የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች የሚደረግባቸው ሜዳዎች ተመረጡ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች የሚደረጉበት ስታዲየሞች ተለይተው ታውቀዋል፡፡

የ2014 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሦስት ምድቦች በ36 ክለቦች መካከል (ሁሉም ክለቦች ከተሟሉ) እንደሚደረግ ሰጠበቅ የፊታችን ረቡዕ የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓቱ ይከናወናል። ባለፈው ዓመት የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ በተመረጡ ቦታዎች የተካሄደው ውድድሩ ዘንድሮም በዚሁ የሚቀጥል ሲሆን የውድድሩ ኮሚቴም በአንደኛው ዙር እንዲካሄድባቸው ሦስት ሜዳዎችን መምረጡን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

ኮሚቴው በመቀነስ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ጋር ስታዲየሞችን ከገመገመ በኋላ ለመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች የሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ፣ ሆሳዕና የሚገኘው አቢዮ አርሳሞ ስታዲየም እና የጅማ ስታዲየሞች ተመርጠዋል።

በተያያዘ የከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊዎችን በተመለከተ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአካባቢው ክለቦች ስለመሳተፍ አለመሳተፋቸው በቀጣይ በሚኖረው የኮሚቴው ስብሰባ እና የክለቡቹ ምርጫ ተጨምሮበት ውሳኔ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።