ከፍተኛ ሊግ | የ4ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች 4ኛውን ሳምንት ሲያሳርግ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነጌሌ አርሲ የድል መንገዳቸውን ሳይስቱ ምድቦቻቸውን መምራት ቀጥለዋል።

ምድብ ‘ሀ’ ጨዋታዎች

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልድያ አገናኝቷል። በመጀመሪያ አጋማሽ ወልድያ በኳስ ቁጥጥሩ ተሽሎ ተገኝቶ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድረጓል። በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአጭር ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ በ20ኛው ደቂቃ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገኙትን የግብ ዕድል የፊት መስመሩ መሳይ ሰለሞን ወደ ግብ ቀይሯል። አጋማሹም በዚሁ መልኩ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጫና የበዛበት እና የመሸናነፍ አጨዋወት የታየበት ሆኗል። ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በ78ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋች የሆነው ሙሉቀን ደሳለኝ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ወልድያ ቀሪ ደቂቃውን የተጫዋች ብልጫ ወስዶ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረገ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ተስኖት ጨዋታው ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ የምድቡ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሩክ የመቶ ፐርሰንት ድሉን ማስቀጠል ችሏል።

ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው የኦሮሚያ ፖሊስ እና ነቀምቴ ከተማ ነው። በጨዋታው ጥሩ የሚባል እና ፈጣን እንቅስቃሴ ተመልክተናል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ረጃጅም ኳሶችን የመጠቀም ሂደት ሲታይ አጋማሹ በዚሁ ሂደት ያለግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጥሩ እና ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ የተመለከትንበት አጋማሽ ሆኗል። በ46ኛው ደቂቃ የነቀምቴ ከተማ ተጫዋች የሆነው  ሮሆቦት ስላሎ ከተሻጋሪ ኳስ ግሩም በሆነ አጨራረስ ግብ አስቆጠሯል። ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ግብ ለማስቆጠር ጥረት በማድረግ በ55ኛው ደቂቃ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ሽመልስ ቦጋለ ወደ ግብ መቀየር ችሏል ከግቡ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ አስመልክተውናል። በ77ኛው ደቂቃ ነቀምቴ ከተማ ያገኘውን የግብ ዕድል ሰለሞን ጌታቸው አስቆጥሯል። ጨዋታውም በነቀምቴ አሸናፊነት ተጠናቋል። በውጤቱም ነቀምቴዎች ሁለተኛ ደረጃቸውን በማስጠበቅ መሪውን በሦስት ነጥብ ርቀት መከተላቸውን ቀጥለዋል።

የእለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ሃላባ ከተማን ከይርጋ ጨፌ ቡና አገናኝቷል። በአጋማሹ ሃላባ ከተማ ጠንከር ባለው የፊት መስመሩ የይርጋጨፌ ቡናን የተከላካይ ክፍል ደጋግሞ ሲፈትሽ ተስተውሏል። በአንፃሩ ይርጋጨፌ ቡና መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። ሆኖም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስም ሀላባ ከተማ ይበልጥ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው የተጫወቱበት አጋማሽ ሆኗል። ይርጋ ጨፌ ቡና በአጭር ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ሀላባ ከተማ ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራ በኋላ በ70ኛው ደቂቃ ከማል አቶም ከርቀት አክርሮ በመምታት ግብ አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ በ74ኛው ደቂቃ ሀላባ ከተማ በፈጣን ሽግግር ያገኙትን ኳስ ፀጋ ከድር በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ መሪነቱን አጠናክሯል። ከግቧ በኋላ ሙሉ በሙሉ የሀላባ ከተማ የበላይነት የታየበት ጨዋታ በቡድኑ አሸናፊነት ተደምድሟል።

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው የጅማ አባቡና እና የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ ጥሩ ፉክክር አስመልክቶናል። እልህ እና ትንቅንቅ በበዛበት ጨዋታ ጅማ አባ ቡና አጭርን ከረጅም የቀላቀለ ቅብብል እና የአየር ኳሶችን ሲያዘወትር ተስተውሏል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ኳስን በመመስረት በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በግብ ሙከራው ረገድ ጅማ አባ ጅፋሮች ተሽለው ተገኝተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጅማ አባጅፋር ራሱን አጠናክሮ ተሽሎ የተገኘበት አጋማሽ ሆኗል። አባ ጅፋር ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አርገዋል። በ51ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ የጅማ አባ ጅፋሩ ተጫዋች ፊልሞን ገ/ፃድቅ በግሩም ሁኔታ አስቆጠሯል። በ74ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ቡና ግብ ለማስቆጠር ከርቀት የመታውን ኳስ የጅማ አባ ጅፋር ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮታል። የጨዋታው ማብቂያ ላይ ጅማ አባ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ተጠናቋል።

የምድብ ‘ለ’ ጨዋታዎች

3:00 ላይ ወሎ ከሞቦልቻን ከ ሸገር ከተማ ያገናኘው በድንቅ እንቅስቃሴ በታጀበው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ተሽለው እና ኳሶችን ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ወሎ ኮምቦልቻዎች ጨዋታው በተጀመረ በ12ኛው ደቂቃ ላይ ተካልኝ መስፍን የሸገር የተከላካይ መስመር ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት በመጠቀም ከመሃል ሜዳ አካባቢ አየገፋ በመሄድ ኳሱን ከመረብ ጋር አገናኝቶት ወሎ ኮምቦልቻዎችን መሪ እንዲሆኑ ማድረግ ችሏል።

በመልሶ ማጥቃት የአቻነት ግብ በተደጋጋሚ ሲፈልጉ የነበሩት ሸገር ከተማዎች እየተመሩ የቆዩት ለሰባት ያህል ደቂቃ ብቻ ሲሆን ወደተቃራኒ የግብ ክልል እየገፉ በመሄድ ላይ እያሉ በተሠራው ጥፋት ያገኙትን የቆመ ኳስ አስናቀ ተስፋዬ ወደግብ ክልል አሻምቶት መረቡ ላይ ሲያርፍ ጨዋታውም በአቻ ውጤት ወደመልበሻ ክፍል አምርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፍጹም የጨዋታ በላይነት የወሰዱት ሸገር ከተማዎች ተደጋጋሚ የግቢ ሙከራ ሲያደርጉ 80ኛው ደቂቃ ላይም ተሳክቶላቸዋል። ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ፋሲል አስማማው አስቆጥሮት ሸገር ከተማን ከመመራት ተነስቶ በ2-1 አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል። ሸገሮች ነገሌ አርሲን በሁለት ነጥብ ርቀት በመከተል ላይ ይገኛሉ።

ነጌሌ አርሲን ከደሴ ከተማ ባገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነጌሌ አርሲዎች 19ኛው ደቂቃ ላይ በርካታ የግብ ዕድሎችን ባገኘው አጥቂያቸው ታምራት አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ሲችሉ ደሴ ከተማዎች በአንጻሩ ግብ ከተቆጠረባችው በኋላ በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት የአቻነት ግብ ፍለጋ ቢታትሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይም በተለይ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ፀጋ ደርቤ በተደጋጋሚ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀማቸው የቀራቸው አጋጣሚዎች አስቆጪ ነበሩ። ድል የቀናቸው ነጌሌ አርሲዎች በአራት ጨዋታ ሙሉ 12 ነጥብ በመያዝ ምድቡን መምራት ቀጥለዋል።

8 ሰዓት ላይ ትልቅ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ባቱ ከተማ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

የአርባምንጭ የፊት መስመር በሙሉ ጨዋታው በርካታ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን ሳይጠቀም የቀረ ሲሆን ባቱ ከተማ በአንጻሩ በዛሬው ጨዋታ የተከላካይ መስመራቸው ጠንካራ ሆኖ ተስተውሏል። ሆኖም በሁለቱም ቡድኖች ከፍተኛ የሆነ የግብ ፍለጋ ቢደረግም ቢሆንም ጨዋታው 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሆነው እና ብዙ ክስተቶች በታዩበት በ10 ሰዓቱ ጨዋታ ቦዲቲ ከተማዎች ድል አድርገዋል።

ጨዋታው ከተጀመረ ገና በ4ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው እስማኤል ጌታሁን ከቅጣት ምት በተሻገረለት ኳስ ግብ አስቆጥሮ ቢሾፍቱ ከተማዎችን መሪ እንዲሆኑ ማድረግ ችሎ ነበር።

የአቻነት ግብን አብዝተው በመፈለግ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቢሾፍቱ ግብ ክልል ሲጠጉ የነበሩት ቦዲቲ ከተማዎች የአጥቂ መስመር ተጫዋች የሆነው ማሞ አየለ ከተከላካይ መሰመር በረጅም የተጣለለትን ኳስ ከመሃል ሜዳ አንስቶ እየገፋ ወስዶ በማስቆጠር አቻ ሆነው ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ ያደረገ ሲሆን ወደ ዕረፍት ለማምራት በተጨመረው ደቂቃ የቦዲቲው ዘሩባቤል ፈለቀ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ባስቆጠራት ግብ በ 2-1 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊትም የቦዲቲው ማንዴላ መለሰ እና የቢሾፍቱው ዳዊት ሽፈራው በገቡት ሰጣገባ ከሜዳ በቀይ ካርድ ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብለው የገቡት ቢሾፍቱ ከተማዎች በተደጋጋሚ ወደ ቦዲቲ የግብ ክልል ቢጠጉም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም።መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሊጠናቀቁ 6 ደቂቃዎች ያህል ሲቀሩም ተቀይሮ የገባው መልካሙ በኬ ከርቀት የመታት ኳስ በቢሻፍቱ ግብ ጠባቂ መዘናጋት ወደ ግብነት ተቀይራ ጨዋታውን 3ለ1 በማድረግ ቦዲቲ መሪነቱን በሁለት ግብ ልዩነት ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም የቢሾፍቱ ተጫዋች የሆነው ጃፋር ከበደ ተቀይሮ በመግባት በእርስ እርስ ቅብብሎሽ ከሽንፈት ያልተደገቻቸውን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በቦዲቲ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።