ፕሪሚየር ሊግ – የ1ኛ ዙር ግምገማ በአዳማ እየተካሄደ ነው

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዙርን በማስመልከት አዳማ በሚገኘው ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል ግምገማ እና ሪፖርት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የግምገማ እና ሪፖርቱን ዋና ዋና ነጥቦች በዚሁ ገፅ ላይ እናቀርብላችኀለን፡፡

ለተጠየቁ ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች
የውድድር እና ስነስርአት ጉዳዮች
– እኛ በተመቻቸ ሜዳ ፣ ሰአት እና ቀን እንዲደረግ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ካሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ነው መሄድ የምንችለው፡፡
– በኮሚኒኬ ላይ የተነሱ ቅሬታዎች ትክክል ናቸው፡፡ በዚህ ዙርያ ያለውን ችግር እንደምናስተካክል ቃል እንገባለን፡፡
– የውድድር ለውጥ ሲነቀር ሁሌም እናሳውቃለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ መዘግየት ሲኖር በስልክ ጭምር ለክለቦች እናሳውቃለን፡፡
– ለየትኛውም ቡድን የሚያደላ የጨዋታ ሰአት መድበን አናውቅም፡፡ ስሌት በማድረግ ነው የውድድር ሰአት የምንመድበው፡፡ ነገር ግን ፍፁም እኩል ሊሆን አይችልም፡፡
– በሜዳዎች ጥራት ላይ አወዳዳሪው እና ተወዳዳሪው ተቀራርቦ መስራት አለበት፡፡ እኛ የሜዳዎችን ጥራት ተከታትለን ባላሟሉት ላይ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ አሁን ያለን መረጃ ግን ሜዳዎችን እያስተካከሉ እንደሆነ ነው፡፡
– የውድድሩ ፕሮግራም ዘመናዊ ስሌት የተከተለ እና እነ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊገ ግየሚጠቀሙበት ነው፡፡ ነገር ግን በአስገዳጅ ሁኔታዎች አፈፃፀም ላይ ጉድለት አለ፡፡
– የጥሎ ማለፉ በአንድ ዙር ስለሆነ ነው አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ያደረግነው፡፡ ክለቦች ጊዜው ይበቃናል ፣ በጀታችን ይበቃናል የሚሉ ከሆነ በደርሶ መልስ ማድረግ እንችላለን፡፡

ከዳኞች ኮሚቴ የተሰጡ መልሶች
– በኛ በኩል በዳኛ ውሳኔ የተጎዱ ክለቦች እንዳሉ አይተናል፡፡ በውጤት ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩትን ዳኞች ቀጥተናል፡፡ ቀላል ጥፋት የፈፀሙ ዳኞችንም ከደረጃቸው እንዲወርዱ ተደርጓል፡፡
– ዳኝነት ምደባ ላይ ክለቦች የማይፈልጓቸው ዳኞችን እንዳይመደቡ ይጠይቃሉ፡፡ ዳኝነቱን የመመደብ ስልጣን ለኛ ተዉት፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ የምንመድባቸው ዳኞችን ለመቀነስ ጥረት እናደርጋለን፡፡
– 350 ዳኞች አሉን፡፡ ነገር ግን ፕሪሚየር ሊጉ ላይ የማጫወት ብቃት ያላቸው 37 ዋና እና 46 ረዳት ዳኞች ናቸው፡፡ ካለደረጃቸው ብንመድብ ተገቢ አይደለም፡፡
– ከ91 ጨዋታዎች የዳኝነት ግድፈት የታየባቸው 3 ጨዋታዎች ናቸው፡፡
– አንድ ዳኛ የአካል ብቃት እና የህክምና መስፈርቱን ካሟላ እንመድባለን፡፡
– ብቁ ዳኛ ያላቸው ክልሎች ጥቂት ናቸው፡፡ ሶማሌ እነና ጋምቤላ ኢንተርናሽናል ዳኛ የላቸውም፡፡ ስለዚህ የተመጣጠነ ምደባ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡
– ዳኛ በሜዳ ውስጥ ለሚወስነው ውሳኔ ክለቦች ሜዳ ላይ የመክሰስ መብት የላቸውም፡፡
– ዳኞች በየሚዲያው እየተዘለፉ ነው፡፡ ዳኞች ሚድያ ላይ ቀርበው የመከላከል መብት ስለሌላቸው ስብእናቸው እየተገፈፈ ነው፡፡
– አንዳንድ ግለሰቦች ከተመልካች መቀመጫ እየተነሱ ዳኞች እንዲከሰሱ ትእዛዝ የሚያስተላልፉ አሉ፡፡
– – – – – – – – – –
ከክለብ ተወካዮች የተሰጡ አስተያየቶች

ከአዳማ
– የውድድር ቦታዎች ቀድሞ የማሳወቅ ችግር አለ፡፡ ይህም ክለቦችን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋል፡፡
– የኮሚኒኬ በቶሎ አለመድረስ ችግር እየታየ ነው፡፡ ኮሚኒኬ በቶሎ ካልደረሰን ያልተገባ ተጫዋች ልናሰልፍ እንችላለን፡፡
– የጥሎ ማለፍ ውድድሩ አዲስ አበባ ላይ ብቻ መደረግ የለበትም፡፡

ከወላይታ ድቻ
– የዳኛ ምደባ ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ብዙ ጊዜ የአዲስ አበባ ዳኞች ናቸው እንዲዳኙ የሚደረገው፡፡ ለሁሉም ፍትሃዊ ሊሆን ይገባል፡፡

ከድሬዳዋ
– የዳኛ ውሳኔዎች ሊስተካከሉ ይገባል፡፡ አንድ ተጫዋች ጥፋት ተሰርቶበት በዝምታ ከታለፈ ጥፋት የተሰራበት ተጫዋች ስሜቱ ይነሳሳና ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ ካለ አግባብ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ይደረጋል፡፡
– የፌዴሬሽኑ ስራ የሚከናወነው ስታድየም እና ካዛንችስ በመሆኑ ተጉላልተናል፡፡ ጨዋታ በሚኖርበት ሰአት ስታድየም የሚገኙ ቢሮዎች ውስጥ መግባት እንከለከላለን፡፡ ይህ ሊስተካከል ይገባል፡፡

ከሀዲያ ሆሳዕና
– የውድድር መቆራረጥ ውጤታችን ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮብናል፡፡
– አንዳንድ ሜዳዎች ለመጫወት አስቸጋሪ ናቸው፡፡
– በሚድያ በኩል ትኩረት የሚደረገው በአዲስ አበባ ጨዋታዎች ላይ ነው፡፡

ከደደቢት
– በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ያለው አሰራር ኀላ ቀር ነው፡፡ ወደ አለም አቀፍ አሰራር መግባት ይኖርብናል፡፡
– የጨዋታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሙከራ ተጀምሮ ነበር፡፡ ምን ደረጃ እንደደረሰ አናውቅም፡፡
– ፉክክሩ በደጋፊ ረገድ ያልተመጣጠነ ነው፡፡ ሁሉም እኩል እንዲመጣ ድጋፍ መደረግ አለበት፡፡
– ስታድየም ላይ የሚሰሙ አጸያፊ ስድቦች እስካልቆሙ ድረስ አዳዲስ ተመልካቾች አይመጡም፡፡ ስለዚህ ሁሌም ውድድሩ የዳዊት እና ጎልያድ ይሆናል፡፡
-ክለቦች ላይ ዳኛን እንደጠላት የምናይበት ሁኔታ አለ፡፡ ውጤት ስናጣ ዳኛ ላይ ማሳበብ እና የፀጥታ ችግር ማስከተል አይገባም፡፡
– ሁሉም ክለቦች ላይ በዳኝነት ስህተት ተጎድተዋል፡፡ ነገር ግን ሚዛናዊ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ስለሀገር ማውራት ካለብን ቡና ብቻ ነው ወይ ፍፁም ቅጣት ምት የተከለከለው? ሁሉም የፍፁም ቅጣት ምት የሚከለክል ዳኛ መቀጣት ሊኖርበት ነው፡፡
– የተጫዋች ተገቢነት ጉዳይ ላይ ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚለው በግልፅ መቀመጥ አለበት፡፡ ቡና ካለ አግባብ ካሰለፈ ሊቀጣ ይገባል፡፡ ቡናን ያሳሳተ አካል ካለም ቅጣት ይገባዋል፡፡

አርባምንጭ
ክለቦች ወደ ራሳችን መመልከት ይኖርብናል፡፡ የዳኞች ውሳኔ ቅፅበታዊ ነው፡፡ ሁሌም ስህተት ሊከሰት ይችላል፡፡ ዋናው መታየት ያለበት ግን ምደባ ላይ ፍትሀዊ ይሁን ነው፡፡
– ውድድር ውስጥ ስንገባ የአምበሳው ድርሻ የዳኞች ቢሆንም ለውድድሩ መንፈስ ማማር የየድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡ ከሁላችንም የሚጠበቀውን ማድረግ ካልቻልን የሁለተኛው ዙር ከመጀመርያውም የባሰ ይሆናል፡፡
– በሚድያ ላይ የክለቦችን ምስል የሚያበላሽ መሰረተ ቢስ ዘገባዎች ይዘገባሉ፡፡

ከዳሽን ቢራ
– በውድድር መቆራረጥ ከተጎዱ ክለቦች አንዱ ነን፡፡ ያደጉ ሃገሮችን ልምድ በመውሰድ ውድድሮች የማይቆራረጡበትን ሁገ፡ኔታ ማመቻቸት ይኖርብናል፡፡

ከመከላከያ
በተመሳሳይ ቀን በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚደረገው የሰአት አመዳደብ ላይ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው፡፡ የፕሮግራም አወጣጥ ላይ ትልቅ ክለቦች ትንሽ ክለቦች የሚል አሰራር መኖር የለበትም፡፡
– የሜዳዎች የጥራት ደረጃ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ፕሮግራሙ መደረጉ ብቻ ሳይሆን መታየት ያለበት ለውድድሩ ጥራት እና ለሜዳ ጥራት ልንጨነቅ ይገባል፡፡
– ለአንዳንድ ክለቦች የሚያደላ የዳኞች አመዳደብ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር የመላቀቅ እና የተዛቡ የዳኝነት ውሳኔዎች ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ ሊኖር ይገባል፡፡
– በስታድየም ያለው አጸያፊ ስድብ ሊቆም ይገባል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ መፍትሄ ማበጀት አለበት፡፡
– ኮሚሽነሮች እና ዳኞች ዘግይተው በመምጣት የጨዋታ ሰአት እያዛቡ ነው፡፡

– – – – – – – – – – – – – – – – – – – – – – –
የዳኞች ኮሚቴ ሪፖርት
– በተካሄዱት 91 ጨዋታዎች እንደየጨዋታዎቹ ክብደት የሚመጥኑ ዳኞች ለመመደብ ተሞክሯል፡፡

– በ3 ጨዋታዎች ላይ ከባድ የዳኝነት ሰህተቶች ተፈፅመዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ከ6ወር እስከ 1 አመት የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ ተወስኗል፡፡

– በዚህ አመት ከሰራናቸው ስራዎች መካከል መደበኛ ባልሆነ መልኩ በየሳምንቱ የመገምገም ስራ ሰርተናል፡፡ በዚህም በ4 ጨዋታ በቂ ሪፖርት ባላቀረቡ ታዛቢዎች ላይ ክትትል አድርገን ከደረጃቸው ወርደው እንዲሰሩ አድርገናል፡፡

የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሪፖርት
– በ1ኛው ዙር 16 ተጫዋቾች በድምሩ 36 ጨዋታ ተቀጥተዋል፡፡ በገንዘብ ደግሞ በድምሩ 16 ሺህ ብር ተቀጥተዋል፡፡ አንድ አሰልጣኝ እና አንድ አሰልጣኝ ከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት በመፈፀማቸው የ1 አመት ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡

– በጨዋታ ላይ በርካታ ቢጫ እና ቀይ የተመለከቱ 8 ቡድኖች እያንዳንዳቸው 5 ሺህ ብር በአጠቃላይ 40 ሺህ ብር ተቀጥተዋል፡፡

– በዲሲፕሊን በኩል ካለፈው አመት መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ በ2007 የውድድር ዘመን 1ኛ ዙር 20 ቀይ እና 321 ቢጫ ሲመዘገብ በ2008 ግን ወደ 14 ቀይ እና 281 ቢጫ ካርድ ቀንሷል፡፡

የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሪፖርት
– ከቡና እና ኤሌክትሪክ ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ቅሬታዎች ቀርበዋል፡፡ በዳዊት እስጢፋኖስ ጉዳይ ላይ የተወሰነው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ የፀና ሲሆን ኤሌክትሪክ ባቀረበው ይግባኝ የአዲስ ነጋሽ ቅጣት ከ1 አመት ወደ 8 ወር ሲቀነስለት የአማረ በቀለ እና የአሰልጣኝ ብርሃኑ ቅጣት ፀንቷል፡፡

– በዳኞች ላይ የተላለፈውን የቅጣት ውሳኔ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ተመልክቶት በኮሚሽነሮች እና ዳኞች ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች አግባብ ሆነው ስላገኘናቸው ተሽሯል፡፡ በኮሚሽነር ሰለሞን ላይ የተላለፈው ውሳኔ ላይ ደግሞ አሻሽለናል፡፡

የፀጥታ ሪፖርት
– የትኬት ሽያጭ መዘግየት ለፀጥታ እክል ስለሚፈጥር ለማስተካከል ጥረት አድርገናል፡፡

– በካታንጋ መቀመጫዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ሪፖርት አድርገን ብናስጠግንም በድጋሚ የመሰባበር እጣ ደርሶበታል፡፡

– የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቡና የደጋፊ ተወካዮችን በመሰብሰብ በጸጥታ ጉዳይ ውይይት አድርገናል፡፡

– በየውድድሩ በስታድየም የፀጥታ ሀይሎች እንዲመደቡ አድርገናል፡፡ ይህ ክልሎችን አይጨምርም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *