በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና እና ናይጄሪያዊው ግብ ጠባቂ ፊበርሲማ ኔልሰን ለመለያየት ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ ከወልቂጤ ከነማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ክለቡን የተቀላቀለቀው ፊበርሲማ በክለቡ በደል እንደደረሰበት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡
“ክለቡ ምግብ እንዳልበላ እና ልምምድ እንዳልሰራ ከልክሎኛል፡፡ ይባስ ብሎ ከታክስ የተጣራ 2500 ብር ደሞዝ አልከፈሉኝም፡፡ ስለዚህም ክለቡ ከሀዋሳ ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ከቡድኑ ጋር ለመጓዝ ፍቃደኛ አልነበርኩም፡፡” ሲል ፊበርሲማ ተናግሯል፡፡
ፊበርሲማ ለቀድሞ አሰልጣኙ ጥላሁን መንገሻ ያለውን አድናቆት ገልጶ ከክለቡ የተሻለ እንክብካቤ ሊሰጠው ይገባ እንደነበር ተናግሯል፡፡
“ከአሰልጣኝ ጥላሁን ጋር ጥሩ መግባባት ነበረን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሰለጡኝ አሰልጣኞች መካከል ምርጡ እርሱ ነው፡፡ ተመልከት ከአሰልጣኜ ጋር የተሻለ ግንኙነት ነበረኝ፤ በክለቡ ግን ስርዓት አልበኛ ነህ ተብዬ መፈረጄ አግባብ አልነበረም፡፡ ሌሎች ክለቦች ከውጪ ላመጡቸውን ተጫዋቾች ከፍተኛ እንክብካቤ ያደርጋሉ ለኔ ግን ይህንን እንክብካቤ ተነፍጊያለው፡፡ ከአዳማው ጨዋታ በኃላም የመሰለፍ እድልን ያለበቂ ምክንያት አጥቺያለው፡፡ ነገር ግን ለክለቡ ደጋፊዎች ያለኝ ፍቅር የተለየ ነው፡፡”
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሙልጌታ ደሳለኝ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ልክ ነው ልጁ ከክለቡ የልቀቁኝ ደብዳቤ አስገብቷል፡፡ ይህ ችግር የተፈጠረው አሁን አይደለም፤ ከወራት በፊት ነው ችግሮች የተፈጠሩት፡፡ ልጁ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ምግባር ችግር አለበት፡፡ በተደጋጋሚ ከተጫዋቾች ጋር ይጣላል፣ ይደባደባል፡፡ ስናመጣው በአሰልጣኞች ዕምነት ስላገኘ ነበር፡፡ ስለስነ-ምግባሩ በተመለከተም ልናርመው ደጋግመን ሞክረናል፡፡ የተለያዩ ቅጣቶችንም ቀጥተነዋል ደሞዝ መቁረጥን ጨምሮ፡፡ ቢሆንም ሊታረም አልቻለም፡፡ ሲጀመር የልጁ አዕምሮ ልክ አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከልጁ ጋር የመቀጠል ምንም ፍላጎት የለውም፡፡ ወደፈለገው ክለብ መሄድ ይችላል፡፡” በማለት የክለቡን አቋም አስረድተዋል፡፡