የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 0-0 ፋሲል ከነማ

👉 “ከወራጆቹ አንዱ ይሆናል ተብሎ የተገመተ ቡድን እዚህ ደረጃ መቀመጡ እና መድረሱ ትልቅ ነገር ነው” ገብረመድህን ኃይሌ

👉 “እኛ የጣልነውን ያህል መሪዎቹ ብዙ አልራቁም ፤ ዋናው ነገር ቡድኑን ማስተካከል ነው” ኃይሉ ነጋሽ

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለጨዋታው…

ጨዋታው መጥፎ የሚባል አይደለም ፤ ግን ከባለፈው ጨዋታ ትንሽ ቀዝቀዝ ብሏል። ይህ ቢሆንም ተጫዋቾቹ ጨዋታውን ለማሸነፍ የነበራቸው ስሜት እና ፍላጎት ጥሩ ነበር። ውጤቱ መሪነት ላይ የሚያስቀምጠን ቢሆንም ትንሽ ከልምድ ጋር የተገናኙት ነገሮች አሉብን። በአጠቃላይ ግን ጨዋታው ጥሩ ነበር።

ስለአማካይ መስመሩ ድክመት…

እኔ ማንንም መውቀስ አልፈልግም። ኳስ አስተካክሎ ለመስጠት የተስተካከለ ሜዳ ያስፈልጋል ፤ በዚህ ሜዳ መርሐ-ግብር ለመጨረስ ካልሆነ ለምን አስተካክለህ አላቀበልክም ብሎ መናገር በጣም አስቸጋሪ ነው።

ስለቡድኑ ጉዞ…

ጥሩ ነው። በጣም ከሚገባው በላይ ጥሩ በሚባል ደረጃ ሊገለፅ ይችላል። ከወራጆቹ አንዱ ይሆናል ተብሎ የተገመተ ቡድን እዚህ ደረጃ መቀመጡ እና መድረሱ ትልቅ ነገር ነው። ይህም ትልቅ ተነሳሽነት የሚፈጥር ነው። ተጫዋቾቻችን ያላቸውን አቅም አውጥተው የሆነ ነገር ለማድረግ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ያስደስታል።

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

በጨዋታው ስላደረጉት እንቅስቃሴ…

ጨዋታው ከሌላው ቀን ትንሽ ይሻላል። አሸንፈን ለመውጣት ነበር ጥረት ያደረግነው። ተጫዋቾቻችንም አቅማቸው የፈቀደውን ያክል አድርገዋል ፤ ግን ማሸነፍ አልቻልንም።

ሦስት ነጥብ ያላሳኩበት ምክንያት…

ከውጤት ማጣት ጋር በተገናኘ ተጫዋቾች ላይ ትንሽ ጭንቀት ይታያል። ነፃ ሆነህ የምታቀብላቸው ኳሶች ሁሉ ይበላሹብሀል። ከዕረፍት በፊት እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ነበሩ። ከእረፍት በኋላ ካወራን በኋላ ግን ትንሽ ለማሻሻል ሞክረዋል። ተጭነት ተጫውተናል። ወደ እኛ የጎል ክልል የደረሱበት አጋጣሚ የለም። ግን በቀጣይ ከዚህ የተሻለ አሻሽለን መቅረብ እንዳለብን ይሰማኛል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን በአጥጋቢ ሁኔታ መፍጠር ስላለመቻላቸው…

አንዳንዴ ስትቸገር እና ውጤት ሲጠፋ ብዙ ነገሮች ናቸው የሚበላሹብህ። እርግጥ ነው ክፍተቶች ይታዩኛል ፤ እዛ ላይ ሰርተን በቀጣይ እንቀርባለን።

ከመሪዎቹ እየራቁ ስለመሆኑ…

ብዙ መራራቅ የለም። እኛ የጣልነውን ያህል መሪዎቹ ብዙ አልራቁም። ዋናው ነገር ቡድኑን ማስተካከል ነው ፤ ቡድኑ ከተስተካከለ እና አሸናፊነቱ ከመጣ የማይደረስበት ምክንያት የለም። ለመድረስ ጥረት እናደርጋለን።