ጅማ አባጅፋር ሊጉ ሊጀምር 7 ቀን ሲቀረው ልምምድ ጀምሯል

በሜዳም ሆነ ከሜዳም ውጪ ችግር ላይ ያለ የሚመስለው ጅማ አባጅፋር ከሌሎቹ የሊጉ ክለቦች እጅግ ዘግይቶ ልምምድ መስራት ጀምሯል።

የአንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባጅፋር ዘንድሮን ጨምሮ ያለፉትን አራት ዓመታት በተለያዩ የአስተዳደራዊ ችግሮች እና የውጤት ማጣት ክፍተቶች እየተቸገረ እየተንገዳገደ እንደሆነ ይታወቃል። ዘንድሮም በዚሁ ችግሩ በቅርቡ ሥራ-አስኪያጅ እና የቡድን መሪ ቀይሮ ከሜዳ ውጪ ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል ቢጥርም ስር የሰደደ የሚመስለው ችግሩን ሙሉ ለሙሉ እስካሁን መቅረፍ አልቻለም። በሜዳ ላይም ማግኘት ከሚገባው 27 ነጥቦች አንዱን ብቻ በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።

ሊጉ ከብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መልስ ሲቀጥል ክለቡ ጠንክሮ በመምጣት ከሦስት ነጥብ ጋር ለመታረቅ ጠንካራ የዝግጅት ጊዜ ይኖረዋል ተብሎ ቢጠበቅም በተገላቢጦሽ ሊጉ ሊጀመር አንድ ሳምንት ብቻ ሲቀረው ልምምድ መስራት ጀምሯል። ከዚህ ቀደም ተጫዋቾች ጥር 1 ተሰባስበው ልምምድ እንዲሰሩ ዕቅድ ቢያዝም ጥሪ ሳይተላለፍ መቅረቱን እና የሦስት ወር ደሞዝ ለተጫዋቾቹ አለመግባቱን ዘግበን እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ባለንበት ሳምንት መጀመሪያ ግን ያሉትን ጥያቄዎች በከፊል መልሶ በዛሬው ዕለት ባልተሟላ ሁኔታም ቢሆን ዝግጅት ጀምሯል።

በሳምንቱ መጀመሪያ (ሰኞ) የአንድ ወር የተጫዋቾች ደሞዝ ከከፈለ በኋላ ትናንት እና ዛሬ ድሬዳዋ እንዲሰባሰቡ ጥሪ ያቀረበው ክለቡም ተጫዋቾች ትናንት ስፍራው ሲደርሱ ማረፊያ እንዳልተዘጋጀላቸው ለዝግጅት ክፍላችን ሲገልፁ ነበር። አመሻሽ ላይ ግን ጥሪውን ተከትሎ የተገኙት 9 ተጫዋቾች በጨረታ የተመረጠው ሆቴል እንዲያርፉ ተደርጓል። በዛሬው ዕለትም ሌሎች ተጫዋቾች ስፍራው የደረሱ ሲሆን ከሰዓት 9 ሰዓትም የመጀመሪያ ልምምዳቸውን በ19 ተጫዋቾች እንደሰሩ አውቀናል።

በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ጅማ እሁድ ጥር 22 ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የ10ኛ ሳምንት ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል።