ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የታኅሣሥ ወር ምርጦች እና የወሩ ቁጥራዊ መረጃዎች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን የስድስት የጨዋታ ሳምንት መርሐ ግብር አከናውናል። ልክ የዛሬ ወር በተጀመረው የ2013 የውድድር ዘመን በታኅሣሥ ወር የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎች እና የወሩ ምርጦችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አጠቃላይ የወሩ መረጃ

የጨዋታ ብዛት – 36
የተቆጠሩ ጎሎች ብዛት – 107
በአማካይ በጨዋታ – 3 ጎሎች
የማስጠንቀቂያ ካርድ ብዛት – 159
የቀይ ካርድ ብዛት– 11


ከፍተኛ ነጥብ የሰበሰቡ ቡድኖች

1. ሀዲያ ሆሳዕና – 13 (+6)
2. ፋሲል ከነማ – 13 (+5)
3. ኢትዮጵያ ቡና – 13 (+4)

ዝቅተኛ ነጥብ የሰበሰቡ ቡድኖች

1. ጅማ አባ ጅፋር – 3 (-8)
2. ወላይታ ድቻ – 3 (-5)
3. ሲዳማ ቡና – 4 (-5)


የጎሎች መረጃ

አጠቃላይ ጎል – 107
በጨዋታ የተቆጠሩ – 87
በፍፁም ቅጣት ምት የተቆጠሩ – 20
በራስ ላይ የተቆጠሩ – 3
የመከኑ ፍፁም ቅጣት ምቶች – 4
ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ብዛት – 57
በርካታ ጎሎች ያስቆጠረ ቡድን – ኢትዮጵያ ቡና (14)
ዝቅተኛ ጎሎች ያስቆጠረ ቡድን – ሲዳማ ቡና (3)
በርካታ ጎሎች የተቆጠረበት ቡድን – ወላይታ ድቻ (13)
ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት ቡድን – ሀዲያ ሆሳዕና (4)


የታኅሣሥ ወር ዲሲፕሊን ቁጥሮች

አጠቃላይ የማስጠንቀቂያ ካርዶች – 159

አጠቃላይ የቀይ ካርዶች – 11

በርካታ ካርዶች ያስመዘገበ ቡድን – ድሬዳዋ ከተማ (16 ቢጫ እና ሁለት ቀይ)፣ ወልቂጤ ከተማ (17 ቢጫ እና አንድ ቀይ)

ዝቅተኛ ካርዶች የተመዘዙበት ቡድን – ሰበታ ከተማ (2 ቢጫ)


የግል ቁጥሮች

ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ – ሙጂብ ቃሲም እና አቡበከር ናስር (8 ጎሎች)

በርካታ ኳሶች ያመቻቸ ተጫዋች – አቤል ያለው (5 ኳሶች)

በርካታ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገ – አቤል ያለው – 7 (ሁለት ጎሎች እና አምስት አሲስት)

በርካታ ጨዋታ ጎል ያልተቆጠረበት – ፍሬው ጌታሁን፣ ጀማል ጣሰው፣ ሀሪስተን ሄሱ፣ መሳይ አያኖ፣ ሚኬል ሳማኬ (2 ጨዋታዎች)

ከፍተኛ ጎል ያስተናገደ ግብ ጠባቂ – ሜንሳህ ሶሆሆ እና ሰዒድ ሀብታሙ (9 ጎሎች)

እያንዳንዷን ደቂቃ የተጫወቱ ተጫዋቾች ብዛት – 35


የወሩ ምርጦች

ከሶከር ኢትዮጵያ ምርጫ በተጓዳኝ 3500 የአንባቢያን ድምፆችን የተቀበልን ሲሆን የሶከር ኢትዮጵያ 70% እና የአንባቢዎቻችንን 30% በማጣመር እና ከ100 ነጥብ በማስላት የታኅሣሥ ወር ምርጦችን በዚህ መልኩ መርጠናል።

የወሩ ኮከብ ተጫዋች – አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለ ኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ የዘንድሮ አቋም ብዙ ተብሏል። በወሩ ቡድኑ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ የተሰለፈው አቡበከር በስምንት ጎሎች የሊጉ ዋና ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ከሙጂብ ጋር በጋራ እየመራ የሚገኝ ሲሆን ቡና ከመሪዎቹ ተርታ ተሰልፎ ወሩን እንዲያጠናቅቅ የአንበሳውን ድርሻ መወጣት ችሏል። በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሦስት ጊዜያት ያህል መመረጥ የቻለው አቡበከር በዝግጅቶ ክፍላችንም ሆነ በአንባቢዎች ምርጫ ቀዳሚ የሆነ ሲሆን አጠቃላይ 95.8 ነጥብ በመሰብሰብ የወሩ ኮከብ አድርገን መርጠነዋል።

ሌላው በዚህ ወር ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው አጠቃላይ 54.6 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ ሙጂብ ቃሲም 45.8 ነጥብ በመሰብሰብ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

የወሩ ኮከብ ጎል ጠባቂ – ፍሬው ጌታሁን (ድሬዳዋ ከተማ)

በታኅሣሥ ወር በተደረጉ ጨዋታዎች ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩ ግብ ጠባቂዎች መካከል የድሬዳዋ ከተማው ፍሬው ጌታሁን የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጥ ተብሎ ተመርጧል። ፍሬው ዘንድሮ ቡድኑ ወጣ ገባ አቋም ቢያሳይም በግሉ ድንቅ ጊዜ በማሳለፍ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለት ጊዜያት መካተት ችሏል። ፍሬው በዝግጅት ክፍላችን ከፍተኛ ድምፅ ያገኘ ሲሆን በአንባቢያን በተሰጠ ድምፅ ሁለተኛ ደረጃ ይዟል። በአጠቃላይ ድምፅ ደግሞ 86.8 ነጥብ በመሰብሰብ የወሩ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተመርጧል።

በወልቂጤ ከተማ መልካም ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ጀማል ጣሰው በ67.8 አጠቃላይ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወጣቱ የሰበታ ከተማ ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል 51.4 ነጥቦች በመሰብሰብ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

የወሩ ኮከብ አሰልጣኝ – አሸናፊ በቀለ (ሀዲያ ሆሳዕና)

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሆሳዕና እጅግ ድንቅ አጀማመር እንዲያደርግ ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውተዋል። አንድ ጨዋታ ያነሰ ተጫውቶ መሪ በመሆን ወሩን ያገባደደው ሆሳዕና ጠንካራ የቡድን አደረጃጀት እንዲኖረው ከማስቻላቸው ባሻገር በስኬታማ የቅያሬ ውሳኔዎቻቸው ከጨዋታዎች ድል ይዘው መውጣት ችሏል። አሰልጣኝ አሸናፊ በዝግጅት ክፍላችን ምርጫ ቀዳሚ የሆኑ ሲሆን በአንባቢዎች ምርጫ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ተቀምጠዋል። በድምር 86.8 ነጥብም የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ቡናው ካሣዬ አራጌ የአንባቢዎች ቀዳሚ ምርጫ ሲሆኑ በሶከር ኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በአጠቃላይ 73.4 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የባህር ዳር ከተማው ፋሲል ተካልኝ ደግሞ በ36 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ