የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር በመጪው ቅዳሜ ይጀመራል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ቡድኖችን በደረጃቸው በመከፋፈል የአንደኛውን ዙር መረጃዎች እና በሁለተኛው ዙር ሊኖራቸው የሚችሉ ለውጦችን በአጭር በአጭሩ እንቃኛለን፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ
ደረጃ – 1ኛ
ተጫወተ – 13 ፣ አሸነፈ – 9 ፣ አቻ – 2 ፣ ተሸነፈ – 2 ፣ ነጥብ – 29
የግብ ሪኮርድ – አገባ – 20 ፣ ገባበት – 6 ፣ ግብ ሳይቆጠርበት የወጣው ጨዋታ መጠን – 9 ፣ ግብ አስቆጥሮ የወጣባቸው ጨዋታዎች ብዛት – 10
የዲሲፕሊን ሪኮርድ – ቢጫ ካርድ – 22 ፣ ቀይ ካርድ – 1
በሽንፈት ውድድር ዘመኑን የከፈተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀስ በቀስ ወደተለመደው የመሪነት መንበሩ ተመልሶ የመጀመርያውን ዙር አጠናቋል፡፡ ፈረሰኞቹ በአመቱ መጀመርያ የአሰልጣኝ ለውጥ ቢያደርጉም በቡድን ስብስባቸው ላይ የጎላ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ውድድር በመግባታቸው ያን ያህል ክፍተት አልታየባቸውም፡፡
ጠንካራ ጎን – የቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫዋቾች ጥራት ከሌሎች የላቀ ሲሆን በሜዳ ላይ እቅስቃሴም 90 ደቂቃ በትኩረት መጫወት ይችላሉ፡፡ በአንደኛው ዙር የተቆጠረበት ግብ 6 ብቻ መሆኑ የተከላካይ መስመሩን ጠንካራነት ይነግረናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴው በተጨማሪ በሌሎች ክለቦች ላይ ያለው የአሸናፊነት ስነልቦና የበላይነት ሊጉን ካለችግር እንዲቆጣጠር አድርጎታል፡፡
ደካማ ጎን – በሜዳ ላይ ቡድኑ የእንቅስቃሴ የወጥነት ችግር ይታይበታል፡፡ ግብ ካልተቆጠረባቸው አልያም ግብ የማስቆጠር ጫና ውስጥ ካልገቡ በቀር የማጥቃትፍላጎታቸው ውስን ነው፡፡ ኳስ የመቆጣጠር እና ቁልፍ ኳሶች ወደተጋጣሚ የግብ ክልል የማድረስ ብቃት ያላቸው የአማካይ ተጫዋቾች እጥረት ያለበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቸኛ የፈጠራ ምንጩ ከመስመር የሚነሱ ኳሶች ላይ መሆኑ በበሃይሉ አሰፋ ላይ ጥገኛ እዲሆን አድርታል፡፡
የአንደኛው ዙር ኮከቦች ፡ ሮበርት ኦዶንካራ እንደሁልጊዜው ሁሉ ምርጥነቱን ማሳየቱን ቀጥሎበታል፡፡ አምና በመጀመርያ የውድድር ዘመኑ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ሰብሮ መግባት ተስኖት የነበረው መሃሪ መና ዘንድሮ ምርጥ አቋሙን አሳይቷል፡፡ አዲስ ፈራሚው አስቻለው ታመነ ቦታውን አስከብሯል፡፡ አዳነ ግርማ ዘንድሮም ግቦችን ማስቆጠሩን ቀጥሎበታል፡፡ ምንተስኖት አዳነ እና በሃይሉ አሰፋ በአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ወደ ቀድሞ ብቃታቸው ተመልሰዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር. . .
ለውጦች – ከወራት በፊት የፈረሙት ሳላዲን ሰኢድ እና ጎድዊን ቺካ በሁለተኛው ዙር ለቅዱስ ጊዮርጊስ መሰለፍ ይጀምራሉ፡፡ ቢያድግልኝ ኤልያስ ወደ አርባምንጭ ከተማ ሲያመራ አትክልት ስብሃት በውሰት ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አቅንቷል፡፡ ዳዋ ሁቴሳ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስሙ ቢያያዝም እስካሁን ከክለቡ ጋር ይገኛል፡፡
የበለጠ ተጠናክሮ ይቀርባል – በአዳነ ግርማ ብቻ ጥገኛ ሆኖ የቆየው የአጥቂ መስመሩ በሳላዲን ሰኢድ እና ጎድዊን ቺካ መምጣት ይጠናከራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዩጋንዳዊው ብሪያን ኡሞኒ ከጉዳቱ አገግሞ መሰለፍ ሲጀምር ደግሞ የአጥቂ ክፍሉ አስፈሪ ይሆናል፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ ፡ በሳላዲን ሰኢድ መምጣት ምክንያት አሰልጣኝ ማርት ኑይ በውድድር ዘመኑ ጥቂት ጨዋታዎች ላይ የተጠቀሙበትን 4-2-3-1 ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሮበርት ግብ ጠባቂነቱን እንደያዘ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ በተከላካይ መስመር አሉላ ፣ አስቻለው ፣ ደጉ እና መሃሪ በአሰልጣኙ እምነት የተጣለባቸው ተጫዋቾች እንደሆኑ ታይቷል፡፡ ምናልባት አይዛክ ኢሴንዴ ከአሉላ እና ደጉ ጋር እየተፈራረቀ በሁለገብነት ሊያገለግል ይችላል፡፡ አማካይ መስመር ላይ ተስፋዬ አለባቸው እና ምንተስኖት/ናትናኤል ሲሰለፉ ከሁለቱ ፊት ራምኬል (ግራ) – አዳነ (መሃል) – በሃይሉ (ቀኝ) እንዲሁም በብቸኛ አጥቂነት ሳላዲን ሰኢድ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡
ደደቢት
ደረጃ – 2ኛ
ተጫወተ – 13 ፣ አሸነፈ – 7 ፣ አቻ – 4 ፣ ተሸነፈ – 2 ፣ ነጥብ – 25
የግብ ሪኮርድ – አገባ – 23 ፣ ገባበት – 15 ፣ ግብ ሳይቆጠርበት የወጣው ጨዋታ መጠን – 3 ፣ ግብ አስቆጥሮ የወጣባቸው ጨዋታዎች ብዛት – 11
የዲሲፕሊን ሪኮርድ – ቢጫ ካርድ – 14 ፣ ቀይ ካርድ – 0
ደደቢት ወጥ ያልሆነ አቋም ቢያሳይም የሊጉን መሪነት እስከመቆጠጥ ደርሶ ነበር፡፡ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ደደቢት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቅርብ ተፎካካሪ ሆኗል፡፡
ጠንካራ ጎን – የሰማያዊዎቹ ጠንካራ ጎን ግብ የማስቆጠር ብቃታቸው ነው፡፡ ቡድኑ በአንደኛው ዙር ከፍተኛውን ግብ ያስቆጠረ ቡድን ሲሆን ግብ ሳያስቆጠር የወጣውም ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ንግድ ባንክ ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዋች ብቻ ነው፡፡ ቡድኑ ኳስ ባይቆጣጠርም ኳስ በእግራቸው ስር ስትገባ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ አደጋ መፍጠር ይችሉበታል፡፡ ሳኑሚ እና ዳዊት ፍቃዱ ጥሩ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ባይሆንም ግብ ማስቆጠራቸውን ቀጥለውበታል፡፡
ደካማ ጎን – ምናልባትም የሊጉን ደካማ የተከላካይ መስመር የያዘው ደደቢት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በ13 ጨዋታ 14 ግቦች ያስተናገደው የደደቢት የተከላካይ መስመር በጉዳት ፣ እድሜ እና አቋም መውረድ ምክንያት ሳስቷል፡፡ አማካይ መስመሩ ሌላው የደደቢት ደካማ ጎን ነው፡፡ ያሬድ ዝናቡ እና ሳምሶን በግላቸው የሚያሳዩት አቋም ድንቅ ቢሆንም እንደ ቡድን የደደቢት የአማካይ ክፍል ክፍት ነው፡፡
የአንደኛው ዙር ኮከቦች : ሽመክት ጉግሳ በደደቢት የአንደኛው ዙር ውጤት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያሳረፈ ተጫዋች ነው፡፡ የደደቢት ግቦች መነሻ ሲሆን ለመልሶ ማጥቃት የተመቸ ፍጥነት እና ጥሩ የማሻገር ብቃት ያለው ተጫዋች ነው፡፡ ያሬድ ዝናቡ ከጉዳት ጋር እየታገለ መልካም የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ ሳምሶን ጥላሁን ሌላው የሚጠቀስ ተጫዋች ነው፡፡
በሁለተኛው ዙር. . .
ለውጦች – ሁለት ጋናዊያንን አስፈርመው የሁለተኛውን ዙር መጀመር እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ምንም ተጫዋች ከክለቡ ያለቀቀ ሲሆን ዳዊት ፍቃዱ እና ያሬድ ዝናቡ የመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች በጉዳት ያመልጧቸዋል፡፡ ጆሴፍ አግዮኪ ደግሞ ከረጅም ጊዜጉዳት ተመልሷል፡፡
ክፍተቶችን ሊደፍን ይችላል – አዲስ ፈራሚው ጆን ቱፈር የተከላካይ መስመሩ ላይ ለውጥ ሊፈጥር እንደሚችል ቡድኑ ከመከላከያ ጋር ባደረገው የሊግ ዋንቻ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ አሳይቷል፡፡ በአማካይ መስመር የጋብሬል አህመድን መውጣት ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ሌላው አዲስ ፈራሚ ክዌሲ ኬይል ሊሸፍን ይችላል፡፡ በ1ኛው ዙር በጉዳት ተቸግሮ ከመሪው ብዙም ያልራቀው ደደቢት በተሟላ ስብስብ የተሻለ እንደሚጓዝ ይጠበቃል፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ ፡ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በደደቢት በሁሉም ጨዋታ የተጠቀሙበትን 4-4-2 አሰላለፍ ይዘው እንደሚቀጥሉ የሚጠበቅ በመሆኑ ከጥቂት ተጫዋቾች ለውጥ ውጪ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አይኖርም፡፡
ታሪክ ጌትነት
ስዩም ተስፋዬ – ጆን ቱፎር – አይናለም ኃይለ – ተካልኝ ደጀኔ
ሽመክት ጉግሳ – ያሬድ ዝናቡ/ክዌሲ ኬይል – ሳምሶን ጥላሁን – ብርሃኑ ቦጋለ
ዳዊት ፍቃዱ – ሳሚ ሳኑሚ
አዳማ ከተማ
ደረጃ – 3ኛ
ተጫወተ – 13 ፣ አሸነፈ – 7 ፣ አቻ – 2 ፣ ተሸነፈ – 4 ፣ ነጥብ – 23
የግብ ሪኮርድ – አገባ – 18 ፣ ገባበት – 14 ፣ ግብ ሳይቆጠርበት የወጣው ጨዋታ መጠን – 4 ፣ ግብ አስቆጥሮ የወጣባቸው ጨዋታዎች ብዛት – 10
የዲሲፕሊን ሪኮርድ – ቢጫ ካርድ – 18 ፣ ቀይ ካርድ – 1
ድንቅ የውድድር ዘመን ጅማሮ ቢያደርግም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ተደራራቢ ሽንፈት አስተናግዶ ተንሸራቷል፡፡
ጠንካራ ጎን – የአዳማ ከተማ ጠንካራ ጎን የሜዳውን ጨዋታ አድቫንቴጅ መጠቀሙ ነው፡፡ ዘንድሮ በሜዳው አንድ ጨዋታ ብቻ የተሸነፈ ሲሆን በጨዋታ እንቅስቃሴ ተበልጦ እንኳን አሸንፎ የመውጣት ልምድን አዳብሯል፡፡ ቡድኑ በ3ኛው ሩብ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በርካታ ግቦችን ማስቆጠሩ በአካል ብቃቱ ላይ የተሻለ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ደካማ ጎን – የወጥነት ችግር ይታይበታል፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በጨዋታ መሃል የመዋዠቅ ችግር አለበት፡፡ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አቀያይሮ የመጠቀም ዝንባሌ ዘንድሮ በተለይም በግብ ጠባቂ እና አጥቂ መስመር ላይ ታይቷል፡፡ ይህም በቡድን ውህደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሮባቸዋል፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ በአጥቂ መስመር ላይ ብዛት ያላቸው ተጫዋቾች በመያዛቸው ምክንያት በሚመስል መልኩ 3 ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው አጥቂዎችን በተደጋጋሚ ማሰለፋቸው የቡድኑ ሚዛናዊነት ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡
የአንደኛ ዙር ኮከቦች – ሞገስ ታደሰ ጥሩ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ በጨዋታ ዘመኑ ማምሻ ላይ የሚገኘው ሱሌማን መሀመድ በንጽጽር ወጥ አቋም በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ አማካዩ ወንድወሰን ሚልኪያስ እና አንጋፋው ታፈሰ ተስፋዬ ሌሎች የሚጠቀሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
በሁለተኛው ዙር. . .
ለውጦች – ዘንድሮ ቡድኑ የተቀላቀለው ተመስገን ገብረጻድቅ ወደ ሃድያ ሆሳዕና ሲያመራ እስካሁን አዲስ ተጫዋች አላስፈረመም፡፡ አንድ ተጫዋች በሙከራ ላይ ሲሆን በ2 ቀናት ውስጥ መፈረም አለመፈረሙ ይታወቃል ተብሏል፡፡ ጉዳት ላይ የነበሩት ወንድወሰን ፣ ታፈሰ ፣ ሚካኤል ጆርጅ ፣ እና ሻኪሩ ወደ ልምምድ ተመልሰዋል፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ – አሰልጣኝ አሸናፊ አዳዲስ ተጫዋቾችን ባለማካተታቸው የአሰላለፍም ሆነ የሲስተም ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ይቀጥላል…