ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማን ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል። ቡናማዎቹም በቀጣይ ዓመት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመሳተፍ ያለውን የሰፋ ዕድል ለማረጋገጥ ወደ ሜዳ የሚገባው ኢትዮጵያ ቡና ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ካሸነፈው ቋሚ ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ጨዋታውን ጀምሯል። ከሊጉ መውረዱን ቀድሞ ያገጋገጠው አዳማ ከተማ በኩል በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈው ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። በዚህም አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ሴኮባ ካማራ፣ ላሚን ኩማሬ፣ ብሩክ መንገሻ እና ሰይፈ ዛኪርን አሳርፈው ዳንኤል ተሾመ፣ እዮብ ማቲያስ፣ ላውረንስ ኤድዋርድ እና ደሳለኝ ደባሽ በቋሚነት አካተዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ድንቅ የውድድር ዘመን ላሳለፈው አቡበከር ናስር ወላጅ አባቱ፣ እናቱ እንዲሁም ወንድሞቹ ሳይጠበቅ ስታዲየም በተገኙበት ሽልማት አበርክቷል። ሽልማቱንም ወላጅ አባቱ አቶ ናስር ለተጫዋቹ (ለልጃቸው) አበርክተዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከአዳማ በተሻለ ኳስን በማንሸራሸር ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከኳስ ጀርባ በቁጥር በዝተው ለቡና ተጫዋቾች ክፍተት በመንፈግ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። ጨዋታው 12ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ቡድኑ የኢትዮጵያ ቡናው የግብ ዘብ ተክለማርያም ሻንቆ በተሳሳተው ኳስ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በዚህም ተክለማርያም ለመሐል ተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ አቀብላለሁ ብሎ የተሳሳተውን ኳስ በላይ አባይነህ አግኝቶት በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው አብዲሳ ጀማል ቢሰጠውም ተክለማርያም የሰራውን ስህተት ማረሚያ ዕድል አግኝቶ ኳሱን አምክኖታል። የቡናን ስህተቶች መፈለግ ያልተውት አዳማዎች በ20ኛው ደቂቃም የተጋጣሚ የአማካይ መስመር ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅመው መሪ ለመሆን ጥረዋል። በዚህ ደቂቃም ኢሊሴ ጆናታን መሐል ሜዳ ላይ ያገኘውን ኳስ የተክለማርያምን ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክቶ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም የግቡ ቋሚ ኳሱን መልሶታል።

ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ተሽለው የተገኙት አዳማዎች በ22ኛው ደቂቃም በፈጣን ሽግግር የቡና የግብ ክልል ደርሰው ነበር። በዚህ ደቂቃም ጀሚል ያቆብ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በቃሉ ገነነ ለመጠቀም ጥሮ ተክለማርያም አውጥቶበታል። ግማሽ ሰዓት እስኪሞላ ድረስ የጠራ የግብ ማግባት ዕድል ያልፈጠሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ መሪ ለመሆን ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል። በቅድሚያም የመሐል ተከላካዩ ደስታ ጊቻሞ ኳስ በእጅ በመንካቱ የቅጣት ምት ያገኘው ቡድኑም በአቡበከር ናስር አማካኝነት ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ መልሶበታል። የተመለሰውንም ኳስ ምንተስኖት ከበደ ወደ ግብነት ቢቀይረውም የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ በሚል ግቡን ሽረውታል። ከዚህ በተጨማሪ አስራት ቱንጆ በግራ መስመር በኩል ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢሞክረውም ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። በ38ኛው ደቂቃ በድጋሜ የቡናን ስህተት ተጠቅመው ወደ ግብ ያመሩት አዳማዎች በበኩላቸው በላይ ዓባይነህ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ለገባው ሀብታሙ ወልዴ አቀብሎት ነገርግን ሀብታሙ ሳይጠቀምበት በቀረው ኳስ እጅግ አስደንጋጭ ሙከራ አድርገዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ እጅግ ብልጫ የነበራቸው ነገርግን የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ የተሳናቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና አጋማሹ ሁለት ደቂቃ ሳይሞላው አስደንጋጭ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም ሀብታሙ ታደሰ በግራ መስመር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ለአቡበከር ቢያቀብለውን የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ወደ ግብ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። በተቃራኒው ኳስን ለመቆጣጠር ብዙም ፍላጎት ያላሳዩት ነገርግን ያለቀላቸው የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያደርጉ የታዩት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በ54ኛው ደቂቃ የልፋታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም ተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በላይ ዓባይነህ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮት መሪ ሆነዋል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር የያዙት ቡናዎች በአመዛኙ መሐል ለመሐል የሚደረጉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲሞክሩ ነበር። በ61ኛው ደቂቃም ዊልያም ሰለሞን ከአቡበከር የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ መቶት ቡድኑን አቻ ለማድረግ ቢጥርም ብዙም ሀይል ያልነበረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ሳይቸገር ተቆጣጥሮታል። ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላም ኢሊሴ ጆናታን የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት አቡበከር ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ መክኖበታል። ከዚህ ቅጣት ምት በተጨማሪም አቡበከር ሌላ የቅጣት ምት በ90ኛው ደቂቃ አግኝቶ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ላይ ሌላ የቅጣት ምት ያገኘው ቡድኑም ኳስ እና መረብን አገናኝቶ አቻ ሆኗል። በዚህም አቡበከር ያሻገረውን የቅጣት ምት ተከላካዮች ሲመልሱት አበበ ጥላሁን አግኝቶት ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተገባዷል።

ባለቀ ደቂቃ አንድ ነጥብ ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ነጥባቸውን 41 በማድረስ የ2ኛ ደረጃን ይዘው የውድድር ዓመቱን አጠናቀዋል። ይሄንንም ተከትሎ ቡድኑ በቀጣይ ዓመት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መሳተፉን አረጋግጧል። ከሊጉ መውረዳቸውን ቀድመው ያወቁት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ነጥባቸውን 14 በማድረስ የውድድር ዓመቱን የደረጃውን ግርጌ በመያዝ ጨርሰዋል።