ካፍ አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባደረገው ስብሰባ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ፣ የውድድር ቀናት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

መጋቢት ወር ላይ ሊካሄድ የነበረውና በኮሮና ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገረው ቻን 2020 መቼ እንደሚደረግ ውሳኔ ተሰጥቶበታል። በዚህም ከጃንዋሪ 26 – ፌብሩዋሪ 27 በካሜሩን የሚከናወን ይሆናል። የዚህ ውድድር ቀን መሸጋሸግን ተከትሎ በአልጄሪያ የሚካሄደው የቻን 2022 ወደ 2023 ተሸጋግሯል።

ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ የነበረው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ መቼ እንደሚካሄድ ካፍ ያሳወቀ ሲሆን ጁላይ 2022 ላይ የሚደረግ ይሆናል።

ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማርች 2020 እንዲካሄድ መርሐ ግብር የወጣለት ሲሆን ያልተጠናቀቀው የ2019/20 ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ እና ፍፃሜ ጨዋታዎች ጥቅምት ወር ላይ እንዲካሄዱ ተወስኗል። የአዲሱ የውድድር ዘመን ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ ዙር ጨዋታዎች ደግሞ በኅዳር ወር ይደረጋሉ።

ከዚህ ቀደም በዘገባችን እንደገለፅነው የካፍ ዓመታዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ቀኑም ዲሴምበር 11 / 2020 ሆኗል።

በ2021 እንደሚጀመር የሚጠበቀው የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ መመርያ ወጥቶለታል። የመጀመርያው ውድድር በየዞኑ በሚደረጉ የማጣርያ ጨዋታዎች የሚያልፉ ስምንት ቡድኖችን የሚያሳትፍ ሲሆን ከየዞኑ አንድ አንድ አላፊ ክለብ ይኖራል። ከሚያዘጋጀው ሀገር እና ዞንም ተጨማሪ ክለቦች ይሳተፋሉ። ከመጀመርያው ውድድር በኋላ ደግሞ ከአሸናፊው ክለብ ሀገር አንድ ተጨማሪ ተሳታፊ ይኖራል። ውድድሩ በአንድ ሀገር ላይ የሚደረግ ሲሆን በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ የሚከናወን ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!