በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረገ ተስተካካይ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን 2-0 በማሸነፍ አንደኛውን ዙር ከተከታዩ ደደቢት በ4 ነጥብ በመራቅ አንደኛውን ዙር በመሪነት አጠናቋል፡፡
በኃይሉ አሰፋ በ13ኛው ደቂቃ የጀማል ጣሰውን ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክቶ ባስቆጠረው ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዳሽን ቢራ በሚጫወቱበት ወቅት የበኩር ልጁን መወለድ ብስራት ሰምቶ በቅጽበት በሞት ያጣው በኃይሉ ግቧን ለልጁ መታሰብያነት የሰጠ በሚመስል መልኩ ጣቶቹን ወደ ሰማይ በማድረግ ደስታውን ገልጧል፡፡
ከሁለቱም በኩል ጥቂት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በተስተናገደበት የመጀመርያ አጋማሽ የሜዳው በዝናብ መበላሸትን ተከትሎ ወጥ የሆነ የኳስ ፍሰት ማሳየት ሲቸገሩ ታይቷል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው አሉላ ግርማ ፍሬው ሰለሞን ላይ ሸርታቴ ሲወርድ በጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት በአንዳርጋቸው ይላቅ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ አሉላ ሜዳውን የለቀቀው በቃሬዛ ሳይሆን በተጫዋቾች ድጋፍ መሆኑ በስፍራው የተገኘው ተመልካች ላይ ቅሬታን አስከትሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመርያው ሁሉ ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 2ኛውን ግብ እስካስቆጠረበት ጊዜ ድረስም ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ዝማሬ እና ድባብ የደመቀ ነበር፡፡ በ73ኛው ደቂቃ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው አማካዩ ምንተስኖት አዳነ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነትን ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ከግቡ በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአዳነ ግርማ አማካኝነት በ76ኛው ደቂቃ የሞከሩት ሙከት የግቡ አግዳሚን ሲመልስ በሃይሉ አግኝቶት የሞከረውን ኳስ ጀማል ጣሰው ያወጣበት 3ኛ ግብ ሊሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር፡፡
ድሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 ነጥቦችን ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በመቀመጥ የሊጉን አንደኛ ዙር እንዲያጠናቅቅ ሲረዳው ተሸናፊው መከላከያ 16 ነጥብ ላይ በመርጋት ወደ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት የነበረውን እድል አምክኗል፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛው ዙር በመጪው ቅዳሜ ሲጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ መከላከያ ደግሞ ኤሌክትሪክን ይገጥማል፡፡