የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስአበባ ከተማ 2-1 ፋሲል ከነማ

አዲስ አበባ ከተማዎች ሳይጠበቁ ፋሲል ከነማን ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ደምሰው ፍቃዱ – አዲስአበባ ከተማ

ስለቡድናቸው እንቅስቃሴ

“እስካሁን ድረስ በጥሩ እና በምንፈልገው መንገድ እየሄደልን ይገኛል።”

በተከታታይ የተቆጠሩት ግቦች ስለነበራቸው ጥቅም

“በእርግጥ በስነልቦና ረገድ ጥሩ ጥቅም አላቸው ነገርግን የእኛ ቡድን ስነልቦናው ከፍ ያለው መከላከያን ያሸነፍንበት ወቅት አንስቶ ነው የዛሬዎቹም ግቦች ይበልጥ እንድንነሳሳ አግዘውናል።”

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከልን ስለመምረጣቸው

“ጉጉትም አለ ተጋጣሚያችንም ደግም ሻምፒዮን የነበረ ሊጉን የሚመራም እንደመሆኑ እዚህ ቡድን ላይ ሁለት ግቦች ማስቆጠር የሚፈጥረው ስለዚህ ሁለት አይነት ነገር ይዘን ነበር የገባነው ጎላችንን ማስጠበቅና ተጨማሪ ግብ ከተገኘ ማስቆጠር ነበር።”

ስለቆይታው

“በእርግጥ ሦስት ጨዋታ ነበር የተሰጠኝ። እንግዲህ እስካሁን ሁለት አሸንፊያለሁ ቀሪ አንድ ነው የሚጠበቅብኝ።”

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

አስቀድመው ስለተቆጠሩባቸው ግቦች

“እግርኳስ ጨዋታ ላይ አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቁ ነገሮች ይከሰታሉ፤ ትልቁ ነገር በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች የነበረን አጀማመር ጥሩ ነበር። ከዛ በኃላ ግን እንዲጫወቱ ፈቅደንላቸዋል። የተቆጠሩትም ግቦች የራሳችን የአቋቋም እና የአደረጃጀት ችግሮች ናቸው። በሁለተኛው አጋማሽ ቅያሬዎችን አድርገን የተለየ ነገር ለማድረግ ሞክረናል ነገርግን ያንን ነገር ማስቀጠል አልቻልንም መቻኮሎች ነበሩ በቀጣይ ስህተቶቻችን እያረምን በጉዳት ያጣናቸው ልጆችም ሲመለሱ ይበልጥ ተሻሽለን እንቀርባለን።”

በተጋጣሚ ስለተወሰደባቸው ብልጫ

“በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ቡድናችን ለሁለት የተቆረጠ ነበር ይህም እነሱ በነፃነት እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል ያ ችግር ፈጥሮብናል በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻለ መጠቅጠቅ ነበረን። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥሩ ነገሮች ነበሩን።”

ሰለሽንፈቱ ተፅዕኖ

“ውድድሩ 30 ጨዋታ ነው ከመጀመሪያው ከፍ ዝቅ መኖሩ ብዙም ችግር አይኖረውም እየተስተካከለ የሚሄድ ነው። ጉዳት ላይ ያሉ ተጫዋቾች አገግመው በጥሩ ብቃት ሲመለሱ ደግሞ ይበልጥ የተሻልን እንሆናለን።”