\”ከ120 ሚሊየን ህዝብ በላይ ወክለን ነው የመጣነው ፤ ስለዚህ ምንም አይነት ፈተና ቢገጥመን ምክንያት ይሆነናል ብዬ አላስብም\” ቢኒያም በላይ

ምሽት 5:30 ጊኒ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከመግጠሟ በፊት የዋልያዎቹ ተጫዋች ቢኒያም በላይ ስለጨዋታው ተከታዩን ብሎናል።

\"\"

ለጊኒው ጨዋታ ያለፉት ቀናት ልምምድ ምን ይመስል ነበር ?

ዝግጅታችን መልካም ነበር። ሀገራችን ላይ የተወሰኑ ቀናትም ቢሆን አንድ ላይ ተሰባስበን ዝግጅታችንን ማድረግ ችለናል። ይህ ጊዜ ግን በቂ ነበር ብዬ አላስብም። በግሌ የዝግጅቱ ቀን አጥሯል ብዬ አስባለሁ። ይህ ቢሆንም አንድ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገናል። ጨዋታው ለእኛም እንደ ተጫዋች ለአሠልጣኞቹም ቡድኑ የቱ ጋር እንዳለ ያሳያል ብዬ አስባለው። ይሄንን በመጠቀም ጥሩ ነገር ታይቷል ብዬ አስባለው። አሁን ደግሞ ወደ ሞሮኮ መጥተን ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው። ትንሽ መንገድ ላይ ከ24 ሰዓታት በላይ በመጓዛችን ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። ግን ይህ ቢሆኑም ቡድኑ ጥሩ የዝግጅት ጊዜ ነው ያሳለፈው ፤ ጥሩ መንፈስ ላይም ነው የሚገኘው።

ከጉዞ መርዘም እና ከዝግጅት ጊዜ ማጠር አንፃር ወሳኙን ጨዋታ ስለሚከውኑበት መንገድ…

እኛ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ነን። ከ120 ሚሊየን ህዝብ በላይ ወክለን ነው የመጣነው ፤ ስለዚህ ምንም አይነት ፈተና ቢገጥመን ምክንያት ይሆነናል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ያንን የሚያክል ህዝብ የወከለ ሰው በተለያዩ ነገሮች ወደ ኋላ ይቀራል ብዬ አላስብም። ስለዚህም ጥሩ ነገር ሰርተን የተሻለ ነገር ይዞ መመለስ ነው ሀሳባችን።

በግልስ ከቢኒያም ምን እንጠብቅ ?

ይሄ ቡድን ሲሰራ እንደቡድን ነው የተሰራው። ብሔራዊ ቡድናችን ላይ የግል ተጫዋች ላይ እንደዚህ ብለን የምንጠብቀው ነገር የለም። ሁላችንም ስናወራና ከአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ የሚሰጠን ነገር በህብረት ለቡድናችን እና ለሀገር ይዘን መሄድ እንዳለብን ነው። እኔም እንደ ቡድኑ አባል የሆነ ጥሩ ነገር ለሀገር ይዘን እንሄዳለን ብዬ አስባለው።

\"\"