ቻን | የዋልያዎቹ የመጀመሪያ የቻን ተጋጣሚ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ልታደርግ ነው

ጥር 6 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የቻን የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርገው ሞዛምቢክ ነገ እና እሁድ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ቀጠሮ ይዛለች።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት 7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየን ሺፕ ውድድር ከቀናት በኋላ በአልጄሪያ ይጀመራል። በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ 18 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው እና ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አንድ የተደለደለው የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ከሁሉም ቡድኖች ቀድሞ አልጄሪያ የደረሰ ሲሆን ዝግጅቱንም በውድድሩ ስፍራ እየከወነ ይገኛል።

\"\"

በብሔራዊ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ጥሩ የስራ ከባቢ አልተፈጠረልኝም በማለት ቅሬታቸውን ሲያሰሙ የነበሩት የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ ለውድድሩ ሦስት የግብ ዘቦች፣ ስምንት ተከላካዮች፣ ስድስት አማካዮች እና ስድስት አጥቂዎችን በአጠቃላይ 23 ተጫዋቾችን በመምረጥ ዝግጅታቸውን አልጄሪያ ላይ እየሰሩ የሚገኝ ሲሆን ነገ እና እሁድም አልጄሪያ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ለማድረግ እንዳሰቡ ታውቋል።

\"\"

ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ከኤም ሲ አልጀርስ ሁለተኛ ቡድን ጋር የፊታችን እሁድ ደግሞ ከቤሉይዝዳድ ወጣት ሁለተኛ ቡድን ጋር ወቅታዊ አቋሙን ለመፈተሽ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።