በአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ሶማልያን 2-1 ያሸነፈው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን 5 ተጫዋቾችን ቀንሶ በምትኩ አዳዲስ ተጫዋቾች በመጥራት ለመልሱ ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት ቀጥሏል፡፡ የዝጅግት ስፍራው ለማድረግ ካሰበበት ድሬዳዋ ለውጥ በማድረግም ወደ አዳማ እንደሚያቀና ታውቋል፡፡ ቡድኑ ነገ ወደ አዳማ የሚጓዝ ሲሆን እስከ መልሱ ጨዋታ መቃረብያ ድረስ በአዳማ ዝግጅቱን ይቀጥላል፡፡
ቡድኑ ዛሬ ጠዋት ላይ ልምምዱን የሰራ ሲሆን በአጠቃላይ 21 ተጫዋቾች ተገኝተዋል፡፡ አሰልጣኝ ግርማ እና ረዳቶቻቸውም በዲፓርትመንት በመከፋፈል ኳስን ከተከላካይ ክፍሉ አደራጅቶ መጫወትን ፣ ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ መቀየር እና ተከላካይ የማስከፈት ልምምዶችን ሲያሰሩ ተስተውሏል፡፡
ለቡድኑ ከተጠሩት ተጫዋቾች መካከል የቡና ተስፋ ቡድን አጥቂ የሆነው ገናናው ረጋሳ በዛሬው ልምምድ ላይ የተገኘ ሲሆን ከድሬዳዋ ከተማ የተመረጠው ሱራፌል ዳንኤል እንዲሁም ከሰበታ ከተማ የተጠሩት ተከላካዩ ኢብራሂም ሁሴን እና አጥቂው ተመስገን ገብረኪዳን ምሽቱን ሆቴል ገብተው ነገ ከቡድኑ ጋር ልምምዳቸውን ይጀምራሉ፡፡ የንግድ ባንኩ ቢንያም በላይ ደግሞ ሰኞ ቡድኑን ይቀላቀላል፡፡