ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባጅፋር ከ ባህር ዳር ከተማ

በ24ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ መርሐ-ግብር የሆነውን ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

መውረዱን ቀደም ብሎ ያረጋገጠው ጅማ አባጅፋር ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ እጅግ ከተራራቀው ድል ጋር ዳግም ለመገናኘት ሲል ብቻ ነገ ወደ ሜዳ ይገባል። ሦስት ነጥብ ካገኙ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው ባህር ዳር ከተማዎችም ከድል ጋር ታርቆ በቀሯቸው ሁለት ጨዋታዎች የሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁበትን ሁነት ለመፍጠር ጨዋታውን ይጠባበቃሉ።

በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም መሻሻል እያሳየ የነበረው ጅማ አባጅፋር ዘግይቶ ነቃ እንጂ በሊጉ ሊቆይ ይችል ነበር። እርግጥ የትግራይ ክልል ክለቦች ጉዳይ አሁንም በውል ባለመታወቁ ጅማ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ በሊጉ ሊተርፍ ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ በመከላከሉ ረገድ ጠንከር ያለ የሚመስለው ቡድኑ ፊት መስመር ላይ ያለውን ክፍተቱን በቀሪዎቹ ጊዜያት አስተካክሎ ለቀጣይ ውሳኔዎች ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል። እስከዛው ድረስ ግን የነገውን ጨምሮ የቀሩትን ሦስት ጨዋታዎች በጥሩ አፈፃፀም ማገባደድ ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ በራሂም ኦስማኖ የሚመራው የቡድኑ የፊት መስመር ግቦችን ማምረት አለበት።

በአብዛኛው ቀጥተኛ አጨዋወት የሚከተለው ጅማ ነገም በዚህ የጨዋታ መንገድ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በተለይ በረጅሙ የሚላኩ እና ከመስመር የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች የቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ ቀዳሚ አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ቁመታሙ አጥቂ ራሂም ኦስማኖ ምቹ ነው። ስለዚህም በነገው ጨዋታ እሱን ዒላማ ያደረጉ ኳሶች ሊበረክቱ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ አይደክሜው ተመስገን ደረሰ በመስመር ላይ የሚያደርጋቸው እንቅስዋሴዎች አደጋቸው ከፍ ያሉ ናቸው። ስለሆነም ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርገው የሰላ እንቅስቃሴም ጎል ሊያገኝ እንደሚችል መታሰብ ይገባል። ከምንም በላይ ደግሞ ቡድኑ ከጫና ውጪ ሆኖ መጫወቱ ከባህር ዳር የበለጠ ነፃነት እንዲኖረው ያደርጋል። 

ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚያደርገውን ውጤት በራሱ ብቃት እያጠበበ የመጣው ባህር ዳር ከተማ ወቅታዊ ብቃቱ ደከም ብሏል። በተለይ ግብ የማስተናገድ ችግር እስከ ቅርብ ጊዜያት የሌለበት ቡድኑ አሁን አሁን በመሰረታዊ ስህተቶችም ጭምር ግቡን እያስደፈረ ነው። ይህ የላላ የኋላ መስመሩ ደግሞ ጨዋታዎችን እንዳያሸንፍ እያደረገው ይገኛል። ከዚህም መነሻነት ቡድኑ የጠበበ የሚመስለውን ዋነኛ ዓላማ (2ኛ ደረጃን መያዝ) ለማሳካት ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል። እርግጥ ይህንን ለማሳካት የራሱን ውጤት ብቻ ባይጠብቅም የዘገየውን ስራውን አጠናቆ የሚፈጠረውን መጠበቁ መልካም ነው። 
ፈጣን ተጫዋቾች ያሉት ባህር ዳር ከተማ ነገም ተጋጣሚውን ላይ ጫና ለማሳደር ፍጥነት የታከለበት እንቅስቃሴ እንደሚከተል ይገመታል። በተለይ ከወገብ በላይ ያሉት ተጫዋቾች በማጥቃት እንዲሁም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር በአንፃራዊነት ዝግ ያለ ፍጥነት ያለውን የጅማን የኋላ መስመር እንደሚረብሹ ይጠበቃል። ከሁሉም በላይ ግን በመስመሮች መካከል አደገኛ የሆነው ፍፁም ለጅማ ተከላካዮች ፈተናን ሊሰጥ ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን በቀላሉ የማይፍረከረከውን የጅማን የተከላካይ መስመር ለማስከፈት እና ለመዘርዘር ሁለቱን መስመሮች (ግራ እና ቀኝ) የታከኩ እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የመስመር አጥቂዎቹ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የመስመር ተከላካዮቹ በላይኛው የሜዳ ክልል ላይ ያላቸው የማጥቃት ተሳፎ እጅግ ሊጨምር ይገባል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ጅማ አባጅፋር እና ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተዋል። በዚህም በ2011 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ግንኙነት ያደረጉት ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት (አንድ አቻ) አገባደዋል። በሁለተኛ ዙር ግንኙነታቸው ግን ጅማ አባጅፋር ከሜዳው ውጪ ባህር ዳርን 1-0 መርታት ችሏል። ዘንድሮ በተከናወነው ሦስተኛ የእርስ በእርስ ጨዋታቸው ደግሞ 2-2 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።