ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ3ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ከረቡዕ እስከ ዓርብ በተደረጉት የሊጉ ስድስት ጨዋታዎች ላይ በመመስረት ሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ስብስብ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ አካታለች።

አሰላለፍ (4-3-3)

ግብጠባቂ

ሀሪስተን ሄሱ (ባህር ዳር ከተማ)

በተጋጣሚዎች መካከል ሰፊ የአቋም ልዩነት በታዩባቸው የሳምንቱ ጨዋታዎች ነጥረው የወጡ ፣ በከባባድ ሙከራዎች ተፈትነው ቡድናቸውን የታደጉ ግብ ጠባቂዎች አልታዩም። ካሉት አማራጮች ውስጥ ግን ግብ ሳይቆጠርበት ያጠናቅቀው ብቸኛው ግብ ጠባቂ ሀሪሰተን ሄሱን የቦታው ተመራጭ አድርገነዋል።

ተከላካዮች

አህመድ ረሺድ (ባህር ዳር ከተማ)

ከኢትዮጵያ ቡናው አሥራት ቱንጆ እና ከፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን ጋር በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በሳምንቱ ድንቅ አቋም አሳይቷል። በሁለቱም መስመር መጫወት ስለሚችልም በቡድናችን የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ አካተነዋል። አህመድ ከአዳማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ የነበረው ሲሆን ወደ ግብ ያልተቀየሩ ሦስት መልካም የግብ አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችሏል።

አይዛክ ኢሲንዴ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ዩጋንዳዊው የመሀል ተከላካይ የሀዲያ ሆሳዕናን የኋላ ክፍል በአግባቡ በመምራት የዘወትር ጠንካራ ተከላካይነቱን ያሳየበትን ጨዋታ አሳልፏል። ከዚህ በተጨማሪም ከሄኖክ አርፌጮ የተሻማውን የማዕዘን ምት በሚታወቅበት የግንባር ኳስ የማስቆጠር ክህሎቱ ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑ ጨዋታው ቀሎት አብዛኛውን ደቂቃ እንዲቀጥል ያደረገች ወሳኝ ግብ በስሙ አስመዝግቧል።

ኤድዊን ፍሪምፖንግ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ጋናዊው ተከላካይ የቡድኑን የመከላከል እንቅስቃሴ በሚገባ ከመምራቱ ባሻገር አንድ ለአንድ ግንኙነቶት ላይ በተደጋጋሚ የበላይነቱን ማሳየት ችሏል። በበርካታ የጨዋታ ቅፅበቶች ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ ለማጥቃት ወደ ፊት በሚጓዝበት ወቅትም ወደ ግራ አስፍቶ በመከላከል የሀዋሳ ከተማ አጥቂዎችን በቀላሉ በመቆጣጠር ጥሩ ቀን ማሳለፍ ችሏል።

አሥራት ቱንጆ (ኢትዮጵያ ቡና)

የግራ መስመር ተከላካዩ አሥራት ቡና ድሬዳዋን ባሸነፈበት ጨዋታ ወደ ፊት በመሄድ በተጋጣሚው ሳጥን ውስጥ በተደጋጋሚ የመገኘት ድፍረቱ ነበረው። ሀብታሙ ታደሰ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች መነሻ የነበረውም አሥራት ነበር። ተጫዋቹ የማጥቃት እና የመከላከል ኃላፊነቱን በአግባቡ በተወጣበት የዕለቱ እንቅስቃሴ ከፋስል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን ጋር በመፎካከር የቦታው ተመራጭ ችሏል። ተጫዋቹ ለሁለተኛ ተከታታይ ሳምንት የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ መካተት ችሏል።

አማካዮች

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

የባህር ዳር የፊት መስመር ተሰላፊዎች በነፃነት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከሳምሶን ጥላሁን ጋር ድንቅ ጥምረት የፈጠረው የቡድኑ አምበል ሚና ከፍ ያለ ነበር። የአዳማን ቁልፍ አማካዮች ከመቆጣጠር ባለፈ ወደፊት ጠጋ በማለት የቡድኑ የማጥቃት ሒደት ላይ በመሳተፍ ጭምር ፍቅረሚካኤል ያሳየው ብቃት በሳምንቱ ምርጥ ቡድን የተከላካይ አማካይነት ሚናን እንዲይዝ የሚያደርግ ሆኗል።

ካሉሻ አልሀሰን (ሀዲያ ሆሳዕና)

ለመጀመሪያ ጊዜ በቡድኑ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የተካተተው ጋናዊው ባለተሰጥኦ የጨዋታ አቀጣጣይ ካሉሻ አልሀሰን የመጨረሻ ኳስ ለአጥቂዎች የማድረስ ብቃቱን በሚገባ አሳይቷል። ቡድኑ ያስቆጠራቸውን ሁለተኛ እና ሦስተኛ ግቦች ለሳልፉ ፎፋና እና ቢስማርክ አፒያ አመቻችቶ በማቀበል ለድሉ ቁልፍ ሚና መወጣት ችሏል።

ያሬድ ታደሰ (ወልቂጤ ከተማ)

የወልቂጤ ከተማን ሁለት ግቦች ከመረብ ያገናኘው እና በመስመር አጥቂነት ጨዋታውን የጀመረው ያሬድ ታደሰን አማካይ ቦታ ላይ ምርጫችን አድርገነዋል። በተረጋጋ አጨዋወት ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ጋር ሲገናኝ የነበረው ብስለት እና በድንገት አክርሮ ወደ ግብ ይልካቸው የነበሩ ኳሶች የቀድሞው የድሬዳዋ ተጫዋች ያለበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሳዩ ነበሩ።

አጥቂዎች

አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ግማሹን የሜዳ ክፍል ኳስ እየገፋ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ ድንቅ ጎል ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረው አቤል ለሀዋሳ ራስ ምታት ሆኖ አርፍዷል። በጨዋታው የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ጎሎች አመቻችቶ ሲያቀብል እሱ ላይ በተሰራ ጥፋት ቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት እንዲያገኝ አድርጋጓል። የሀዋሳው ዳዊት ነጋሽ ራሱ ላይ ያስቆጠራት አራተኛ ጎል ከማዕዘን ምት የተሻማችውም በአቤል ያለው ነበር።

ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)

ታታሪው የመስመር አጥቂ ዐፄዎቹ በጅማ ላይ ባስቆጠሯቸው አራት ግቦች ላይ ሁሉ ተሳትፎ ነበረው። የአምሳሉ የቅጣት ምት ጎል ሲቆጠር እሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘ ዕድል ሲሆን ሌሎች ሁለት ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል እና አራተኛውን ራሱ ከመረብ በማሳረፍ ቁልፍ ተጫዋችነቱን አሳይቷል። ከዚህ ባለፈ በጨዋታው የነበረው አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና የጨዋታ ፍላጎቱ የተለየ ሆኖ አግኝተነዋል።

ሀብታሙ ታደሰ (ኢትዮጵያ ቡና)

የቡና ከፊት አጥቂ በመሆን ሁለተኛ ጨዋታውን የጀመረው ሀብታሙ ቡድኑ የሚፈልገውን አጨዋወት ለማገዝ በቅብብሎች ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በመገናኘት ጥሩ መናበብ ሲያሳይ እንደመጨረሻ አጥቂነቱም በግብ ፊት ካገኛቸው አጋጣሚዎች ሁለቱን ወደ ግብነት ለውጧል። በተለይም ግብ ጠባቂውን አልፎ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ የአጥቂውን ክህሎት የምታሳይ ነበረች።

አሰልጣኝ – አሸናፊ በቀለ

ከቡድናቸው ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ያሳኩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን ላይ በአሰልጣኝነት ተሰይመዋል። ሀዲያ ሆሳዕና ሲዳማን በገጠመበት በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በፊት መስመሩ ላይ የዳዋ ሆቴሳን ክፍተት በመሸፈን እና ቡድኑ ጫና ውስጥ በገባባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች በጥብቅ እንዲከላከል በማድረግ ውጤት ይዞ እንዲወጣም አስችለዋል።

ተጠባባቂዎች

ፍሬው ጌታሁን (ድሬዳዋ ከተማ)
ሰለሞን ወዴሳ (ባህር ዳር ከተማ)
አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከነማ)
አብዱልከሪም ወርቁ (ወልቂጤ ከተማ)
ሳሙኤል ዮሐንስ (ፋሲል ከነማ)
ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)
ጌታነህ ከበደ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)


© ሶከር ኢትዮጵያ