የኢትዮጵያ የሊግ ውድድሮች በሙሉ አቅማቸው በተባሉበት ቀን ይጀምሩ ይሆን?

ሊጀመሩ የሳምንታት እድሜ የቀራቸው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ሆነ ሌሎች የውስጥ ውድድሮች በሙሉ አቅማቸው በተባሉበት ቀናት ይጀምሩ ይሆን?

የኢትዮጵያ የሊግ ውድድሮች የሚጀምሩበት ቀናት ይፋ መደረጋቸውን ተከትሎ በሁሉም ወገን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛል። በተለይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥቂት ክለቦች ካልሆነ በቀር አብዛኛዎቹ ክለቦች የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛል። አወዳዳሪውም አካል የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ባሳለፍነው ቅዳሜ በማካሄድ ክለቦች ተጋጣሚዎቻቸውን እንዲያውቁ አድርጓል። ይሁን እንጂ ትልቁ ጥያቄ እየሆነ የሚገኘው እና መልስ የሚፈልገው ጉዳይ ውድድሩ በሙሉ አቅሙ የመጀመሩ እና በተባለለት ጊዜ ታኅሣሥ ሦስት ቀን የመጀመሩ ነገር እርግጠኛ መሆን ጉዳይ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ውድድሩ በአግባቡ ተጀምሮ ስለ መጠናቀቁ በራሱ ብዙ ውስብስብ ነገሮች ከፊቱ ተደቅነዋል።

በዋናነት ኢትዮጵያ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ፣ ባህር ዳር ከተማ ከ ሱሑል ሽረ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሲዳማ ቡና የሊጉን የመክፈቻ ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ መርሐግብር ወጥቷል። ሆኖም አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች የመጀመርያ ጨዋታቸውን የማድረጋቸው ጉዳይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በአየርም በምድርም ቆሟል። ሦስቱ የትግራይ ክለቦች አሁን ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ምንም አይነት መረጃ ከአወዳዳሪው አካል ጋር እየተለዋወጡ አይገኝም። ባሳለፍነው ቅዳሜ በተካሄደው የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ላይም የሦስቱ ክለቦች ተወካዮች አልተገኙም። ቅድመ ዝግጅታቸውን በተሟላ ሁኔታ እየሰሩ ነው የሚለው ጉዳይም ማወቅ አልተቻለም። ከዚህ ባለፈ አሁን ያለው ሁኔታ መረጋጋት እና ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ የማይችል ከሆነ በውድድሩ የመሳተፋቸው ነገር በራሱ ትልቅ መልስ የሚፈልግ ጉዳይ አድርጎታል። ለዚህም ነው ከወዲሁ ውድድሩን በሙሉ አቅሙ የመጀመሩን ጉዳይ አጠራጣሪ ያደረገው። ከውድድሩ መጀመር ባሻገር ከዲኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት የውል ስምምነት ጋር ተያይዞ ሌላ ፈተና ይዞ እንደሚመጣ ተሰግቷል።

በዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ከሊግ ኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት ከአቶ ክፍሌ ሰይፉ ጋር ቆይታ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ሲሆን እንዳገኘናቸው ይዘናቸው እንደምንቀርብ ከወዲሁ እናሳውቃለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!