረውት የተጫወቱ ምርጥ 11 ምርጫ

የቀድሞው ድንቅ አማካይ አሸናፊ ግርማ በኢትዮጵያ ቡና ከ1992 -1998 በቆየባቸው የወድድር ዘመናት አብረውት ከተጫወቱ ተጫዋቾች ራሱን ጨምሮ ምርጥ የሚላቸውን እንዲህ አጋርቶናል።

በዩቲዩብ ለመመልከት ይህን ይጫኑ ፡ You Tube

አሰላለፍ : 3-4-3

ግብጠባቂ – አሊ ረዲ

ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩት ምርጥ ብቃት ካላቸው ግብጠባቂዎች ተርታ ይመደባል። አሊ የሜዳ ላይ ብቃቱ የአየር እና የመሬት ኳስ አያያዙ፣ በእግርም ሲጫወት እንዲሁም ታይሚንግ አጠባበቁ እና አንድ ለአንድ የሚያድናቸው ኳሶች በአጠቃላይ አንድ ግብ ጠባቂ ሊያሟላ የሚገባውን ነገር ሁሉ አሟልቶ ያያዘነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ባጋጠመው የጤና ችግር ምክንያት ከሜዳ ራቀ እንጂ እስከ አሁን ዘመን ድረስ በብቃት ሲጫወት የምንመለከተው ግብ ጠባቂ ይሆን ነበር።

ተከላካዮች

አንዳርጋቸው ሰለሞን

አንድ ተከላካይ ሊያሟላቸው የሚገባውን ነገሮች በሚገባ ያሟላ እግር ኳስ ተጫዋች ነው። ኳስ መንጠቅ ባለበት ሰዓት ይነጥቃል። መጫወት ባለበት ሰዓት ይጫወታል። ከኋላ ተነስቶ ወደ ፊት እየሄደ ጎል ያገባል። የአየር ኳስም በጭንቅላት ይገጫል። ኳስ ሲጫወት ለአማካይ ይመቻል፤ ቀለል አድርጎ ይጫወታል። እልኸኛ እና ለማልያ ሟች የሆነ የመስመር ተከላካይ ነው።

መሐመድ ኢብራሂም (ኪንግ)

የአየር ኳስ በጭንቅላት ሲገጭ ጥሩ ነው። ኳስ ሲነጥቅ እና ታክል ሲወርድ በብቃት ነው። ኳስም አውርዶ ሲጫወት ጥሩ ነው። ከቆሙ ኳሶች ቅጣት ምት ጎል የማስቆጠር ልዩ አቅም አለው። በቀኝም በግራ እግሩም መጫወት ይችላል። ሜዳ ውስጥ ሁሉ ነገሩን የሚሰጥ ተጫዋች ነው።

ሳሙኤል ደምሴ (ኩኩሻ)

በጣም ጎበዝ፣ ብልጥ፣ ብልህ እና ጉልበት ሳይጠቀሙ በአይምሮቸው ከሚጫወቱ የመሐል ተከላካዮች ግንባር ቀደሙ ነው። በጣም ፈጣን ነው። ከመስመር ተከላካዮች የሚያመልጡ ኳሶችን በማቋረጥ፤ በቀላሉ አጥቂዎችን በመንጠቅ የተዋጣለት ነው። ኳስ ሲጫወት አቅልሎ ነው። ለአማካይ ተጫዋቾች ኳስ ሲያቀብል ይመቻል። በአጠቃላይ ስለእርሱ ብዙ ማለት የሚቻልለት ምርጥ ተከላካይ ነው።

አማካዮች

አሸናፊ ግርማ

ዕድሉ ደረጄ

ኳስ ነጣቂ፣ ደፋር እና አልሸነፍ ባይነት ካላቸው የመሐል ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። ኳስ ይነጥቃል፣ የአየር ኳስ በጭንቅላት ይገጫል። ታክል ይወርዳል፣ ረጅም፣ አጭርም ኳስ ይጫወታል። በሜዳ ላይ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርግ በሁለቱም እግሩ መጠቀም የሚችል ኳሶችን በቀላሉ የሚነጥቅ አሪፍ ተጫዋች ነው።

ካሳዬ አራጌ

ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ምርጥ የመሀል ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደም ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ምክንያቱም ሜዳ ላይ ያለውን ኃላፊነት ከጎንህ እየተጫወተ ይወስድልሃል። በተለይ አዲስ ተጫዋች ስትሆን አትቸገርም። በሁለቱም እግሩ ይጫወታል። ቡድን ይመራል፣ አጭርም ረጅምም ኳስ ይጫወታል። ካሳዬ ሲሸፍን ይገርማል፤ ኳስ ከሸፈነ ማንም አይነጥቀውም።

ካሊድ መሐመድ

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ግራኝ እግርኳስ ተጫዋቾች ውስጥ ጥሩ ችሎታና ብቃት ያለው ተጫዋች ነው። ኳስ ሲጫወት ጎበዝ ነው። ከቆመ ኳስ ጎል ያገባል። እንዲሁም ከመስመር እየተነሳ የሚያስቆጥራቸው ጎሎች ብዙ ናቸው። አጨራረሱ የተለየ ነው። ለአጥቂዎችም ያለቀላቸው ኳሶችን አመቻችቶ ያቀብላል። አንድ ለአንድ አብዶ ሰርቶ ያልፋል። ጥሩ ችሎታ እና ብቃት የነበረው ተጫዋች ነው። ያለ እድሜው በጉዳት ከሜዳ መራቁ ያሳዝነኛል።

አጥቂዎች

አሰግድ ተስፋዬ

በጣም ጎበዝ አጥቂ ነው። በኔ እይታ ሙሉ እግርኳስ ተጫዋች ነው። አንድ ለአንድ አብዶ አድርጎ ተከላካይ አልፎ ጎል ያገባል። ጨረቃ ውስጥ ጨራሽ አጥቂ ነው። አንድ ሁለት ይጫወታል፣ የቆመ ኳስ ጎል ያገባል፣ ይሸፍናል፣ አሲስት ያደርጋል፣ የሰጠኸውን ኳስ ባግባቡ ይጠቀማል። ከአሰግድ በአሰልጣኝነት ህይወቱ ወደ ፊት ብዙ እንጠብቅ ነበር፤ አልሆነም። እግዚአብሔር ነፍሱን በገነት ያኑረው።

ታፈሰ ተስፋዬ

ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣን እና ጉልበተኛ ከሚባሉት ምርጥ አጥቂዎች አንዱና ዋናው ነው። የሚመታው ኳስ በጣም ጠንካራ ነው። አንድ ሁለት ይጫወታል፣ ያቀበልከውን ኳስ በአግባቡ ይጠቀምበታል።

ዮርዳኖስ ዓባይ

ብልጥ እና ጎበዝ አጥቂ ነው። ኳስ ይችላል፤ አንድ ለአንድ ሲገናኝ አብዶ ሰርቶ አልፎ ጎል ያስቆጥራል። አሲስት ያደርጋል፣ ሲሸፍን ጎበዝ ነው። የተዋጣለት ጨራሽ አጥቂ ነው። የምትሰጠውን ኳስ በአግባቡ ይጠቀምበታል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ