ከፍተኛ ሊግ | ቡራዩ ከተማ የነባሮቹን ውል ሲያራዝም አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ወደራቀበት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዳግም የተመለሰው ቡራዩ ከተማ የነባር ተጫዋቾችን ውል ሲያራዝም የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።

በ2013 የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድርን ሻምፒዮን በመሆን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጉን ያረጋገጠው ቡራዩ ከተማ ከዘንድሮ ዓመት ውድድር ራሱን አጠናክሮ ለመቅረብ የተለያዩ ተግባራቶችን ፈፅሟል። የዋና አሰልጣኝ መኮንን ማሞን ጨምሮ የረዳት አሰልጣኙ ጳውሎስ ፀጋዬን ቆይታ ለአንድ ዓመት ውል ያደሰው ክለቡ የአስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቅ የአስራ አምስት ተጫዋቾችን ውልም ለተጨማሪ ዓመት አድሷል።

በጅማ አባ ቡና ጅማ አባ ጅፋር ሲጫወት የምናቀው የፊት አጥቂው ቴዎድሮስ ታደሰን ጨምሮ አይችሉም (ግብጠባቂ ከዳሞት)፣ ኢብሳ አበበ (ግብጠባቂ ከአዳማ)፣ አማኑኤል ጌታቸው፣ (ተከላካይ ከጅማ አባ ጅፋር)፣ ታመነ ቅባቱ (ተከላካይ ከለገጣፎ)፣ ጥላሁን (ተከላካይ አዲስ ከተማ)፣ ጴጥሮስ ጥላሁን (አማካይ ከኤጀሬ ከተማ)፣ ቶሎሳ ንጉሤ (አጥቂ ከመድን)፣ ደረጄ ነጋሽ (አጥቂ ከዳሞት) እና ሀብታሙ (አጥቂ ከለገጣፎ) ለክለቡ የፈረሙ አዳዲስ ተጫዋቾች ነው።

በ2014 የውድድር ዘመን ምድብ ለ ላይ የተደለደለው ቡራዩ ከተማ ቅድመ ዝግጅቱን በባቱ ከተማ ማድረግ የጀመረ ሲሆን የተወሰኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን በማድረግ ለዋናው ውድድር ወደ ሀዋሳ ከተማ እንደሚያቀና ሰምተናል።