የሪዮ ኦሎምፒክ የእግርኳስ ውድድር የምድብ ድልድል ወጥቷል

በመጪው ክረምት የብራዚሏ ሪዮ ዲጄኔሮ ለምታስተናግደው ኦሎምፒክ ዛሬ የእግርኳስ ውድድር የምድብ ድልድል በማራካኛ ስታዲየም ወጥቷል፡፡

በወንዶች የአፍሪካ ተወካዮቹ ደቡብ አፍሪካ ከአዘጋጅዋ ብራዚል፣ ከኢራቅ እና ዴንማርክ ጋር ስተደለደል፤ ናይጄሪያ ከስዊድን፣ ኮሎምቢያ እና ጃፓን እንዲሁም አልጄሪያ ከሆንዱራስ፣ አርጀንቲና እና ፖርቹጋል ጋር ተደልድለዋል፡፡ የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮኗ ናይጄሪያ በምድብ ሁለት ትገኛለች፡፡

ባሳለፍነው ታህሳስ ወር አልጄሪያን በፍፃሜው ጨዋታ ያሸነፈችው የ1996 አትላንታ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ናይጄሪያ በ2008 ቤጂንግ ኦሎምፒክ በአርጀንቲና ተሸንፋ የብር ሜዳሊያ ስታገኝ በለንደን ባዘጋጀቸው የ2012ቱ ኦሎምፒክ ተሳታፊ አልነበረችም፡፡

በ2015 የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ለደረጃ በተደረገ ጨዋታ አዘጋጅዋን ሴኔጋልን አሸንፋ ለኦሎምፒክ የቀረበቸው ደቡብ አፍሪካ በምድብ አንድ ከኦሎምፒክ አዘጋጅዋ ብራዚል ጋር በመክፈቻ ጨዋታ የምትገናኝ ይሆናል፡፡

ከ36 አምታት በኃላ ወደ ኦሎምፒክ እግርኳስ የተመለሰችው አልጄሪያ በምድብ አራት ከባድ ፈተና ይገጥማታል፡፡ አልጄሪያ ለመጨረሻ ጊዜ በኦሎምፒክ የተሳተፈችው በ1980 ሞስኮ ኦሎምፒክ ነበር፡፡ ለመጨረሻ ግዜ የአፍሪካ አህጉርን ወክሎ የውርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለችው ካሜሮን መሆኗ ይታወሳል፡፡

የ2012 ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ብራዚልን ያሸነፈቸው ሜክሲኮ መሆኗ ይታወሳል፡፡ ሶስተኛ በመሆን የነሃስ ሜዳሊያን ያሸነፈችው ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ነበረች፡፡

በሴቶች እግርኳስ አፍሪካን የሚወክሉት ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ የምድብ ድልድላቸውን ዛሬ በማራካኛ ስታዲየም በተደረገው የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት አውቀዋል፡፡ እንደወንዶቹ ሁሉ በሴቶቹም ደቡብ አፍሪካ ከአዘጋጅዋ ብራዚል፣ ስዊድን እና ቻይና ጋር እንዲሁም ለመጀመሪያ ግዜ ለኦሎምፒክ እግርኳስ ውድድር የቀረበችው ዚምባቡዌ በምድብ ሁለት ከካናዳ፣ አውስትራሊያ እና ጀርመን ጋር ተደልድላለች፡፡

የ2012 ለንደን ኦሎምፒክን ያሸነፈቸው ዩናይትድ ስቴትስ ስትሆን ጃፓን እና ካናዳ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን መጨረሻቸው ይታወሳል፡፡

ሙሉ የምድብ ድልድል

በወንዶች

ምድብ 1 ብራዚል ደቡብ አፍሪካ ኢራቅ ዴንማርክ

ምድብ 2 ስዊድን ኮሎምቢያ ናይጄሪያ ጃፓን

ምድብ 3 ፊጂ ደቡብ ኮሪያ ሜክሲኮ ጀርመን

ምድብ 4 ሆንዱራስ አልጄሪያ ፖርቹጋል አርጀንቲና

በሴቶች

ምድብ 1 ብራዚል ቻይና ስዊድን ደቡብ አፍሪካ

ምድብ 2 ካናዳ አውስትራሊያ ዚምባቡዌ ጀርመን

ምድብ 3 ዩናይትድ ስቴትስ ኒው ዚላንድ ፈረንሳይ ኮሎምቢያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *