“ጋርዚያቶን የማረከችው እንስት…” የሚካኤል አብርሀ ትውስታ

ከዚህ ቀደም ብለን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያገለገለው እና በክለብ ደረጃ ጉና ንግድ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሐራር ቢራ እና ሜታ ቢራ የተጫወተው የአጥቂ አማካዩ እና ጨዋታ አዋቂው ሚካኤል አብርሀ የወጣቶች አፍሪካ ዋንጫ ትውስታውን ወደ እናንተ ማቅረባችን ይታወሳል አሁን ደግሞ ከውድድሩ በፊት በኬንያ ያጋጠመውን አቅርበንላችኃል።

ኢትዮጵያ ካዘጋጀችው የወጣቶች አፍሪካ ዋንጫ በፊት በኬንያ ጥሩ የዝግጅት ወቅት እንደነበራቸው የሚገልፀው ሚካኤል አብርሀ ብሔራዊ ቡድኑ በወቅቱ በናይሮቢ ከምትኖረው ኢትዮጵያዊ የብሔራዊ ቡድን ደጋፊ ጋር በተያያዘ የነበሩትን ትውስታዎች ይናገራል።

” ዲዬጎ ጋርዝያቶ ይወደኝ ነበር። ኬንያ ስንሄድ መቐለ ላይ የማውቃት አንዲት ጓደኛየ ነበረች፤ የብሔራዊ ቡድናችን ቀንደኛ ደጋፊ ነበረች። እኔ መቐለ እያለው ነው የማውቃት፤ የመቐለ ልጅ ነች። በሥራ ምክንያት ነበር ወደ ናይሮቢ የሄደችው። ዋና አሰልጣኛችን ጋርዝያቶም ልጅቷን በጣም ወዷታል። እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችም ልጅቷን ይወዷት ነበር። በጣም ቆንጆ ነበረች፤ በዛ ላይ አለባበሷ በሰዓቱ ማራኪ ነበር። ሁሉም ያልተረዱት ነገር ባለትዳር እንደሆነችና ባለቤቷም የቡድናችን የቅርብ አጋዥ እንደነበረ ነው። ሁሉም ባለቤቷ መሆኑን አያውቁም ነበር። ኋላ ላይ ጋርዝያቶ እኔ መቐለ እያለሁ እንደማውቃት አወቀ… ቆይቶም ምን እንዳሰበ አላውቅም በጣም ተናደደ። ደስ እንዳላለውም ምክትል አሰልጣኙ ዚያድ አማካኝነት ነገረኝ። እኔ ግን ትዳር እንዳላት አስረግጬ ነገርኩት።

“ከዛም በነጋታው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ነበረን። ከጨዋታ በፊት ጋርዝያቶ አሰላለፍ እየተናገረ እኔ ስም ላይ ሲደርስ በፈረንሳይኛ ስሜታዊ ሆኖ እየተናደደ ብዙ ነገር ተናገረ። እኔም ግራ ገባኝና ስብሰባው ሲያልቅ በፍጥነት ወደ ምክትል አሰልጣኙ ዚያድ በመሄድ ስለተናገረው ነገር ጠየቅኩት። እሱም ‘ዛሬ የሆነ ተዓምር መፍጠር አለብህ ጋርዚያቶ ተናዶብሀል’ አለኝ በአጭሩ። እኔም ብዙ ነገር እያሰብኩ ወደ ጨዋታ አመራሁ፤ ያለኝን አውጥቼ ለመጫወትም ወስኜ ገባሁ።

” ጨዋታው ተጀመረ፤ በመጀመርያው አጋማሽም ሦስት ግቦች አስቆጠርኩ። ሆኖም በእረፍት ቀይሮ አስወጣኝ። በናይሮቢ ባደረግናቸው ሁለት ጨዋታዎች በጣም ምርጥ ነበርን፤ የቡድን መንፈሳችን አጠቃላይ የቡድናችን አቋም ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ከጨዋታው ከአንድ ቀን በኃላ ደግሞ አንድ የኬንያ ጋዜጣ የፊት ገፁ ላይ ‘ The danger man Mikael Abrha ‘ ብሎ ስለ ጨዋታው ብዙ ነገር ፅፏል። በዛን ወቅት በሕይወቴ ምርጥ የብቃት ጣርያ ላይ የነበርኩበት ወቅት ነበር።

” ከኬንያ ልንመለስ አካባቢ ደግሞ ጋርዚያቶ የወደዳት ልጅ የሚያግዘን ታታሪ ልጅ ሚስት መሆኗን ሲያውቅ ‘ሁሉም ነገር ትቼዋለው’ አለን። እንደውም መጨረሻ ላይ ከልጅቷ ጋር ፎቶ ተነስቶ ነበር የተለያየው። የኬንያ ቆይታችንም በተሳካ ሁኔታ አጠናቀቅን። እዛ የነበረኝ ትውስታ ይሄን ይመስላል። ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ