የወጣቱ አጥቂ ዝውውር አልተሳካም

ከሳምንት በላይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያደርገው የነበረው ዝውውር በእንጥልጥል የቆየው የወጣቱ አጥቂ ጉዳይ እንዳልተሳካ ተሰምቷል።

በኢትዮጵያ መድን ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡደን ድረስ መዝለቅ የቻለውን ወጣቱ አጥቂ መሐመድኑር ሀሰን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየቱ ተጫዋቹ በኢትዮጵያ መድን ያለውን ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት ማፍረሻ የተጠየው አምስት መቶ ሺህ ብር እስኪከፈል ድረስ የዝውውር ሂደቱ እንዲዘገይ ሆኖ ነበር።

የዝውውር ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ቢሸፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው አካዳሚ በመግባት ከቡድኑ ጋር እየተዘጋጀ የቆየው መሐመድ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሮም ነበር።

በቅርቡ ወደ ፈረሰኞቹ የሚያደርገው ዝውውር ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም ተጫዋቹ በትናትናው ዕለት ቡድኑ ካረፈበት ካምፕ በመውጣት ወደ አዲስ አበባ መመለሱ እና ዝውውሩ አለመሳካቱን ሰምተናል።

ይህን ተከትሎ መሐመድ ኑር ምን አልባት በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሊያመራ እንደሚችል ሰምተናል።