ካሜሮን በህዳር 2016 ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ያለፉ ሃገራት በአንድ ሳምንት ውስጥ በተደረገው የመጨረሻ ማጣሪያ ዙር ጨዋታዎች ተለይተዋል፡፡
ግብፅ ከ18 ዓመት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስትመለስ ኬንያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ለውድድሩ አልፋለች፡፡ በአፍሪካ ሴቶች እግርኳስ ትልቅ ስም ያላቸው ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ኤኳቶሪያል ጊኒ እና ደቡብ አፍሪካ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሃገሮች ናቸው፡፡
ግብፅ ከ1998 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለአፍሪካ ዋንጫው አልፋለች፡፡ እንስቶቹ ፈርኦኖች አቢጃን ላይ በኮትዲቯር 2-1 ቢሸነፉም ባሳለፍነው ሳምንት ካይሮ ላይ 1-0 ማነሸፍ ችለዋል፡፡ ኔቬን ጋማል ወሳኝን ግብ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ከመረብ አዋህዳለች፡፡ ግብፅ በ2012 በኢትዮጵያ በ2014 ደግሞ በቱኒዚያ ተሸንፋ ለአፍሪካ ዋንጫው ሳታልፍ ቀርታ ነበር፡፡
ኬንያ በሜዳዋ ከአልጄሪያ ጋር 1-1 በመለያየት በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፋለች፡፡ አልጀርስ ላይ 2-2 የተለያዩት ሃገራቱ በመልሱም ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ነኢማ ቦሂኒ ለአልጄሪያ እንዲሁም ቼሪሽ አቪላ ሳላኖ ለኬንያ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡ ቦሂኒ በደርሶ መልስ ጨዋታው የአልጄሪያን ሶስቱንም ግቦች ማስቆጠር ችሏለች፡፡ ኬንያ የመጀመሪያ ማጣሪያውን ዙር ዲ.ሪ. ኮንጎ በገንዘብ ችግር ምክንያት ከውድድር በመውጧቷ በቀጥታ ያለፈች ሲሆን ሁለት ጨዋታዎችን በማድረግ ብቻ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች፡፡ አልጄሪያ በመጀመሪያው የማጣሪያ ዙር ኢትዮጵያን ጥላ ማለፏ የሚታወስ ነው፡፡
ለሪዮ ኦሎምፒክ በ2015 መጨረሻ ማለፋን ያረጋገጠችው ዚምባቡዌ ዛምቢያን በማሸነፍ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚወስዳትን ትኬት ስትቆርጥ ከሜዳ ውጪም ዛምቢያን 2-3 ማሸነፍ ችላለች፡፡
ጋና ቱኒዚያ 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ስትረታ የአፍሪካ ዋንጫው ከተጀመረ ጀምሮ አንድም ግዜ ከውድድሩ ቀርታ የማታውቀው ናይጄሪያ በሴኔጋል ብትፈተንም 2-0 በማሸነፍ ለተከታታይ 12ኛ ግዜ በአፍሪካ ዋንጫው መካፈሏን አረጋግጣለች፡፡ ደቡብ አፍሪካም ጎረቤት ቦትስዋናን በቀላሉ 3-0 በማሸነፍ ለውድድሩ አልፋለች፡፡ ኤኳቶሪያል ጊኒ ማሊን 2-1 በመርታት የአፍሪካ ዋንጫውን የተቀላቀለች ሌላኛዋ ሃገር ነች፡፡
በ2014 ናሚቢያ ላይ በተካሄደው ውድድር ናይጄሪያ ካሜሮንን በፍፃሜው 2-0 በመርታት ለ9ኛ ግዜ ሻምፒዮን መሆኗ ይታወሳል፡፡ በወድድሩ ላይ ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል የመሃል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በምድብ ሁለት ጋና ከደቡብ አፍሪካ 1-1 የተለያዩበት እንዲሁም በግማሽ ፍፃሜው ካሜሮን ኮትዲቯርን 2-1 የረታችበትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መምራቷ ይታወሳል፡፡
የ2016 አዘጋጅዋ ካሜሮን ውድድሩን በያውንዴ እና ሊምቤ ከተሞች የምታስተናግድ ይሆናል፡፡
ውጤቶች
ዕሁድ
ኢኳቶሪያል ጊኒ 2-1 ማሊ [3-2]
ዛምቢያ 2-3 ዚምባቡዌ [2-4]
ሰኞ
ኮትዲቯር 2-1 ግብፅ [2-2]
ማክሰኞ
ኬንያ 1-1 አልጄሪያ [3-3]
ናይጄሪያ 2-0 ሴኔጋል [3-1]
ጋና 4-0 ቱኒዚያ [6-1]
ደቡብ አፍሪካ 3-0 ቦትስዋና [5-0]
የ2016 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራት ካሜሮን – ናይጄሪያ – ኤኳቶሪያል ጊኒ – ኬንያ – ጋና – ደቡብ አፍሪካ – ግብፅ – ዚምባቡዌ
© ፎቶዎች ከ fcnija, Soka እና Ghanasoccernet