የሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች የደመወዝ ቅሬታ እና የክለቡ ምላሽ

ከሁለት እስከ አምስት ወራት ድረስ ወርሀዊ የደመወዝ ክፍያን ሳይፈፅም የቆየው ሀዲያ ሆሳዕና እስከ ቀጣይ ሳምንት የደሞዝ ክፍያ እንደሚያጠናቅቅ አስታውቋል፡፡

በሀገራችን በኮሮና ስጋት የተነሳ ከሁለት ወራት በፊት ቀሪ የሊግ የእግር ኳስ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸውን ይታወሳል፡፡ ይሁንና ፌድሬሽኑ ውድድሮቹን ይሰርዛቸው እንጂ ክለቦች በገቡት ውል መሠረት ለተጫዋቾቻቸው ክፍያን በአግባቡ መፈፀም አለባቸው ቢልም በርከት ያሉ ክለቦች ግን ተፈፃሚ ማድረግ ባለመቻላቸው ከተጫዋቾቹ ዘንድ ቅሬታ በተለያየ መልኩ ይደመጣል፡፡ ከእነኚህ ክለቦች መካከል ሀዲያ ሆሳዕና አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ “ከሁለት እስከ አምስት ወራት ድረስ ደመወዝ ክለቡ ሊከፍለን አልቻለም። በተደጋጋሚ ስንጠይቃቸውም የካሽ እጥረት አለ በማለት እያጉላሉን ነው። በስልክም ሆነ በተለያየ መልኩ አቤት ብንልም መልስ የሚሰጠን አጣን።” በማለት ተጫዋቾቹ ቅሬታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡

ችግሮቻቸው እየገፋ የመጣው የክለቡ ተጫዋቾች ወደ ሀዲያ ዞን አስተዳደር በማምራት ለዞኑ አስተዳደሪ እና የዞኑ ምክትል አስተዳደር በተጨማሪነትም ክለቡን በላይነት ከሚመሩት አካላት ጋር በአካል በመገናኘት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ የክለቡ አመራሮችም የዘገየበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ ኃላፊዎቹ “የካሽ እጥረት ስለገጠመን የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ደግሞ የኮሮና ወርሺኝም ስለተከሰተ ትኩረታችንን ወደዛ አድርገን ስለነበረ የተፈጠረ ችግር ነው። አሁን ግን ሙሉ በሙሉ እንቀርፍላችዋለን።” በማለት ለተጫዋቾቹ መልስን ሰጥተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ሀሳብ ለስከር ኢትዮጵያ እንዲሰጡ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ “የደመወዛቸው ጉዳይ ተፈቷል። ትላንት ተጫዋቾቹ ቢሮ ሄደው መልስ ተሰጥቷቸዋል። በጣም ሲያስቸግረኝ የነበረ የደመወዝ ጥያቄ ነበር፤ አሁን ግን ጨርሰናል፤ ብር ተመድቦልናል። ሰኞ እለት ግማሹ ብር ይገባላቸዋል። ከሳምንት በኃላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ እናጠናቅቃለን።” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ይህ የደመወዝ ጥያቄ በፕሪምየር ሊጉ ባሉ ክለቦች ላይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን ከሴቶች ፕሪምየር ሊግ እስከ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከከፍተኛ ሊግ እስከ አንደኛ ሊግ ባሉትም ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበበት ያለ ጉዳይ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በትናንትናው ዕለት ክለቦች ተገቢውን ክፍያ እንዲፈፅሙ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ