“በሚቀጥለው ዓመት ከፈጣሪ ጋር ጠንካራ፣ የተረጋጋ እና ተፎካካሪ የሆነ ቡድን ለመገንባት ነው የማስበው” በፀሎት ልዑልሰገድ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከስድስት የውድድር ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመለሰው አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በሀገራችን ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት አሠልጣኞች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞ የበቆጂ ከተማ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ኢኮስኮ እና ገላን ከተማ አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በኢትዮጵያ እግርኳስ ገናና ስም የነበረውን ንግድ ባንክ በመያዝ ክለቡን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደጉ ይታወቃል። ዓምናም ኢትዮጵያ መድንን አሳድጎ የነበረው አሠልጣኙ በተከታታይ ዓመት ሁለት ክለቦችን ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር በማሳደግ ስሙን በታሪክ መዝገብ ላይ አፅፏል። ሶከር ኢትዮጵያም ስለዘንድሮ ውድድር ዓመት እና ስለቀጣይ ጊዜያት ከአሠልጣኙ ጋር ቆይታ አድርጋለች።
\"\"

የውድድር ዓመቱ እንዴት ነበር?

በመጀመሪያ ውድድራችንን ከመጀመራችን በፊት ውድድሩ ጠንካራ፣ ጥሩ ተፎካካሪዎች ፣ ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት እንዲሁም በአንድ ምድብ ውስጥ 14 ቡድኖች የሚገኙበት እና 5 ወራጆች የነበሩበት ከመሆኑ አንፃር ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ከባድ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር። በዚህ መሠረት የመጀመሪያ የቤት ስራችን የነበረው የሚፈለገውን ነገር የሚያመጡ ተጫዋቾችን መሰብሰብ ነበር። በጥንቃቄ ተጫዋቾችን ካስፈረምን በኋላ ወደ ዝግጅት ነው የገባነው። የቅድመ ውድድር ዝግጅታችንን ልንዘጋጅ ካሰብነው ጊዜ ትንሽ ዘግይተን ነበር የጀመርነው። የሆነው ሆኖ በዝግጅት ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታዎችንም አርገን ተዘጋጅተን ወደ ውድድር ገባን። የመጀመሪያውን ዙር ባህር ዳር ላይ ነበር ያደረግነው። ባህር ዳር ጥሩ ቆይታ ነበረን። ምናልባት እንዳልኩት ከዝግጅት ጊዜ ማጠር ጋር ተያይዞ የምንፈልገው ነገር ላይ አለመድረሳችን መጀመሪያ አካባቢ ትንሽ እንድንቸገር አድርጎን የነበረ ቢሆንም ወዲያው አስተካክለናል። ከዚህ ውጪ እዛ ትንሽ ስንቸገር የነበረው የምንወዳደርበት ሜዳ ስፋቱ ጠበብ የሚል በመሆኑ ተጋጣሚዎች አፈግፍገው ይጫወቱ ነበር። የሜዳው ለውጥ ሲደረግ ግን ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ በ1ኛ ዙር 13 ጨዋታዎች አድርገን 7 አሸንፈን 4 አቻ ወጥተን እንዲሁም አንድ ተሸንፈን አንደኛ ደረጃን ይዘን ጨርሰናል።

በመቀጠል ሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ በፊት አጭር የሽግግር ጊዜ ቢኖርም ቡድናችንን የመገምገም ስራ አከናውነን ሦስት ተጫዋቾችን ጨምረን የበለጠ ተሻሽለን ቀረብን። የሁለተኛው ዙሩ አሰላ ላይ ነው የተደረገው። አሰላ ላይ ጥሩ አቀባበል ነበር የተደረገልን። እዛ እንደ ችግር የነበረው ነገር ዝናቡ ነበር። ዝናብ በየቀኑ ይዘንብ ነበር። እዛ 10 ጨዋታ ተጫውተን 7 አሸንፈን፣ 2 አቻ ወጥተን 1 ብቻ ተሸንፈናል። ይህ በጣም ጥሩ ውጤት ነበር። ጭቃ እና ዝናብ ስለነበር ውጤት ለማግኘት ብቃት ብቻ ሳይሆን ዕድለኝነትንም ይፈልጋል። አሰላ የዝናቡ ነገር እየባሰ ሲሄድ የመጨረሻዎቹን 3 ጨዋታዎች ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም መጣን። ከጭቃ ወጥተህ ደግሞ ወደ አርቴፊሻል ሜዳ ስትመጣ ሌላ ነገር ይፈልጋል ፤ ግን በፍፁም በማይነፃፀር መልኩ ይህ ተመችቶን ሦስቱንም አሸንፈናል። በአጠቃላይ በሁለተኛ ዙር ከ13 ጨዋታ 10 አሸንፈን፣ 2 አቻ ወጥተን 1 ብቻ ተሸንፈን አጠናቀናል። በድምር ውጤት ሪከርድ በሆነ 60 ነጥብ እና በብዙ የግብ ክፍያ አጠናቀን ጥሩ ዓመት አሳልፈን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ገብተናል።

ዓምና ኢትዮጵያ መድንን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳድገህ ከክለቡ ጋር እንደማትቀጥል ካወክ በኋላ ምን ነበር የተሰማህ? ወደ አዲስ ክለብስ ስታመራ ምን አይነት ሀሳብ በውስጥህ ነበር?

2014 ላይ ወደ ኢትዮጵያ መድን ስመጣ ለሁለተኛ ጊዜ ነበር የተመለስኩት። ሲጠሩኝ በዋነኛነት ያወሩኝ ነገር \’ያለፉትን ስምንት ዓመታት ቡድኑን ገምግመን ያንተ የ2012 ቡድን አለማስቀጠላችንና ያንተን ውል አለማደሳችን ስህተት ነበር\’ የሚል ነው። ይህንን ተከትሎ ክለቡን እንዳሳድግ ተግባብተን ገባሁ። ያው እኔ ቃሌን ጠብቄያለው ፤ ክለቡ አደገ። ልትለያይ ትችላለህ ስትለያይ ግን ተመሰጋግነህ ቢሆን ደስ ይል ነበር። ድንገተኛ ነበር። እኔ እስከዛ ድረስ ስራ እየሰራው ነበር። ይሄ ትንሽ ስሜትን የሚጎዳ ነበር። እንደ ሰወኛ ቢሰማህም ያልፋል። ዓመቱን ሙሉ ለፍተህ በመጠቀሚያህ ሰዓት ይህ መሆኑ ትንሽ ስሜት ይነካል። ግን ደግሞ ህይወት ይቀጥላል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስታወቂያ ሲወጣ ተወዳድሬ ገባሁ። ባንክ ስመጣ በአዲስ መንፈስ ነበር የመጣሁት። የኋላውን ስትረሳ ነው የወደፊቱን የምትሰራውና ያለፈውን ሙሉ ለሙሉ ትቼ ነው ትኩረቴን ስራው ላይ ያደረኩት።

እርግጥ ገና ወጣት አሠልጣኝ ነህ። በስልጠናው ዓለም በቆየህበት በዚህ አጭር ጊዜ በተለይ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ ቡድን ከሚሰሩና ውጤታማ አሠልጣኞች መካከል አንተ ትጠቀሳለህ። አንዳንዶች እንደውም \’የከፍተኛ ሊጉ ስፔሻሊስት\’ ይሉሀል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ምን ሀሳብ አለህ። በተከታታይ ቡድኖችን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማሳደጉ ሚስጥርስ ምንድን ነው?

የከፍተኛ ሊጉ ስፔሻሊስት ከተባለው ጋር እሱን ላሉት ሰዎች ልተው (ከሳቅ ጋር)። በዋናነት ውድድሩ ምን ይፈልጋል የሚለውን ነገር በጥልቀት ማየት እንዲሁም ውጤታማ የሚያደርግህን ነገር በሥነ-ምግባር መስራት ነው። ሥራ እና ሥራን በትኩረት የምታይ ከሆነ ውጤታማ ያደርጋል ብዬ አስባለው። ይህ ማለት ጨዋታዎችን ማየት እና ተጫዋቾችን ማወቅ ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም በምፈልገው የቡድን ቅርፅ ተጫዋቾችን ማሰባሰብ ላይ በደንብ ትኩረት መስጠቴ ይመስለኛል ውጤታማ ያደረገኝ። ከዚህ በተረፈ መጀመሪያ ላይ የምትሰራው ሥራ አጠቃላይ ሥራህን ያቀልልሀል። መጀመሪያ የሰበሰብካቸው ተጫዋቾች እና የገነባከው ቡድን እንዲሁም ያለውን ነገር ማስቀጠሉ ትልቁ ሥራ ነው። በተጨማሪም ከኮቺንግ ስራፍ፣ አመራር እና ተጫዋቾች ድረስ ያለው የቡድን መንፈስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብዬ ነው የማምነው።

\"\"

አብዛኞቹ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች በአጭር የኳስ ንክኪ (በረጃጅም ኳሶች) ጎል ላይ መድረስ የሚፈልጉ ናቸው። ያንተ ቡድን በተቃራኒው ዘለግ ያለ ጊዜ ከኳስ ጋር ማሳለፍ ይፈልጋል። ከጠቀስኩት የሊጉ ባህሪ ተደርጎ ከሚወሰደው አጨዋወት ወጣ በማለት ስትጫወት ከሜዳ ጀምሮ የገጠሙህን ፈተናዎች እንዴት አለፍካቸው?

እንዳልከው ለጨዋታ ዘይቤ በተለይም ኳስ ይዘህ ለመጫወት ምንም ጥርጥር የለውም ፤ የሜዳ አለመመቸት ብዙ ነገርህን ያበላሽብሃል። በምትፈልገው ልክ እንዳትሆን እንደ አንድ ክፍተት ወይም እንደ አንድ ጫና ምታየው ነገር ነው። ነገር ግን በአንጻራዊነት ሜዳው ባይመችም ያንን ኳስ ተቀባብሎ የመሄድ ሀሳባችንን ሳንለቅ ለመጫወት ነው የምናስበው። ሜዳው እንደማይመች የታወቀ ነው አምናም ሁለተኛውን ዙር ሀዋሳ ላይ ነበር የጨረስነው። ሀዋሳ ላይ ያለው ሜዳ ኳስ ተቆጣጥሮ ለመጫወት አይመችም ፤ አይተህ ከሆነ የኛ ቡድን ግን ይጫወት ነበር። ያን ሜዳ ለመልመድ በተቻለ መጠን ልምምዶችን በመሥራት በማይመች ሜዳ ውስጥም ለመቀባበል ማሰብ በተለይም የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመወጣት በጣም ትኩረት የማድረግ ያንን በየጨዋታው የመገምገም ፤ ማለትም ከዛ ትዕዛዝ እንዳይወጡ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ ያው በዘፈቀደ እንዲጫወቱ አልፈቅድም ብዙ ጊዜ በተነጋገርነው መሠረት ምክንያቱም በዘፈቀደ ከተጫወቱ እነሱ ናቸው እየመሩ ያሉት ማለት ነው። ባልከው ልክ ስትጫወት ስህተት እንኳን ቢኖር ታርማለህ ምክንያቱም በዚህ ስለተጫወትን ወይም ደግሞ ነጥብ ማድረግ ትችላለህ ከፍተትህን እና ጠንካራ ጎንህን መለየት ትችላለህ ባልከው ዓላማ ስትሄድ ማለት ነው። አልያ ግን ከሀሳብ ተወጥቶ ሲኬድ ስህተትህን ለማየት እና ለማረምም ይከብዳል እና በተቻለ መጠን ያንን ለማድረግ ነው የምንሞክረው። አንዳንድ ጊዜ ግን ተለዋዋጭ የምትሆንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ ለምሳሌ ስትራቴጂህን የምትከልስበት ስትወጣ እያንዳንዱን ከመጀመሪያው ጀምሮ መስርተህ መውጣትም ብትፈልግ አንዳንድ ጊዜ ከመካከለኛ ርዝመት ላይ የመጀመር ለምሳሌ በመሀል ተከላካይ እና በመስመር ተከላካይ ላትጀምር ትችላለህ ሜዳው ሳይመችህ ቀርቶ ማለት ነው። በጣም ተጭኖ ለሚያደርግ ቡድንም ሜዳው አመቺ ይሆናል እና እነዛንም ታሳቢ አድርገን የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ማለትም የምትደራጅበትን ቅርፅ ሳትቀይር የመከለስ ነገሮች ላይ ማየት ያስፈልጋልና በዛ መሠረትም እንዘጋጅ ስለነበር ሜዳው ባይመችም ከሞላ ጎደል ጥሩ ኳስ እየተጫወትን ነው የነበርነው ብዬ አስባለሁ።

ብዙ ጊዜ የምትሰራቸው ቡድኖች በወጣቶች የተገነቡ ናቸው። በቀጣይስ ይህ ሀሳብ በሊጉ ይቀጥላል?

እንዳልከው በወጣት የማመኑ ነገር ይቀጥላል ግን በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ በሊጉ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች አብረን የማቀናጀት ነገር አሁን መቶ በመቶ በወጣቶች ብለህ በምትፈልገው ልክ ሪትም ውስጥ እስኪገቡልህ ላታገኛቸው ትችላለህ። እነሱንም በራስ መተማመናቸውን የመሸርሸር ነገር ሊሆን ይችላል ግን አብሮ ጎን ለጎን ሊያግዟቸው እና ልምድ ሊሰጧቸው የሚችሉ በሊጉ በደንብ የለመዱ ተጫዋቾችን አብሮ በማቀናጀት ግን ያው ሀሳቡ ወይ ደሞ ኳስ የመጫወት ነገራችንን ሳንለቅ አሁን ካለንበት ደግሞ የምንገነባውን ቡድን የብቃት ደረጃ ከፍ አድርገን ሊጉ በሚፈልገው ልክ ለማድረግ ነው እያሰብን ያለነው።
\"\"

ከንግድ ባንክ ጋር በአሰልጣኝነት የመቀጠልህ ነገር ዕርግጥ የሆነ ይመስላል። ምንም እንኳን በይፋ ባይገለፅም የቀጣይ ዓመት ስራዎችን ከወዲሁ ጀምራችኋል። ለፕሪምየር ሊጉ በምን አይነት መልኩ እየተዘጋጀህ ነው?

እንዳልከው መቀጠል የሚለው ሥራ ላይ ነው ያለነው ፤ ውሌም አላለቀም። እንደገና ደግሞ በቀጣይ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች እየሠራሁ ነው። ከአለቆች ጋራም አብረን እዛው ሀዋሳ ላይ እያየን ነው። እነሱ መጥተው ነበር። እንግዲህ ቀጣይ ደግሞ ምን እናደርጋለን ወይም ደግሞ በምን መልኩ የሚለውን እና የምጠይቃቸውን ተጫዋቾች ታቅደው ሰዓቱ ሲደርስ ወደ ሥራ የምንገባበትን ነገር እናደርጋለን። ዞሮ ዞሮ ቡድኑን የበለጠ ለማጠናከር እንዳልኩህ ቅርፁን ሳይለቅ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያላቸው እና ጥሩ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች ቡድኑ ውስጥ በማካተት የጥናት ሥራ በመሥራት ላይ ነው ያለነው። ተጫዋቾችንም እያየን ነው ያለነው ማለት ነው። አሁን ሊጉም ወደ አዳማ መጥቷል እዛም እናይና ወደሚቀጥለው ሥራ እንሄዳለን ማለት ነው። በዚህ ሂደት ላይ ነው ያለነው።

እንደ አሰልጣኝ ከአንተ እንደ ቡድን ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፕሪምየር ሊጉ ምን እንጠብቅ?

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ ክለብ ነው። በሚቀጥለው ዓመት ከፈጣሪ ጋር ጠንካራ፣ የተረጋጋ እና ተፎካካሪ የሆነ ቡድን ለመገንባት ነው የማስበው። ለዛም ነው ዝግጅት ላይ ያለነው። እንግዲህ የሚሆነውን አብረን የምናይ ነው የሚሆነው።