በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል እየተደረገ የሚገኘው የጥሎ ማለፍ ሩብ ፍጻሜ ዛሬ 2 ጨዋታዎች ተደርገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል፡፡
በ9፡00 ሲዳማ ቡናን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-1 አሸንፏል፡፡ ጋብሬል አህመድ ከማዕዘን ምት የተሸገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ንግድ ባንክን ቀዳሚ ሲያደርግ ቢንያም በላይ ከፊሊፕ ዳውዚ የተሸገረለትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ተከላካዮችን አምልጦ በመሄድ 2ኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በንግድ ባንክ 2-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና የተሸለ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን ከተፈጥሯዊው የአማካይ ሚናው በተለየ መልኩ ዘንድሮ በግራ ተከላካይነት እየተጫወተ የሚገኘው ሄይቲያዊው ሳውሬል ኦልሪሽ የሲዳማን ግብ በቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ የማስጠንቀቅያ ካርድ ተመልክቶ የነበረው ፊሊፕ ዳውዚ በ68ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ሳይሰራበት ወድቋል በሚል በ2ኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል፡፡
11፡30 ላይ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ካለግብ በማጠናቀቅ በመለያ ምቶች 4-2 አሸንፏል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ እና የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት እቅስቃሴ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱ ቡድኖች የሚያስቆጩ የግብ አድሎችን አምክነዋል፡፡ አዳማ ከተማ በ46ኛው ደቂቃ በተስፋዬ ነጋሽ ላይ በተሰራ ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኝ ዮናታን ከበደ መትቶ በግቡ አናት ወደላይ ሰዶታል፡፡ ጫላ ድሪባ ከግብ ጠባቂው ሀሪሰን ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከነው እንዲሁም ተስፋዬ ነጋሽ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ውጪ የወጣበት ከአዳማ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ በቡና በኩል ደግሞ ተቀይሮ የገባው ንዳዬ ፋይስ በጨዋታው መገባደጃ ያገኘውን ግልጽ የማግባት እድል አምክኗል፡፡
አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች አዳማ ከተማዎች የመቷቸውን 4 ኳሶች በሙሉ ሲያስቆጥሩ ከኢትዮጵያ ቡና በኩል ወንድይፍራው ጌታሁን እና ያቤውን ዊልያም አምክነው ጨዋታው በአዳማ 4-2 አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የአዳማ ከተማን የማሸነፍያ መለያ ምት በቀድሞ ክለቡ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ፋሲካ አስፋው ነው፡፡
በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የክለቡ አመራሮች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ አምሽተዋል፡፡ በ20ኛው እና 40ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የተሰሙ ተቃውሞዎችን ጨምሮ ነጭ ጨርቅ በማውለብለብም የክለቡ አመራሮች በተለይም ስራ አስኪያጁ አቶ ገዛኸኝን ሲቃመሙ ተስተውለዋል፡፡
በሊግ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ መደረግ ከነበረባቸው 4 ጨዋታዎች ሶስቱ ተደርገው መከላከያ ፣ አዳማ ከተማ እና ንግድ ባንክ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ሲያልፉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ የሚያደርጉት ጨዋታ እስካሁን ቀን አልተቆረጠለትም፡፡
ማስታወሻ
የዚህ ውድድር ስያሜ ‹‹የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ዋንጫ›› ነው፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ለአጠራር እና ዘገባ አመቺነት ሲባል ‹‹የኢትዮጵያ ሊግ ዋንጫ›› በሚል አሳጥራ ትጠቀማለች፡፡