የዋልያዎቹን የአሜሪካ ጉዞ በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል

👉”ወደ አሜሪካ የተደረገው ጉዞ የተሳካ ነበር” አቶ ባህሩ

👉”ይህ ጉዞ እንዲሳካ ላደረጉ አካላት ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው” ኢንስትራክተር ዳንኤል


👉”ጉዞው አርኪ ነበር” አቶ ዳዊት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የስምንት ቀናት የአሜሪካ የጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታዎችን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። ከ10 ሰዓት ጀምሮ በተሰጠው መግለጫ ላይ የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም እንዲሁም ጉዞውን ያዘጋጁት የሲ ጄ ኒው ማን ተወካት አቶ ዳዊት አርጋው ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በቅድሚያ ይህ የጉብኝት ጨዋታዎች እንዲሳኩ ላደረጉ አካላት ምሳጋና በማቅረብ ንግግራቸውን የጀመሩት ኢንስትራክተር ዳንኤል በአሜሪካ ያደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ በቀጣይ ላለባቸው የግብፅ ጨዋታ ግብዐት ለማግኘት፣ የተጫዋቾችን የራስ መተማመን ለማሳደግ እንዲሁም ተጫዋቾች በእንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገኙ ለማድረግ ጥቅም እንዳለው ገልፀዋል። ትልቁ አላማም ኢትዮጵያዊውያን ተጫዋቾች በሌሎች ሀገራት የሚጫወቱበትን ዕድል እንዲያገኙ እንደነበርና በዚህም ተጫዋቾች የመታየት ዕድል እንዳገኙ አመላክተዋል። በተጨማሪም ለአራት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ተመርጠው ሁለቱን ለማየት እንደተሞከረ ገልፀዋል። ሜዳ ላይም የተለያዩ የጨዋታ መንገዶችን እንደሞከሩ የተናገሩት አሠልጣኙ እንደ አሠልጣኝም ሆነ እንደ ቡድን ከወዳጅነት ጨዋታዎቹ ልምድ እንደወሰዱ ጠቅሰዋል።

በማስከተል መጠነኛ ገለፃ ያደረጉት አቶ ዳዊት ጉዞውን “አርኪ” በማለት ከገለፁ በኋላ ይህ የሙከራ ጉዞ ነው ብለው ከጠበቁት በላይ ግባቸውን አሳክተው እንደተመለሱ ገልፀው መድረኩን ለአቶ ባህሩ ለቀዋል።

አቶ ባህሩ ጉዞውን አሳክተው በመመለሳቸው ደስተኛ እንደሆኑ አውስተው ይህ ጉዞ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ታቅዶ እንደተደረገ ገልፀው በፌዴሬሽኑ ግምገማ ብሔራዊ ቡድኑ የተሳካ ቆይታ በአሜሪካ እንዳሳለፈ በአፅንኦት ተናግረዋል። በተለይም ወደ ስፍራው ሲጓዙ ለማሳካት አስበዋቸው የነበሩትን የማርኬቲንግ ስራ፣ የወዳጅነት ጨዋታዎች ጥቅም እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተደራሽ የማድረግ ስራ በዝርዝር በመጥቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከስታዲየም ትኬት ገቢ ጋር በተያያዘ በመጀመሪያው ጨዋታ 260 ሺ ዶላር እንደተገኘ ተናግረው ከማሊያ ሽያጭ ጋር በተገናኘ ግን ስኬታማ ስራዎችን እንዳልሰሩ ሳይሸሽጉ በመጥቀስ አሜሪካ ከሚገኙ ታላላቅ የቢዝነስ ተቋማት ጋር ግን ስምምነቶችን ለመፈፀም የሚያስችሉ ስራዎችን ሰርተው እንደመጡ አመላክተዋል። በጉዞ ሂደት በትልቁ ቡድኑን ሲደግፉ የነበሩት የዲሲ ዩናይትድ ባለ ድርሻ አቶ እዮብ ማሞ ጋር በቅርቡ ሌላ ስምምነት እንደሚፈራረሙም ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት እንደተገለፀው ዮሴፍ ታረቀኝ እና ብርሃኑ በቀለ በዲሲፕሊን ምክንያት ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የተደረገበትን ዝርዝር ሁኔታ ያስረዱት ዋና ሥራ-አስፈፃሚው ሁለት ሌሎች ሰዎች ወደ ሀገር ቤት ከቡድኑ ጋር እንዳልተመለሱም ይፋ አድርገዋል። በዚህም የትጥቅ ኃላፊው አቶ ኃይሉ እና ወጌሻው አቶ ሽመልስ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ከሆቴል መጥፋታቸው በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት አስረድተዋል። ግለሰቦቹ ከሆቴል ቢጠፉም ፓስፖርታቸው ግን በኢትዮጵያ እግርኳስ እጅ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በመግለጫው ላይ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን የወሰደው የዑመድ ኡኩሪን ጉዳይ በተመለከተ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኩል የተሰጠውን ምላሽ ከቆይታ በኋላ ይዘን እንቀርባለን።