ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 ከሐብታሙ “ጠፋኸኝ” ወደ ሐብታሙ ገዛኸኝ

በ2010 የውድድር ዘመን ደቡብ ፖሊስን ለቆ ሲዳማ ቡናን ከተቀላቀለ ወዲህ ፈጣን እምርታን በማሳየት በሊጉ ከመደርደርያው አናት ከሚቀመጡ የመስመር አጥቂዎች መካከል የነበረው ሐብታሙ አምና እና ዘንድሮ እያሳየን የሚገኘው ብቃት ግን ፍፁም የወረደ መሆኑን ስንታዘብ ቆይተናል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ወላይታ ድቻን ሲረታ የተመለከትነው ሐብታሙ ገዛኸኝ ግን የቀደመውን ማንነቱን ያስታወሰን ነበር። የሽግግሮች ተጫዋች የሆነው የመስመር አጥቂው ወላይታ ድቻዎች ላይ የመጀመሪያዋን ግብ ከማስቆጠሩ ባለፈ በሁለተኛዋ ግብ ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎን ማድረግ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ኳስ በግቡ ቋሚ ሲመለስበት በአንድ አጋጣሚ ደግሞ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ እንደምንም ያዳነበት ያመከነበት ተጠቃሽ ሙከራዎቹ ነበሩ።

በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው ሐብታሙ ሁኔታዎችን እየተገነዘበ ከተከላካዮች ጀርባ ያደርጋቸው የነበሩ አፈትላኪ ሩጫዎች እጅግ አደገኛ ነበሩ። ከአዲስ ግደይ መልቀቅ በኋላ ሁነኛ የፊት መስመር ተጫዋች ያጡት ሲዳማ ቡናዎች ከሐብታሙ ገዛኸኝ ብዙ ቢጠብቁም ከተጫዋቹ ይህን ማግኘት ሳይችሉ ቆይተዋል። ምናልባት የወላይታ ድቻው ጨዋታ ያሳየን እንቅስቃሴ የቀደመውን ሐብታሙ ፍንጭ የሰጠ መሆኑ የክለቡ ሰዎች ተስፋ እንዲጥሉበት የሚያደርግ ሆኖ አልፏል።

👉 ለሲዳማ ቡና ችግር መፍትሄ የሰጠው ደግፌ ዓለሙ

የአማኑኤል እንዳለን መጎዳት ተከትሎ በቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራ ተተኪ ተጫዋች አጥተው የቆዩት ሲዳማ ቡናዎች በደግፌ ዓለሙ በኩል መልስ ያገኙ ይመስላል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት በተለይ የቀኝ መስመር የተከላካይ ስፍራን የማጠናከር ፍላጎት የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች ይህ ጥረታቸው አለመሳካቱን ተከትሎ በቦታው አማኑኤል እንዳለ ውጪ ያለ ተፈጥሮአዊ አማራጭ ውድድሩን መጀመራቸው ይታወቃል።

በዚህ መልኩ ወደ ውድድር ገብተው በ6ኛው ሳምንት ብቸኛ ተመራጭ የቀኝ መስመር ተከላካያቸው ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ ቦታውን ለመሸፈን ተቸግረው ቢቆዩም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትነው ደግፌ ፍቃዱ ለቦታው የሚመጥን አቅም እንዳለው ማስመስከር ችሏል።

ከሲዳማ ቡና የ23 ዓመት በታኝ ቡድን የተገኘው ደግፌ ተፈጥሮአዊ የመጫወቻ ቦታው የመስመር አጥቂ ቢሆንም በቦታው የአማራጭ እጥረት የገጠማቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ተጫዋቹን ወደ ኋላ ስበው በመስመር ተከላካይነት የተጠቀሙበት ሲሆን ተጫዋቹም ጥሩ የሚባል እንቅሰቃሴ ማድረግ ችሏል።

በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት በነበረው የበላይነትም ሆነ ለማጥቃት በነበረው ተነሳሽነት እና ፍጥነቱ ተጫዋቹ ለአሰልጣኝ ገብረመድህን በቀጣይ አማራጭ ሊፈጥርላቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 በቀድሞ የቡድን አጋሮቹ የተከበረው እያሱ ታምሩ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡናው ተጫዋች እያሱ ታምሩ በአዲሱ ክለቡ ሀዲያ ሆሳዕና መለያ ኢትዮጵያ ቡናን በተቃራኒ በገጠመበት የመጀመሪያው ጨዋታ በቀድሞ የቡድን አጋሮቹ ስጦታ ተበርክቶለታል።

የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በስብስባቸው ውስጥ በነበረበት ወቅት በክለቡ መለያ የተነሳቸው ፎቶዎች ያረፉበትን ምስል በስጦታ ያበረከቱለት ሲሆን ፤ ከተጫዋቹ ጋር በጋራ በመሆንም የቡድን ፎቶ ተነስተዋል።

በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ካደረጉት ጨዋታ መጀመር በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቡድን አባላት በቅርቡ ለተሞሸረው እና የመጀመሪያ ልጁን እየተጠባበቀ ለሚገኘው ሄኖክ አዱኛን የማስታወሻ ስጦታ አበርክተውለታል።

👉 ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ተመልሷል

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ጅማ አባ ጅፋርን የተቀላቀለው ዳዊት እስጢፋኖስ በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ በተሸነፈበት ጨዋታ በተመለከተው የቀይ ካርድ መነሻነት በተላለፈበት ቅጣት ከጨዋታ ርቆ ቢቆይም በ9ኛ ሳምንቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በገጠመበት ጨዋታ ተሰልፎ መጫወት ችሏል።

በሀዋሳው ጨዋታ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቶ በተጠባባቂ ወንበር የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ በአንድ ኳስ አቀባይ ታዳጊ ላይ የፕላስቲክ ውሃ ጠርሙስ መወርወሩን ተከትሎ የጨዋታ አልቢትር በነበሩት ኃይለየሱስ ባዘዘው ቀጥታ ቀይ ካርድ የተመለከተ ሲሆን ሂደቱን የገመገመው የዲሲፕሊን ኮሚቴም ዳኞችን አፀያፊ ስድብ ተሳድቧል በሚል የሰባት ጨዋታ እና ሰባት ሺህ ብር ቅጣት እንዳስተላለፈበት አይዘነጋም።

የሰባት ጨዋታዎች ቅጣቱን ያጠናቀቀው ዳዊት አሁን ላይ ምንም ድል ሳያስመዘግብ በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን ቡድኑን ከዚህ ስፍራ ለመላቀቅ በሚያደርገው ጥረት የግሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከቅጣት ወደ ሜዳ መመለሱ ለጅማ ጥሩ ዜና ሆኗል።

👉 በጉዳት እየፈተነ የሚገኘው ተካልኝ ደጀኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ የግራ መስመር ተከላካይ ተካልኝ ደጀኔ በሊጉ የቀደመ ብቃቱን ለማሳየት እየተቸገረ ይገኛል።

የቀድሞው የደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚታወሰው ተካልኝ ደጀኔ ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ ባለፉት ሁለት ዓመታት መነሻው ከነበረው አርባምንጭ ከተማ ጋር ቆይታ በማድረግ ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና መወጣትን ችሏል።

ሆኖም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን በፕሪሚየር ሊጉ ዳግም ራሱን እንዳያሳይ ጉዳት እያገደው ያለ ይመስላል። እስካሁኑ በሊጉ ጨዋታ በሚገባ ራሱን ለመግለፅ የተቸገረው ተካልኝ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመጨረስ እየተቸገረ ይገኛል። በዚህ ሳምንትም በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ቢካተትም ከግማሽ በላይ መቀጠል አልቻለም።

👉 ደረጄ ዓለሙ ከተጠባባቂነት ባለፈ ሚና ይወጣ ይሆን ?

በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ ከስምንት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫ የተጓዘው የቡድን ስብስብ አባል የነበረው ደረጀ ዓለሙ በክለብ እግርኳስ ህይወቱ ግን ባለፉት ዓመታት ከተጠባባቂ ግብ ጠባቂነት ያለፈ ሚናን ለመወጣት እየተቸገረ ይገኛል።

ከዳሽን ቢራ በኋላ ቆይታ ባደረባቸው ክለቦች በአውስኮድ ከነበረው ቆይታ ውጪ በፕሪሚየር ሊጉ ወልዲያ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ዘንድሮም በሚገኝበት ድሬዳዋ ከተማ ከተጠባባቂነት ውጪ በአስገዳጅ ሁኔታዎች ካልሆነ በግቡ ቋሚዎች መካከል በዋና ተመራጭነት ሲያገለግል አንመለከተውም።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 1-0 ሲረታ በአዲሱ ቡድኑ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው ደረጀ በተጋጣሚው ተደጋጋሚ ፈተናዎች ባይገጥሙትም የተሰነዘሩበትን ጥቂት አደገኛ አጋጣሚዎች በጥሩ ሁኔታ ማዳን ችሏል።

በአሰልጣኝ ዘማሪያም ዕምነት ተጥሎበት በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ይሰለፍ እንጂ የእስካሁኑ አካሄዱ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ግብ ጠባቂ የነበረው ደረጀ ዓለሙ በቋሚነት የመጫወት ዕድልን ማግኘት በሚችልባቸው ክለቦች መጫወት እየቻለ ከተጠባባቂነት የዘለለ ሚናን ወደ ማይወጣባቸው ክለቦች በመዘዋወር የእግርኳስ ህይወቱን እያባከነ ይሆን ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል

👉 የሙኸዲን እና ምንተስኖት የደስታ አገላለፅ

ድሬዳዋ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በረታበት ጨዋታ ብቸኛዋን ግብ ማስቆጠር የቻለው ሙኸዲን ሙሳ ደስታውን የገለፀበት መንገድ አስገራሚ ነበር።

እንየው ካሳሁን ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ሙኸዲን ሙሳ ወደ ቡድኑ ተጠባባቂ ተጫዋቾች በማምራት በቅርቡ የመጀመሪያ ልጁን እየተጠባበቀ ከሚገኘው የቡድኑ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ከሆነው ምንተስኖት የግሌ ጋር ደስታውን ሲገልፅ ተመልክተናል።

ከዚህ የደስታ አገላለጽ ጋር በተያያዘም ሙኸዲን ሙሳ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆኗል።

👉 ስንታየሁ መንግሥቱ እና ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ የተሻለ የውጤታማነት ጉዞ ባደረገባቸው ጨዋታዎች የስንታየሁ መንግሥቱ አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ወላይታ ድቻ ከሰሞኑ ውጤት ለማስመዝገብ በተቸገረባቸው ጨዋታዎች ስንታየሁ በጉዳት እና ተያያዥ ጉዳዮች በሚገባ ማገልግል ባለመቻሉ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ቡድን መቸገሩን እየተመለከትን እንገኛለን።

ለመከላከል ቅድሚያ በሰጠው የቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ ውስጥ በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ተጋጣሚን ለመጉዳት በሚያደርጋቸው ጥረቶች ውስጥ የስንታየሁ መንግሥቱ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። ለዚህም ቡድኑ እሱ በሌለባቸው ጨዋታዎችም ሆነ በጉዳት በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ ባልቻለባቸው ጨዋታዎች ከፊት ያለውን አስፈሪነት እያጣ ነው።

በመሆኑም በቀጣዮቹ የዕረፍት ጊዜያት የተጫዋቾቹን የጉዳት ሁኔታ በማጥናት የልምምድ እና የጨዋታ ደቂቃዎች ጫናን ማመጣጠን የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲሁም ሌሎች ከጉዳት ነፃ ሆኖ ሊቆይባቸው የሚችሉ መፍትሄዎችን ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ለማፈላለግ የማይዘይዱ ከሆነ ውድድሩ ከዕረፍት ሲመለስም የመቸገራቸው ነገር የሚቀር አይመስልም።