የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 15ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በዐፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ተከናውነው ገላን ከተማ ድል አስመዝግቧል። ሀላባ እና አምቦ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

8:00 ላይ ገላን ከተማ ጌዲኦ ዲላን ገጥሞ 3-2 አሸንፏል። የኋላሸት ፍቃዱ ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ባስቆጠረው ጎል ገላኖች ቀዳሚ ቢሆኑም ተስፋዬ በቀለ በ 36ኛው እንዲሁም ሙሉ ዓለም በየነ በ56ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ጌዴኦ ዲላን መሪ እንዲሆን ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም በሱፍቃድ ነጋሽ በ74ኛው ደቂቃ በጨዋታ ፣ በ 86ኛው ደቂቃ ደግሞ በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠራቸው ጎሎች ገላን ከተማ ከጨዋታው ሦስት ነጥቦች ይዞ እንዲወጣ አስችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ገላን ከተማ የደረጃ መሻሻል ባያሳይም በ18 ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው በአራት ነጥቦች መራቅ ሲችል ባልተጠበቀ ሁኔታ ዘንድሮ ተዳክሞ የቀረበው ጌዴኦ ዲላ በ14 ነጥብ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

10:00 ላይ የተደረገው የሀላባ ከተማ እና አምቦ ከተማ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ሀላባ ከተማ ገና በአራተኛው ደቂቃ በቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አጥቂ ማናዬ ፋንቱ ጎል ረጅም ደቂቃዎችን መምራት ቢችልም ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩ ብሩክ ቸርነት አምቦን አቻ አድርጓል።

በውጤቱ መሰረት ሀላባ ከተማ በ18 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አምቦ ከተማ በ10 ነጥቦች አሁንም ግርጌው ላይ ረግቷል።