የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0-3 ደደቢት – ታክቲካዊ ትንታኔ

ሚልኪያስ አበራ

 

በአለም እግርኳስ በትልቅ ደረጃ የሚገኙ ቡድኖች በአጨዋወት ዘይቤያቸው የብቸኛ አጥቂን ሚና በመውሰድ በ4-4-2 ፎርሜሽን ላይ ጀርባቸውን ከሰጡ የሰነበቱ ይመስላሉ፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ በሁለት የተለያየ ሚና ያለቸው የመሃል አጥቂዎች የሚጫወቱ ትልልቅ ቡድኖች ቢታዩም ታክቲካዊ አቀራረባቸው የቀድሞውን classic 4-4-2 አመላካች አይደለም፡፡

በቅርብ አመታት ታላላቅ ቡድኖች 4-4-2ን በተለያየ መንገድ እና ታክቲካዊ ይዘት ሲተገብሩ ተመልክተናል፡፡ የ4-4-2 ፎርሜሽን ዋነኛ ድክመት ተደርጎ የሚታየው በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሁለት ተጫዋቾችን (ብዙውን ጊዜ ወደ ተከላካይ ክፍሉ የቀረቡ የተከላካይ አማካዮች) ስለሚያሰልፉ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም በ4-3-3 ፣ 4-2-3-1 ፣ 3-5-2 እና ሌሎች መሰል ፎርሜሽኖች የመሃል ሜዳ የቁጥር ብልጫ ይወሰድበታል ከሚል እሳቤ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4-4-2ን መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ አብዛኛውን ግዜ የሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች በሁለት የተከላካይ አማካዮች እና በሁለት የመስመር አማካዮች እንዲሁም ሁለት ተመሳሳይ የሜዳ ላይ ሚናን በሚተገብሩ የሳጥን አጥቂዎች የሚገነባው 4-4-2ን ይጠቀማሉ፡፡

በደደቢት አሰልጣንነታቸው የመጨረሻ የሆነውን ጨዋታ ያካሄዱት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም 4-4-2ን ሌሎቹ የሊጉ አሰልጣኞች ከሚጠቀሙበት ዘይቤ በተለየ ተግብረውታል፡፡

በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ወጥ አቋም ሲያሳይ የተስተዋለው ንግድ ባንክ በ4-1-4-1 (በአንዳንድ አጋጣሚዎች 4-2-3-1) ተግብሯል፡፡

(ምስል 1)

በታዲዮስ እና የአጥቂ አማካዮቹ መካከል የነበረው ክፍተት

በ4-1-4-1 ፎርሜሽን የተከላካይ አማካዩ የሚሸፍነው የሜዳ ክፍል ሰፊ ነው፡፡ በእለቱ ጨዋታ የንግድ ባንኩ አምበል ታደዮስ በሜዳው ቁመትም (vertically) ሆነ በአግድሞሽ መስመር (laterally) ያለውን ሰፊ ክፍተት እንዲሞላ ሲገደድ ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በ4-2-3-1 ከጎኑ ይሰለፍ የነበረው እና ሚናውን የሚጋራለት ደረጄ መንግስቴ በዚህኛው ጨዋታ ይበልጥ ከፊቱ ላሉት የማጥቃት አማካዮች በቀረበ ቦታ ላይ መጫወትቱ ከታዲዮስ ፊትና በጎን (በሁለቱም መስመሮች) ሰፊ ክፍተትን የፈጠረ ነበር፡፡ ታዲዮስም ወደኋላ በማፈግፈግ በመሃል ተከላካዮች መካከል እየተገኘ የፉልባኮቹን ወደፊት መሄድ ተከትሎ በመሃል ተከላካዮች እና ፉልባኮች መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት (channels) ለማጥበብ (ultra-defending system) የሚተጋበት ሰአት በመበራከቱ ከአጥቂ አማካዮቹ ጋር ያለው ርቀት የበለጠ ሲለጠጥ ታይቷል፡፡ በንግድ ባንክ የማጥቃት አጨዋወት (attacking phase) ላይ ካፈገፈገበት ቦታ ተነስቶ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ወደ ፊት ሲሄድ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ለመድረስ የሚወስድበት ጊዜ አና የሚሸፍነው ርቀት ብዙ ነበር፡፡

ደደቢቶች በፈጣን የመስመር አማካዮቻቸው እገዛ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረገው የመስመር ሽግግር (flank attacking transition) ለመከላከል ወደ ሁለቱም ጎኖች በሚያደርገው እንቅስቃሴ እና በሚሸፍነው ቦታ ከወትሮው በተለየ ተዳክሞ ታይቷል፡፡

ተክሉና ዋለልኝም የተጋጣሚን የመስመር የማጥቃት አጨዋወት ለመግታት እንዲሁም ወደ ፊት የሄዱ ተመላላሽ ተከላካዮቻቸውን ክፍተት ለመዝጋት በማያስችላቸው የቦታ አያያዝ (positioning) አብዛኛውን ጊዜ በማሳለፋቸው የመስመር ተከላከዮቹ አዲሱ እና አለምነህ በተደጋጋሚ ለሳኑሚ እና በረከት ተጋላጭ ሲሆኑ ታይቷል፡፡

በ7ኛው ደቂቃ ላይ ሳኑሚ ያስቆጠራት ግብ የዚህ ድክመት ማሳያ ልትሆን ትችላለች፡፡ ሳኑሚ በግራ መስመር ከባንኩ የቀኝ ፉልባክ (አዲሱ) ጀርባ ከመገኘቱ በፊት የጨዋታው የእንቅስቃሴ ትኩረት በሙሉ በደደቢት ቀኝ መስመር ነበር፡፡ ይህም የባንኮችን የተከላካይ መስመር ትኩረት ወደ ግራው እንዲያዘነብል አድርጎታል፡፡ ወደ ክፍት ቦታው የተላከውን ኳስም ሳኑሚ ወደ ግብነት ቀይሮታል፡፡

(ምስል 2)

22

የደደቢት የፊት መስመር ተሰላፊዎች ተደጋጋሚ የቦታ እና ሚና ቅይይር

በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ የፊት መስመር ተሰላፊነትን (forwards) ሚና በቋሚነት (ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ) የያዘ የደደቢት ተጫዋች አልነበረም፡፡ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ዳዊት እና በረከት ፣ ቀጥሎ ሳሚ እና ዳዊት ከዚያም በረከት እና ሳኑሚ በሚናው ተፈራርቀውበታል፡፡

ሂደቱ ሶስቱም ተጫዋቾች ከመስመር እየተነሱ የማጥቃት አጨዋወትን ለመተግበር የሚያስችል ባህርይ ከመላበሳቸው ጋር በመሆኑ ስኬታማነቱ ጎልቶ ታይቷል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት ይህንን አቅደውበት እንደገቡና ለተጫዋቾቹም ይህንን እንዲተገብሩ ማዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ሂደቱ ሶስቱም ተጫዋቾች ከመስመር እየተነሱ የማጥቃት አጨዋወትን ለመተግበር የሚያስችል ባህርይ ከመላበሳቸው ጋር በመሆኑ ስኬታማነቱ ጎልቶ ይታያል፡፡ በዚህ የአቀራረብ ስልት የንግድ ባንክን ጠንካራ እና የተደራጀ የመከላከል መስመር ሲፈትኑትና ውህደቱንም ሲሰብሩት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ በሚፈጥሩት የቦታ እና የሚና ለውጥ የባንክን ሁለት የመሃል ተከላካዮች (ቢንያም እና አቤል) የተሳካ ጥምረት ሲያከሽፉ ከመታየታቸውም ሌላ አጠቃላይ የንግድ ባንክን የመከላከል አደረጃጀት (defending organization) የትኩረት አቅጣጫ ያስቀየረ ነበር፡፡ ዘዴው ራሳቸውን ከመከላከል ስልት ነፃ እንዲሆኑ እና በተለያዩ መስመሮች የሚፈጠሩ ክፍተቶችን እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል፡፡

የባንክ ፉልባኮች (አዲሱ እና አለምነህ) በደደቢቶቹ የመስመር ተሰላፊዎች ወደ መሃለኛው የሜዳ ክፍል ገብቶ ማጥቃት (cut inside) የሚፈጠርላቸውን ክፍተት ተጠቅመው ወደ ፊት ሲሄዱ ኳላ የሚተዉትን ክፍተት በአግባቡ እና በፍጥነት ሲሸፍኑ አልታዩም፡፡ ይህም ደደቢቶች በ final third የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው በተለይ በሜዳው የጎንዮሽ ክፍል ሰፊ የመጫወቻ ቦታ እና የማሰብያ ግዜን አስገኝቶላቸዋል፡፡

ሁለቱም ፉልባኮች በተመሳሳይ ግዜ የፊት ለፊት ሩጫን ስለሚያድጉ ሁለቱን የመሃል ተከላካዮች ለሁለት የደደቢት የፊት አጥቂዎች ያጋልጡ ነበር፡፡ ይህም በንግድ ባንክ የአደጋ ክልል የ 2ለ2 ግንኙነቶችን በተደጋጋሚ እንድናስተውል አድርጎናል፡፡ ይህ ሌላኛው የንግድ ባንክ የተከላካይ ክፍል የውህደት እና የመናበብ ችግርን ያጋለጠ ነው፡፡

(ምስል 3)

33

የሁለተኛው አጋማሽ ለውጦች

ደደቢቶች በዚህኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ የበለጠ የመሃል ክፍሉ ላይ የሚገኘውን ክፍተት ለመጠቀም የተጫዋቾች እና የቅርፅ ለውጥ አድርገው ቀርበዋል፡፡ ሰለሞን ወጥቶ ሳምሶን ሲተካ ወደ 4-1-3-2 ያመዘነ መዋቅር (አደራደር) ታየ፡፡ ሳምሶን ከሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ በመገኘት የቡድኑን የማጥቃት ምስረታ (attacking buildup) ከመስመሮች ወደ መሃከለኛው የሜዳ ክፍል ቀይሮታል፡፡ ዳዊት እና ሳኑሚን ከታደለ እና በረከት እንዲሀም ከጋብሬል ጋር የማገናኘት ስራ ሲሰራም ነበር፡፡ በረከትም የባንኩን ፉልባክ (አዲሱ) የፊት ለፊት ሩጫ የመግታት ኃላፊነትን መወጣት ጀመረ፡፡

ወደቀኝ መስመር ያጋደለው የማጥቃት እንቅስቃሴም በ58ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፈራ፡፡ ዳዊት ከቀኝ መስመር ወደ ባንክ farpost የላካትን ኳስ በረከት አስቆጥሮ ደደቢት 2-0 መምራት ቻለ፡፡ በጥሩ ሁኔታ ያለተዘጋጀው እና ተደጋጋሚ ጫና ሲደርስበት የነበረው የባንክ የተከላካይ ክፍል እንደወትሮው ጠንካራ ላለመሆኑ ይህም ግብ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

በዚህኛው የጨዋታ ክፍል ጊዜ ንግድ ባንኮች የተጫዋች ለውጥ ቢያደርጉም በቡድኑ ላይ የቅርፅ ለውጥ አላመጣም፡፡ አብዱልከሪም ተክሉን ተክቶ በቀኝ መስመር የአጥቂ አማካይነትን ያዘ፡፡ ከሪም ብርሃኑ ቦጋለን በራሱ ይግብ ክልል እንዲቀር በማድረግ (stifle በማድረግ) በቀኝ መስመር ቡድኑ አጥቶት የነበረውን ስፋት (width) ማስገኘትና የመቀባበያ አማራጮችን ማስፋት ቢችልም እጅግ ተጠቅጥቀው በሜዳው ቁመት አጥብበው ወይም ተቀራርበው (vertically solid) ሲከላከሉ የነበሩትን የደደቢት ተከላከዮች ማስከፈት አልቻለም፡፡

ባንኮች የመሃል ሜዳ ተሰላፊዎቻቸውን ጨምረው የበለጠ ወደፊት ተጠግተው በተጋጣሚ ሜዳ የአደጋ ክልል ላይ የቁጥር ብልጫ በመውሰድ ውጤት ለመቀየር ሞክረዋል፡፡በ54ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ከቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ ጫላ በግንባሩ በመግጨት የግብ ሙከራ ቢያደርግም የደደቢትን ተከላካይ የሚፈትን ተጨማሪ የግብ ሙከራ እና እንቅስቃሴ አላደረጉም፡፡በዚህ ሂደት በ90ኛው ደቂቃ በዳዊት ፍቃዱ ተቀይሮ ወደሜዳ የገባው ሽመክት ጉግሳ ከግራው መስመር ሳጥን ጠርዝ አክርሮ የመታት ኳሰ ግብ ሆና ደደቢት በ3-0 ውጤት ጨዋታውን ጨርሷል፡፡

44

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *