የሰማንያዎቹ… | የንግድ ባንክ የልብ ምት ጸጋዬ ወንድሙ (አግሮ)

በእግርኳሱ አይረሴ ጊዜያትን አሳልፏል። ጠንካራ እና ጠንቃቃ ተጫዋች እንደነበረ የሚነገርለት በወኔ፣ በፍላጎት በመጫወት የሚቴወቆ ነው። ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት ውጤታማ መሆኑን እያሳየ የሚገኘው በሰማንያዎቹ ከተፈጠሩ ኮከቦች አንዱ ጸጋዬ ወንድሙ (አግሮ) የዛሬው እንግዳችን ነው።

በእግርኳሱ አቃቂ ተፈጥሮ አቃቂ አድጓል። አሁንም አቃቂ እየኖረ ብዙ ትውልድ ፈጥሯል። በቀደመ ዘመን ከአዲስ አበባ ወደ ድሬደዋ በሚደረግ የባቡር ትራንስፖርት ጉዞ መስጫ ጣቢያ ግቢ ከቤቱ ፊት ለፊት በምተገኝ ሜዳ ጠዋት ወጥቶ ሲጫወት ውሎ ወደ ቤቱ ይሄዳል። በተለይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ትግል ፍሬ ተጫዋች የነበረው ንጉሤ አስፋውን እያየ እርሱ በሄደበት እየሄደ ማደጉ እግርኳስን እንዲወድ ምክንያት ሆኖታል። በአቃቂ አካባቢ ስለሺ ዳንኤል በሚያሰለጥነው የታዳጊ ቡድን ውስጥ ተይዞ መጫወት የጀመረው ይህ እግርኳሰኛ መንግሥቱ ቦጋለ በያዘው የቡና “ቢ” ቡድን ውስጥ በ1981 በመታቀፍ ለተወሰነ ጊዜ ተጫውቶ አሳልፏል። በመቀጠል የስሙን ያህል በቅፅል ስሙ ወደሚጠራበት አግሮ ኢንዱስትሪ ክለብ በማቅናት በሚያሳዝን ሁኔታ የመንግሥት ለውጥ መጥቶ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ለሦስት ዓመት ተጫውቷል። በኃላም በጊዜው የፊርማ ገንዘብ የቋሚ ሠራተኝነት ቅጥር በሆነበት ወቅት በ1985 ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማምራት እጅግ አይረሴና መልካም አስር ዓመታትን በመጫወት አሳልፏል። በመሐል ግን በ1988 ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ ለወራት ንግድ ባንክን ሲረከቡ የቡድኑን ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች በቀነሱበት ወቅት ጸጋዬ ወንድሙ ከመብራት ኃይሉ ሰይፈ ውብሸት ጋር በመቀያየር ለተወሰነ ወራት ለመብራት ኃይል ተጫውቶ በድጋሚ ከመንግሥቱ ስንብት በኋላ ከሰይፈ ውብሸት ጋር እንደገና ተቀያይረው ለንግድ ባንክ ተጫውቷል።

በንግድ ባfinance ረጅም ዓመት የተጫወተው በላቸው አበራ (ትንሼ) ስለ ፀጋዬ አግሮ ሲመሰክር “በጣም ደፋር፣ ልበ ሙሉ ሜዳ ውስጥ መሸነፍ የማይወድ፣ ሁሉን ነገር ሜዳ ውስጥ የሚሰጥ፣ በየትኛውም ቦታ የምታጫውተው ሁለገብ ተጫዋች ነው። ከሜዳ ውጭ በማኅበራዊ ህይወቱ ለተቸገሩ ተጫዋቾች በፍጥነት የሚደርስ፣ የሚያስተባብር እና የቡድን መንፈስ የሚጠብቅ ሰው ነው። አሁን አሰልጣኝ ለመሆን ያበቃው በተጫዋችነት ዘመኑ ያዳበራቸው መልካም ህይወቱ ነው። ፀጋዬ ለኔ ምርጥ ተጫዋች የነበረ ነው። ” በማለት ገልፆታል።

ከንግድ ባንክ በኃላ ለተወሰኑ ወራት ለብርሀንና ሰላም ከተጫወተ በኃላ በ1996 ራሱን ከእግርኳስ ተጫዋችነት አግልሏል። በብዙዎች ተጫዋቾች ዘንድ እንብዛም ባልተለመደ ሁኔታ በንግድ ባንክ እየተጫወተ ጎን ለጎን ትምህርቱን በመማር Banking and financ ድግሪውን በመያዝ በዛው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቋሚ ሠራተኝነት ሲያገለግል ቆይቷል። ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል በ1996 በተወለደበት አካባቢ በመጀመርያ ልጁ ስምዖን ስም “ሲማ” የተሰኘ የታዳጊ ፕሮጀክት በመክፈት መሥራት ጀምሯል። በኃላም የባንክ ቢ ቡድንን በ1999 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከሰራ በኃላ ቀጥታ ፊቱን ወደ ሴቶች እግርኳስ በማዞር ቼራልያ፣ ኢትዮጵያ ምርት ገቢያን፣ መከላከያ የሴት ክለቦችን በተለያዩ ጊዜያት ለአምስት ዓመታት አሰልጥኖ በ2007 የኢትዮጵያ መድን የወንዶች ቡድንን በመያዝ በብሔራዊ ሊግ የምድብ ማጣርያውን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ በቀዳሚነት አጠናቆ ድሬደዋ ከተማ ለሚዘጋጀው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት በሚደረግ የማጠቃለያ ውድድር ሳይሳካለት በቀረው ቡድን ውስጥ ፀጋዬ በምክትል አሰልጣኝነት መሥራት ችሏል። አቃቂ ቃሊቲ የወንዶች ቡድኑን ከ2008 ከምስረታው ጀምሮ እስከ 2011 ድረስ በአዲስ አበባ የዲቪዚዮን ውድድር አሸናፊ፣ የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ወልድያ ላይ አሸናፊ ፣ የብሔራዊ ሊግ ውድድር አዳማ ላይ አሸናፊ በመሆን በተከታታይ ሦስት ዓመት ቡድኑን ባለ ድል በማድረግ እና ሦስቱንም ዓመታት ኮከብ አሰልጣኝ ክብርን በማግኘት አቃቂ ቃሊቲን በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆን አድርጎታል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ አዲሱ የኢትዮጵያ መድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሹሟል።

ሌላኛው በንግድ ባንክ በተከላካይ ሥፍራ ተጣማሪው በመሆን አብሮት የተጫወተው ዐቢይ ሃይማኖት (አስቴር) ስለ ፀጋዬ ይህን ምሰክርነት ነግሮናል። “ፀጋዬ ከእኔ ጋር አብሮ በተጫወተበት ጊዜ በተለይ በቀኝ መስመር ላይ ከሚጫወቱ ከማቃቸው ተጫዋቾች መካከል በጣም ጠንካራ፣ ጠንቃቃ፣ አስተዋይ፣ አልሸነፍ ባይ እና ቡድንን በትክክል መምራት የሚችል አቅም የነበረው ተጫዋች ነው። በተለይ ጥንካሬው ልዩ የሆነ የመስመርን አጨዋወት በሚገባ የተረዳ ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ቦታዎች የተከላካይ አማካይ ቦታን ጨምሮ የተጫወተ ሁለገብ ጠንካራ ሰው ነው።”

ብዙዎቹ በተጫዋችነት እና ወደ አሰልጣኝነት ከገባ በኃላ ያለውን ችሎታ የሚመሰክሩለት ይህ የሰማንያዎቹ ድንቅ ተጫዋች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወጣት እና በዋናው ቡድን በመጫወት ሀገሩን አገልግሏል። ያለፉትን አርባ ዓመታት በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት እያገለገለ የሚገኘው ጸጋዬ ወንድሙ የዛሬ ተረኛ እንግዳችን በመሆን ይሄን ሀሳቡን አጋርቶናል።

“በእግርኳስ ተጫዋችነቴ ለኔ ስኬቴ የምለው አግሮ እያለው ከታችኛው ዲቪዚዮን ወደ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ስንገባ የውድድሩን ዋንጫ ያነሳንበት። እንዲሁም በእኛ ዘመን የነበረው ባንክ ጠንካራ ቡድን የተሰራበት ጊዜ ነው። ሁለተኛው ዙር ላይ በምን ምክንያት ወደ ኃላ እንደምንሸራተት ባይገባኝም ከንግድ ባንክ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ይፎካከር የነበረ ቡድን ነው። በባንክ ብዙ ነገር የተማርኩበት፣ ያገኘሁበት በጣም የማይረሳ ጥሩ ጊዜ ማሳለፌ ለኔ ስኬቴ ነው። ሌላው በወጣት በዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወቴ ትልቅ ስኬት ነው። በዛን ጊዜ ማንኛውም ተጫዋች የሚመኘው የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን ማልያ ለብሶ መጫወት ነው። እኔም በዚህ መልኩ ለሀገሬ በመጫወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

“በተጫዋችነት ዘመኔ አላደረኩትም ብዬ የማስበው የምቆጨው ነገር የለም። እኔ በተፈጥሮዬ ደፋር ነገር ነኝ። በቃ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደምችል አስባለው። የተለያዩ አሰልጣኞች በተለያዮ ቦታዎች ተከላካይ፣ አማካይ፣ አጥቂ ሁሉ አጫውተውኛል። ስለዚህ እኔ አላደረኩትም ብዬ የምቆጭበት ነገር የለም። ሆኖም በተወሰነ የሚቆጨኝ ነገር ድሮ የሚሰጠው ስልጠና እና አሁን የሚሰጠው ስልጠና በጣም ልዮነት አለው። አሁን አብዛኛው ተጫዋች እግሩ በሽተኛ ነው። በኛ ግዜ ጉዳቶች ሊኖሩ ይችላለሉ ግን በጣም ጠንካራ የአካል ብቃት የነበረበት ጊዜ ነው። በዚያን ዘመን እንደነበረው ወርቃማ ትውልድ ሀገር አለመጠቀሟ ይቆጨኛል።

” በ1987 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ወሳኝ የፍፃሜው ጨዋታ ላይ አልተጫወትኩም። በጊዜው ደግሞ በጣም ጥሩ አቅሜን የማሳይበት ወጣትነቱ፣ የመጫወት ፍላጎቴ ከፍተኛ የነበረበት ጊዜ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ አስቀድሞ በነበሩ የንግድ ባንክ ጨዋታዎች በሙሉ ተጫውቻለው። የዛን ዕለት ግን ያልገባሁበት ምክንያት ከጊዮርጊስ ጋር ልንጫወት አንድ ጨዋታ ሲቀረን ከመድን ጋር ጨዋታ ነበረን። ይህን ጨዋታ የመራው ዳኛ ደግሞ ኪነጥበቡ ነበር። ኪነጥበቡ ደግሞ በይፋ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነው። ወደ ሜዳ ስንገባ ተልዕኮ ይዞ ነው የገባው። ማንን በቀይ ማስወጣት እንዳለበትና ለሚቀጥለው ጨዋታ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያስበው። ምክንያቱም በዚህ ጨዋታ ላይ ንግድ ባንክ በየትኛውም አጋጣሚ መሸነፍ ወይም አቻ መውጣት አለበት። መድንን ካሸነፍን የጊዮርጊስን ጨዋታ ሳይጠብቅ ባንክ ቻምፒዮን ስለሚሆን። አሳይመንት ይዞ እንደገባ ያስታውቃል። ምንም ባላደረኩበት ሁኔታ “ኪነ አጫውተን እንጂ ብዙ በደል እያደረስክብን ነው። በትክክል አጫውተን እንጂ።” ስለው “ዝም በል” አለኝ። “ለምድነው ዝም በል እያልክ የምታስፈራራኝ” ስለው አውጥቶ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጣኝ። በኃላ ስሰማ የቡደኑ ወሳኝ ተጫዋች እርሱ ስለሆነ አስወጣው ተብሎ አሳይመንት አንደተሰጠው አወቅኩ። እርሱም በግልፅ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ መሆኑን በሚዲያ የተናገረበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ዓመቱን ሙሉ የለፋንበት ነገር በእንዲህ ያለ ሁኔታ በእንደዚህ ሁኔታ ዋንጫውን ማጣታችን በህይወቴ መቼም የማረሳው አሳዛኝ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

“የአግሮ መፍረስ ምክንያቱ የመንግሥት ለውጥ ነው። አግሮ ማለት የመንግሥት እርሻዎች ስብስብ ቡድን ማለት ነው። ይህ ማለት የሰባት የእርሻ ልማት ድርጅቶች የፈጠሩት የስብጥር ቡድን ነው። የራሱ የተጫዋች ዘመናዊ ማረፊያ ካምፕ፣ መጫወቻ ሜዳ የነበረው አደረጃቱ ጠንካራ የነበረ። ትጥቅ ሁሉ ከውጭ ሀገረረ በማስመጣት በጣም ጠንካራ ቡድን ነበረ። ለብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ያስመርጥ የነበረ ቡድን ከመንግስት ለውጥ በኃላ እነዚህ ሰባቱ ድርጅቶች ሲበተኑ ባለቤት አጥቶ በ1985 ለመፍረስ ቻለ እንጂ ብዙ ልጆችን ያስመርጥ የነበረ ጠንካራ ቡድን ነው።

“ከገጠመኝ ጋር ተያይዞ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ሞሮኮ ሄደናል። ፍስሀ በጋሻው በጣም የምንቀራረብ ጓደኛዬ የሆነ ተጫዋቾች ነበርን። ሐሙስ ሞሮኮ እንደገባን ደላሎች መጥተው መጥፋት ትፈልጋላቹ መቶ ዶላር አምጡ ስፔን በመርከብ እናስገባችኋለን ይሉናል። ‘አይ እኛ ጨዋታ አለብን ስለዚህ ነገር አናወራም ከጨዋታው በኋላ ናና እንነጋገራለን’ ይለዋል ፍስሀ፣ ከጨዋታው በኋላ ያ ደላላ ይመጣና ፍስሐን ያነጋግረዋል። መቶ ዶላር አምጡ በመርከብ የአንድ ቀን ጉዞ ነው ስፔን ትገባላቹ ሲል እኔ ብዙም የሚያወራው ነገር አልተመቸኝም ነበርና ፍስሀ እንሂድ ሲለኝ አልሄድም ይቅርብኝ አንተ መሄድ ከፈለክ አንተ ሂድ አልኩት። እርሱም ብቻዬን አላደርገውም ብሎ ይቀራል። ተመልሰን ወደ ሀገራችን ልንመጣ በግብፅ በኩል አንድ ቀን አድረን ሳለ አንድ ቴፕ ገዝቼ አዲስ አበባ መጣን። ቤት ገብቼ ቴፑን ሰክቼው ልሞክረው ሬዲዮኑን ስከፍት ከአንድ ቀን በፊት ከሞሮኮ ተነስተው ወደ ስፔን በጀልባ ሊሄዱ ሲሉ ሰምጠው በውስጡ የነበሩ በሙሉ አለቁ ብሎ ዜና ሰማሁ። የሚገርምህ ነገር ይሄን ስሰማ በጣም ደነገጥኩ። በዛን ሰዓት እሺ ብለን ብንሄድ ኖሮ ዛሬ እኔን ማግኘት አይቻልም ነበር። እና ይህ ነገር ሁሌም የማረሳው ገጠመኜ ነው።

“ብዙ ጊዜ በኛ ዘመን ተጫዋች ይጠፋበት የነበረው ምክንያት፤ የሚገርምህ ብሔራዊ ቡድን ሁላችን በጊዜው ተመርጠን የመጫወት ፍላጎቱ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም ከማን ሀገር ጋር ቢደርሰን እያልን እንጓጓ ነበር። ምክንያቱም ሞሮኮ ቢሆን ለትራንዚት ጣልያን ስለምንገባ እንጠፋለን ብለን እናስብ ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ይህ የሚሆንበትን ምክንያት እኔ ስገምት። አንድ ተጫዋች እግርኳስን ተጫውቶ ሲያቆም ቀጣይ ህይወቱ ማሰልጠን ነው። ሆኖም ያ ነገር በብዙ መልኩ ተዘግቶበታል። አሁን ምን እየሆነ መጣ በሆነ አጋጣሚ በክብር እንግድነት አውሮፓ ሄዶ በዛው እንዲጠፋ እየተደረገ ነው። ወይም የሆነ ቦታ እንዲሄድ ወይም እንዲሸሽ እየተደረገ ነው ያለው። ከተጫወተ በኃላ ምን እንደሚሆን ስለሚያሳስበው ይጠፋል። እኛ እዚህ የደረስነው በብዙ ትግል ውስጥ ነው። አሁን ላይ ለተጫዋች የሚሰጠው ክብር በዛን ዘመን ያልነበረ በመሆኑ መጥፋትን ያስብ ነበር። ስለዚህ እኔ አሁንም የምለው ነገር ተጫውቶ የሚያሳልፍ ተጫዋች በተጫዋችነት ዘመኑ መቼም መጫወት ስራው ስለሆነ ሊማር አይችልም። አሁን ማስተርስ የተለያዩ ነገሮች እያሉ ከጨዋታው ውጭ ለማድረግ ይሞክራሉ። ለተጫዋች ማስተርሱ ተጫውቶበት ያለፈበት ልምዱ ነው። ስለዚህ እኛ በትግል ውስጥ ነው የወጣነው አሁን ትንሽ እየተጠጋን መጥተናል። ሌሎችም ወደ አሰልጣኝነቱ እንዲቀርቡ መታገዝ አለባቸው።

” ወደ አሰልጣኝነቱ ለመግባት ምክንያት የሆነኝ ገና እግርኳስን እየተጫወትኩ በተወለድኩበት ሠፈር ታዳጊዎችን ሰብስቤ አሰለጥን ነበር። በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ በአንበልነት ቡድን መርቻለው ይህ የመሪነት ስሜቱ የማስተባበሩ እና ኃላፊት የመቀበል አቅሙ እና የማሰልጠኑ ፍላጎት ተደምሮ ወደ አሰልጣኝነቱ እንድመጣ መንገዱን ያመቻቸልኝ ይመስለኛል። እግርኳስን ሳቆም ሲማ ፕሮጀክትን በልጄ ስም ከፍቼ በባንክ ሰራተኛ ሆኜ ውጭ ሀገር ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር ግኑኝነት ፈጥሬ በአንድ ጓደኛዬ አማካኝነት የኦላይን የአሰልጣኞች ኮርስ በመውሰድ እራሴን እያሳደኩኝ አሁን ላለሁበት ደረጃ እንድደርስ በተለያዩ ክለቦች በማሰልጠን አልፌ እዚህ ደርሻለው”።

“በአቃቂ ስኬታማ ዓመታት ለማሳለፉ የረዳኝ በዋናነት መድን በ2007 እያለው ጥሩ ቡድን ሠርተን ቶርናመንት ላይ በሚያሳዝን ሁኔታ በጥቂት ልጆች ምክንያት ውጤት ማጣታችን የሚያስቆጭ ነበር። ወደ አቃቂ ስመጣ በተለይ በቶርናመንት ውድድር ላይ መድን እያለው ምድነው ክፍተታችን፣ ቶርናመንት ላይስ የሚያስፈልጉ ነገሮች ምድናቸው ብዬ በመድን የወሰድኩት ትምህርት ጠቅሞኛል። ለዚህም ነው ለተከታታይ ዓመት አቃቂን ከምስረታው ጀምሮ ከፍተኛ ሊግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋንጫ አሸናፊ በመሆን እና እኔም ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን ክለቡን እዚህ ያደረስኩት። እንዲያውም በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በተመሰረተ ጀምሮ በሦስት ዓመት ከፍተኛ ሊግ የገባ ቡድን ያለ አይመስለኝም።

“እንደ አሰልጣኝ መሥራት የምፈልገው ቡድን በእግርኳስ ማጥቃትም መከላከልም ሥራዎች ናቸው። እኔ በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ልጆቼ ጊዜአቸውን እንዲያጠፉ እፈልጋለው። ፖዝሽን ለኔ የጨዋታ አንድ መሳርያ(መጠቀሚያ) ነገር ነው። እኔ በቀጥተኛ ፉትቦል (Direct Football) አምናለው። በሚጠቅሙ ነገሮች የተሻሉ ነገሮች እየመረጥክ ውጤት እንዲመጣ እፈልጋለው። አሁን ለምሳሌ መጀመርያ የሚጠቅሙ አጥቂ ከሆነ አጥቂ መጠቀም፣ መከላከል ከሆነ መከላከሉን መጠቀም እንጂ ኳስ በመቆጣጠር ብቻ ጊዜው እንዲባክን አልፈልግም። ስለዚህ በሚጠቅሙ ቦታዎች ላይ ክፍተቶችን እያየህ አሸናፊ የምትሆንበትን መንገድ መቀየስ ዋና ግቤ ነው። ስለዚህ የአካል ብቃቱ የተሟላ ቡድን እንዲሆን እፈልጋለው። በአጠቃላይ በዚህ መንገድም አቃቂ እያለው ውጤታማ ሆኜበታለው። ሦስት ዓመት ዋንጫ ማንሳት የሚያሳየው ነገር አለ።

“የቤተሰብ ህይወቴ በመጀመርያ የኔ ቤተሰቦች የቃሊቲ የመጀመርያው ሠፋሪዎች ናቸው። ከዛም እኔም እስካሁን ትዳር መስርቼ የምኖረው በዚሁ አቃቂ ከተማ ነው። ስምኦን፣ ናትናኤል እና ዮናታን ፀጋዬ የሚባሉ የሀያ አንድ፣ አስራ ስድስት እና የስምንት ዓመት እድሜ ያላቸው ልጆች አሉኝ። እግርኳስን በተያያዘ የመጀመርያው ልጄ ስምኦን ወደ ትምህርቱ ነው የሚያዘነብለው፣ ናትናኤል ዓምና መብራት ኃይል ከ15 ዓመት በታች ቡድን እየተጫወተ ነበር የኮሮና ወረርሽኝ መጥቶ ውድድሩ ተቋረጠ እንጂ እየተጫወተ ነው። የመጨረሻው ልጄ ብዙም ፍላጎት የለውም የመጫወት እንግዲህ ከሦስቱ ልጆቼ ናትናኤል ነው የኔን አርአያ ተከትሎ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብዬ አምናለው።

በመጨረሻ ኢትዮጵያ መድንን ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ በቅርቡ ኃላፊነቱን ተረክቤያለው። የሚገርምህ የመድንን ታሪክ ከልጅነቴ ጀምሮ አቀዋለው። እኔ ባንክ እየተጫወትኩ መድን ድንቅ ትውልዶች የፈጠረ ቡድን ነው። ያኔ የነበረው ጠንካራ ቡድን አሁን የት ነው ያለው ምክንያቱ ምንድነው የሚለው መልስ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። እኔ አሁን ይሄን ኃላፊነት ስወስድ የቀድሞ የአጨዋወት ባህሉን፣ ስሙን ለመመለስ ነው። የመጀመርያው አንድ ዓመት ቡድን የምገነባበት ነው። ሁለተኛው ዓመት አዋህደህ በሦስተኛው ዓመት አንድ ጠንካራ ቡድን ፈጥረህ ክለቡ የሚያስብበትን ዓላማ ማሳካት አለብኝ ብዬ ነው ፕሮፖዛል ያስገባሁት። በአንድ ዓመት ታግለህ ፕሪሚየር ሊግ ልትገባ ትችላለህ። ግን የመድንን ዝና ለመመለስ ጊዜ፣ ትዕግስት፣ ዕውቀት ይፈልጋል። በአንድ ዓመት ውስጥ ፕሪምየር ሊግ ካላስገባህ የሚል ነገር ብዙ ጊዜ አሰልጣኝ ላይ እንደ ቅድመ ሁኔታ ይቀርባል። ይህ አሰልጣኙን ተረጋግቶ እንዳይሰራ ጫና ውስጥ እንዲገባ ከዛ ይባረር እና ወደ ሌላ ክለብ በመቀያየር ወንጀል ይሰራል። አላስፈላጊ ነገሮች ይፈፀማሉ። ስለዚህ እኔ ዘንድሮ በጣም የመጫወት ፍላጎት ባላቸው ወጣቶች እና ትንሽ ልምድ ባላቸው ቡድኑ በጥንቃቄ ሳልቸኩል እየሰራሁ ነው። ብቻ ዘንድሮ ከቻለ ፕሪምየር ሊግ የሚገባ ካልቻለ ግን የተሻለ ተስፋ ሰጪ የሆነ ቡድን በመስራት በሦስት ዓመት ውስጥ ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ መመለስ አቅጄ ለመስራት መድንን ተረክቤያለው። ደግሞም ይሄን እቅዴን በእርግጠኝነት አሳካዋለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!