የሴቶች ገፅ | “አሁን በጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለሁ”

ከ8 ወራት በፊት የጉልበቷ የፊተኛው ማጠናከሪያ ጅማት ላይ (የACL) ጉዳት አጋጥሟት ለህክምና እርዳታ ሲጠየቅላት የነረችው ቤዛ ታደሰ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አጫውታናለች።

በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ቤዛ በታዳጊነቷ እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ህልም እንዳልነበራት ትናገራለች። ይልቁንም ፍጥነቷን ያውቁ የነበሩ የአካባቢዋ ሰዎች ሯጭ እንድትሆን የሚሰጧትን ምክር ተቀብላ በአትሌቲክሱ ዓለም ብቅ ለማለት ትሻ ነበር። ነገርግን ሙጂድ በተባለ የሰፈሯ ልጅ የተለየ ምክር ወደ እግርኳሱ እንድትገባ እና ሙከራ እንድታረግ ሆነ። ከዛም ተጫዋቿ ጥሩ የሙከራ ጊዜን በማሳለፍ በወረዳ፣ በዞን እና በከተማ በመቀጠልም ደግሞ በክልል ደረጃ በመጫወት ካሳለፈች በኋላ ወደ ተሻለ ደረጃ ተሸጋግራ የመጫወትን እድል አግኝታለች። በተለይ በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ክልሏን ወክላ ስትጫወት ባሳየችው አቋም የብዙ አሠልጣኞች ዐይን ውስጥ ገባች። በውድድሩ ላይም ምልመላ ሲያከናውን የነበረው የጊዜው የደደቢት ክለብ አሠልጣኝ ፍሬው ተጫዋቿን በማግባባት ወደ አዲስ አበባ መጥታ የእግርኳሰ ህይወቷን በክለብ እንድትገፋ አደረገ። በደደቢት ቤትም ለአንድ ዓመት ከግማሽ ቆይታን ካደረገች በኋላ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ፊርማዋን አኑሯ ተጫውታለች። በዚህ ክለብም አንድ ዓመት ግልጋሎት ከሰጠች በኋላ ወደ ጌዲዮ ዲላ ተጉዛ በሊጉ መጫወት ቀጥላለች።

በደደቢት የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ቆይታዋን ስታደርግ በአሠልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ጥሪ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን እንድታገለግል የሆነችው ተጫዋቿ ዓምና ጌዲዮ ዲላ እያለች አሰቃቂ ጉዳት በማስተናገድ ከእግርኳሱ ተገላ ቆይታለች። ሶከር ኢትዮጵያም ስለጉዳቷ እና አሁን ስላለችበት ሁኔታ ጥያቄ አቅርቦላት ተከታዩን ምላሽ ሰጥታናለች።

“ይህ ጉዳት የደረሰብኝ ልምምድ ላይ ነው። ለ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመዘጋጀት የቅድመ ውድድር ጊዜ ላይ እያለሁ ነው የተጎዳሁት። ውድድሩ ሊጀመር 2 ወራት ሲቀሩት ነበር ቡድናችን ዝግጅት የጀመረው። በመጀመሪያው ወር ትንሽ የህመም ስሜት ቢሰማኝም ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። እርግጥ ብዙ ቦታ ሄጄ ታሽቼው ነበር። ግን ከመታሸት ውጪ ምንም እንክብካቤ ሳላደርግለት ልምምዴን እሰራ ነበር። የቅድመ ውድድር ዝግጅታችን መገባደጃ አካባቢ ላይ ግን ሜዳ ላይ ልምምድ እየሰራሁ ኳስ ወደ ጎል ስመታ እግሬ ታጥፎ ቀረ።

“ከዛም የተሻለ ህክምና ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። አዲስ አበባም ይሳቅ ሽፈራውን አግኝቼ እንዲያየኝ አደረኩ። እሱም ራጅ እንድነሳ አዞኝ የራጁ ውጤት ሲታይ የጉልበት ጅማት መበጠሱ ታወቀ። ዶክተሮቹም በቀጥታ ቀዶ ጥገና እንድሰራ አዘዙኝ።”

ጉዳቱ የደረሰባትን አጋጣሚ እና ከዛ በኋላ ወደ ህክምና ማዕከል አምርታ የተነገራትን ነገር ያጫወተችን ተጫዋቿ ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ የተጠየቀውን ገንዘብ እና ይህንን ገንዘብ ለመሰብሰብ የተኬደበትን ርቀት አያይዛ ታወሳናለች።

“ለቀዶ ጥገናው 160 ሺ ብር ነበር የተጠየቀው። ይህንን ወጪ በግሌ መክፈል ስለማልችል ለእርዳታ እጄን ዘረጋሁ። በቅድሚያ ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት ላይ የሚሰራውን ጋዜጠኛ ዳዊትን ነበር ያማከርኩት። እሱም በራሱ ገፅ ብዙ ረዳኝ። ከዳዊት በተጨማሪም ጋዜጠኛ ዳኛቸውን ረድቶኝ የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስራዎች ተሰሩ። ከሁለቱ ግለሰቦች ውጪ ግን ቡታጅራ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ተሯሩጠውልኝ ገንዘቡ ተገኘ።

“ከገንዘቡ ጋር ተያይዞ ግን ሲነሳ የነበረውን ነገር ባጠራው ደስ ይለኛል። በጊዜው 160 ሺ ብር ለቀዶ ጥገናው ያስፈልጋል ብንልም ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ግን ነበሩብን። እንደውም የተባለው ገንዘብ ተሰብስቦ ህክምናውን ስጀምር የገንዘብ እጥረት አጋጥሞኝ ነበር። ግን በጊዜው ከህክምናው ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ወጪዎች ለመሸፈን ከተባለው ገንዘብ ጨመር ተደርጎ ገንዘብ ተሰብስቧል። ግን እንዳልኩት ይህ የሆነው ከቤት ኪራይ፣ ከፊዚዮ ቴራፒ፣ ከትራንስፖርት፣ ከምግብ፣ ከመዳኒት እና ከተያያዥ ወጪዎች ጋር ተያይዞ ነው።”

ከ6 ወራት በፊት በስፖርት ቤተሰቡ ርብርብ የቀዶ ጥገናውን ህክምና ያደረገችው ተጫዋቿ አሁን ላይ ስለምትገኝበት ሁኔታ በቀጣይ ትነግረናለች።

“ቀዶ ጥገናውን ካደረኩ 6 ወር ሆኖኛል። አሁን ፈጣሪ ይመስገን ደህና ነኝ። ቆሜ መሄድ መጀመሬ እራሱ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። አሁን ላይ ቀለል ያሉ እንቅስቃሴዎችን ጂም በመሄድ መስራት ጀምሬያለሁ። ቀስ በቀስ እያልኩም ወደ ቀድሞ አቋሜ ለመመለስ እጥራለሁ።

“ዘንድሮ በክለብ ደረጃ አታዩኝም። ህመሙ እየተሻለኝ ቢሆንም ቸኩዬ ወደ ጨዋታ ተመልሼ ሌላ አደጋ ማመምጣት አልፈልግም። በተጨማሪም በችግር ጊዜዬ ከጎኔ ሆኖ የነበረውን የስፖርት ቤተሰብ ለማገልገል በጥሩ አቋም ላይ መገኘት አለብኝ። ስለዚህ በ2013 በርትቼ ሰርቼ በ2014 ወደ ክለብ ተመልሼ መጫወት እቀጥላለሁ።”

ተጫዋቿ በችግር ጊዜዋ በገንዘብ፣ በሃሳብ እና በፀሎት ከጎኗ የነበሩትን ሁሉ በማመስገን በቶሎ ወደ እግርኳስ ህይወቷ በመመለስ የስፖርት ቤተሰቡን ለማስደሰት እንደምትጓጓ በመናገር ሃሳቧን አገባዳለች።

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!