ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ11ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ11ኛ ሳምንት የተደረጉ ጨዋታዎችን በመንተራስ ተከታዩን ምርጥ ቡድን አዋቅረናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-2-1-3

ግብ ጠባቂ


ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ

በጨዋታ ሳምንቱ የነጠረ ብቃት ያሳዩ የግብ ዘቦችን መመልከት ባንችልም በአንፃራዊነት ሳማኬ በግሉ ጥሩ ምሽት በማሳለፉ በግብ ብረቶቹ መካከል እንዲቆም አድርገነዋል። ቡድኑ በድሬዳዋ ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበት ቢሸነፍም ሌሎች እጅግ ለግብ የቀረቡ ሦስት አጋጣሚዎችን ያመከነበት እና በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ የድሬን ተሻጋሪ ኳሶች ሲመክት የነበረበት መንገድ በምርጥ ቡድናችን ቦታ እንዲያገኝ አስችሎታል።

ተከላካዮች


ብርሃኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

በየሳምንቱ ምርጥ ብቃት ከሚያሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ብርሃኑ በቀለ ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ወሳኝ ድል ሲቀዳጅ የነበረው ብቃት መልካም የሚባል ነበር። ለማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመሄድ የማይሰንፈው ተጫዋቹ በተለይ ዋነኛ ኃላፊነቱ በነበረው መከላከል የተጋጣሚን ፈጣን የመስመር አጥቂ ተቆጣጥሮ ቦታውን ማስከበሩ ትልቅ አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል።

አሳንቴ ጎድፍሬድ – ድሬዳዋ ከተማ

በመቀመጫ ከተማው አልቀመስ ካለው ድሬዳዋ ቡድን ጎልቶ የወጣው (ከወልቂጤው ጨዋታ ውጪ) አንደኛው ተጫዋች ጎድፍሬድ ነው። ግዙፉ ተከላካይ የፋሲልን የመሬት እና ዐየር ጥቃቶች እያሸተተ ከአደጋ በፊት ማምከኑ እና ቡድኑ የቆሙ ኳሶችን ሲያገኝ ቁመቱን ተጠቅሞ ለመጠቀም መጣሩ የሚደነቅ ሲሆን በጨዋታው ቢኒያም ያስቆጠራትን ሁለተኛ ጎልም መነሻ ነው።

ያሬድ ባየ – ባህር ዳር ከተማ

በሳምንቱ ተጠባቂ ፍልሚያ የጣና ሞገዶቹ ከፈረሰኞቹ ጋር ነጥብ ሲጋሩ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ብቃት ያሳየው ያሬድ ከአሳንቴ ጋር አጣምረነዋል። እርግጥ አጋሩ ፈቱዲንም የጊዮርጊስን የማጥቃት አጨዋወት ለማምከን ሲጥር የነበረ ቢሆንም በአንፃራዊነት አምበሉ ያሬድ በጥሩ መታተር ግዙፉን አጎሮ ጨምሮ ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎች ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ የሄደበት ርቀት የተሻለ አድርጎት እንዲመረጥ ኖኗል።

ካሌብ በየነ – ሀዲያ ሆሳዕና

በዘንድሮ የውድድር ዓመት አንድም ደቂቃ ሳይጫወት ባሳለፍነው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ የጨዋታ ዕድል ያገኘው ወጣቱ የመስመር ተከላካይ በከባዱ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል ቢያገኝም ራሱን በሚገባ አሳይቶ ወጥቷል። ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥቶ ሲጫወት የተመለከትነው ካሌብ በሽግግሮች ወቅትም በተሰለፈበት መስመር አበርክቶ ለመስጠት ሲታትር ውሏል። በእርሱ ቦታ የነበረውን የተጋጣሚ አጥቂም በሚገባ ተቆጣጥሮ ቡድኑን ጠቅሟል።

አማካዮች


አለልኝ አዘነ – ባህር ዳር ከተማ

በቅርብ ሳምንታት በምርጥ ብቃት ላይ ሆኖ ቡድኑን በሚገባ እያገለገለ የሚገኘው አለልኝ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሲንቀሳቀስ አስተውለናል። በጨዋታው የነበረው የአማካይ መስመር ፍልሚያ ጠንካራ የነበረ ቢሆንም አለልኝ ከአጋሮቹ ጋር የኃይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው ለማድረግ ሲጥሩ ነበር። በተጨማሪም ከኳስ ውጪ ቡድኑ ጥቃቶች እንዳይበዙበት ለተከላካይ ክፍሉ ተገቢ ሽፋን ሲሰጥ ታይቷል።

ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጠባቂ ከነበረው መርሐ-ግብር በምርጥ ቡድናችን የተካተተው ሌላኛው ተጫዋች ሀይደር ሸረፋ ነው። ከሳጥን ሳጥን ቡድኑን ለማገዝ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሀይደር ቡድኑ የግብ ምንጭ አጥቶ በተቸገረበት ሰዓት የዘገዩ የሳጥን ሩጫዎችን በመከወን ሙከራዎችን ለማድረግ በተደጋጋሚ ሳጥን ውስጥ ሲገባ ያስተዋልን ሲሆን በመከላከል ቅርፅም የተጋጣሚን የኳስ ቅብብሎች በጥሩ ሁኔታ ለማጨናገፍ ሲሞክር አምሽቷል።

ፍፁም ዓለሙ – መቻል

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ መቻል ከሦስት ነጥብ ጋር ሲታረቅ የፍፁም መኖር ወሳኝ ነበር። ፈጣኑ የአጥቂ አማካይ በቁጥር በዝተው ሲከላከሉ የነበሩትን የሀዋሳ ተጫዋቾች ለማስከፈት ከአጋሮቹ ጋር ሲጥር የነበረ ሲሆን በግሉም ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ተስተውሏል። ምንም እንኳን ተጫዋቹ ኳስ እና መረብን በስሙ ማስመዝገብ ባይችልም ሁለቱንም የተቆጠሩትን ጎሎች በሚገርም ሁኔታ አቀብሏል።

አጥቂዎች

አቡበከር ወንድሙ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከለገጣፎ ለገዳዲ ሦስት ነጥብ ሲወስድ ለ2ኛ ጊዜ በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ የገባው አቡበከር ምርጥ የሚባል የጨዋታ ዕለት አሳልፏል። የመስመር አጥቂው በተደጋጋሚ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ሲገባ የነበረ ሲሆን አደገኛ የሚባሉ የግብ ዕድሎችንም ከቆሙ እና ክፍት ጨዋታዎች ሲፈጥር ነበር። ተጫዋቹ የቡድኑን የመጀመሪያ ጎል በግንባሩ በስሙ ሲያስመዘግብ የማሳረጊያውንም የአሜ ጎል አመቻችቶ አቀብሏል።

ቢኒያም ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ

በአስራ አንዱም የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው ቢኒያም በፋሲሉ ጨዋታ ራሱ ደምቆ ቡድኑን ጣፋጭ ሦስት ነጥብ አስገኝቷል። በተለይ ተጫዋቹ ጎሎቹን ያስቆጠረበት መንገድ እየበሰለ እንደመጣ ያሳየ ነበር። በዚህም የመጀመሪያውን ጎል ከመዓዘን ምት የተሻማን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ በቅርቡ ቋሚ በመገኘት በግንባሩ ሲያስቆጥር ሁለተኛውን ደግሞ በመስመሮች መካከል በመገኘት ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሯል።

አሜ መሐመድ – አዳማ ከተማ

በጨዋታ ሳምንቱ ተቀይሮ በመግባት የተዋጣለት ጊዜን ካሳለፉ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ አሜ ነው። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሰከንዶች ሲቀሩት ዳዋን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተጫዋቹ ቡድኑ በአስተማማኝ ሁኔታ ሦስት ነጥቡን በእጁ እንዲያስገባ ያደረጉ ሁለት ጎሎች በሰከንዶች ልዩነት አስቆጥሯል። ከግቦቹ ውጪም ፍጥነቱን ተጠቅሞ ሌሎች ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥር ተስተውሏል።

አሠልጣኝ


ፋሲል ተካልኝ – መቻል

መቻል ከስድስት ጨዋታዎች የድል ናፍቆት በኋላ ሲያሸንፍ ያሳየው የሜዳ ላይ ብልጫ የቡድኑን አሠልጣኝ በምርጥ ቡድናችን እንድናካትት አድርጎናል። እርግጥ አሰልጣኝ ዮርዳኖስ እና ያሬድም በምርጫው የቀረቡ እጩዎች የነበሩ ቢሆንም እንደገለፅነው ከተገኘው ሦስት ነጥብ ባለፈ ቡድኑ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውን በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የነበረው ብርታት ፋሲልን ቀዳሚ እንድናደርግ አስገድዶናል።

ተጠባባቂ

ባህሩ ነጋሽ
ሚሊዮን ሰለሞን
ዳዊት ማሞ
ብሩክ ማርቆስ
ምንያህል ተሾመ
ኤሊያስ አህመድ
ሳሙኤል ሳሊሶ
ናትናኤል ሠለሞን
አማኑኤል ገብረሚካኤል