“ሙጂብ ወደ አልጄሪያ ጉዞው ካልተሳካ ዳግም ለፋሲል ለመጫወት ተስማምቶ ነው መልቀቂያ የወሰደው” አቶ አብዮት

ወደ አልጄሪያ የሚያደርገው ጉዞ እክል ያጋጠመው ሙጂብ ቃሲም ከበርካታ የሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር ንግግር እያደረገ ሲሆን በፋሲል ከነማም የሚቀጥልበት ዕድል እንዳለ ተጠቁሟል።

ግዙፉ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ሙጂብ ቃሲም ከቀናት በፊት ወደ አልጄሪያው ክለብ ጄ ኤስ ካቢሌ ለማምራት ስምምነት ማድረጉ ተሰምቶ ነበር። ተጫዋቹ ራሱ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ከጄ ኤስ ካቢሌ ጋር በሦስት ዓመት ውል ለመጫወት ቢስማማም እንደ አዲስ በተፈጠረ ድርድር የሙጂብ ወደ አልጄሪያ የማምራት ዕድል እየጠበበ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የተጫዋቹን ዝውውር በመጥለፍ ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ንግግር እያደረጉ መሆኑን ስንገነዘብ ፋሲል ከነማም ተጫዋቹን ዳግም የግሉ ማድረጊያ ዕድል እንዳለው ሰምተናል።

የፋሲል ከነማ ሥራ-አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሙጂብ ያለውን የአንድ ዓመት ውል በማቋረጥ ወደ አልጄሪያ ለመጓዝ ከፋሲል ከነማ ጋር ሲደራደር ምናልባት ከጄ ኤስ ካቢሌ ጋር ሳይስማማ ቀርቶ ሀገር ውስጥ የሚቀር ከሆነ በቅድሚያ ለፋሲል ከነማ ለመጫወት እንደተስማማ ነግረውናል። እንደ አብዮት ገለፃ ከሆነ ተጫዋቹ በቃል የተገደበ ስምምነት ብቻ ሳይሆን በወረቀት የሰፈረ “ቅድመ ሁኔታ” ላይም ስምምነት እንደፈፀመ አመላክተውናል።

አሁን ላይ እንደሚሰሙ መረጃዎች ከሆነ ደግሞ የሙጂብ የአልጄሪያ ጉዞ እውን የመሆኑ ዕድል እየተመናመነ ይገኛል። ይህንን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰበታ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጫዋቹን ለማስፈረም ጠንከር ያለ ንግግር ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ምናልባት ውዝግቦች እንደሚኖሩት የሚጠበቀው የተጫዋቹ እና የቀጣይ ማረፊያው ጉዳይን ጨምሮም የተጫዋቹን ሀሳብ ድረ-ገፃችን እየተከታተለች የምታቀርብ ይሆናል።