የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ዳሰሳ – ክፍል 2

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገ ይጀምራል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም የሊጉን ክለቦች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲሁም በ2ኛው ዙር የሚኖራቸዉን ለውጥ በክፍል አንድ ለማሳየት ሞክራለች፡፡ በክፍል 2 ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ ከ4-7ኛ ላይ የሚገኙ ክለቦችን እንዳስሳለን

ወላይታ ድቻ

ደረጃ 4ኛ
ተጫወተ – 13 ፣ አሸነፈ – 6 ፣ አቻ – 2 ፣ ተሸነፈ – 5 ፣ አስቆጠረ – 13 ተቆጠረበት 16
የዲሲፕሊን ሪኮርድ ፡ ቢጫ ካርድ – 15 ፣ ቀይ ካርድ – 3

ጠንካራ ጎን – የድቻ የመከላከል አጨዋወት እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ መልካም ነው፡፡ የመሳይ ተፈሪ ቡድን በተለይ ከሜዳው ውጪ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በጥልቀት ይከላከላል፡፡ ተከላካዮቹ በማጥቃት አንቅስቃሴ የማይሳተፉ በመሆኑ ለመልሶ ማጥቃት የተጋለጡ አይደሉም፡፡ ከተቆጠረባቸው 16 ግቦች መካከል ግማሹን ያስተናገዱት ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጋር በመሆኑ የተቆጠረባቸው የግብ መጠን የተከላካይ ክፍሉን ጥንካሬ አይገልጽም፡፡ ሌላው የድቻ ጠንካራ ጎን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ናቸው፡፡ በርካታ ተጫዋቾችን ለቆ የውድድር አመቱን የጀመረው ወላይታ ድቻ እንደተፈራው ቁልቁል ሳይወርድ በጥሩ ደረጃ ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው በአሰልጣኙ ብርታት ነው፡፡

ደካማ ጎን – የቡድኑ ዋንኛ ችግር በየጨዋታው ይዞት የሚገባው ሲስተም ተመሳሳይ መሆን ነው፡፡ የአሰልጣኙ የመጀመርያ ምርጫ መከላከል በመሆኑ ቡሉም ጨዋታ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይከተላል፡፡ በዚህም ምክንያት በየጨዋታው በአማካይ 1 ግብ ብቻ አስቆጥረዋል፡፡ ሌላው የቡድኑ ችግር በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ቢቀረፍም የወጥነት ችግር አለበት፡፡ በተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፎ ጥሩ ግስጋሴ ማድረግ ይጀምርና ተመልሶ በተከታታይ ይሸነፋል፡፡

የቡድኑ ኮከቦች – አዳዲስ ፈራሚዎቹ አማኑኤል ተሾመ ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ ቶማስ ስምረቱ እና ወንድወሰን አሸናፊ በመጀመርያ የውድድር ዘመናቸው ድንቅ አቋም እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ከቡድኑ ነባር ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አላዛር ፋሲካም ቡድን የመምረት ሃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ይገኛል፡፡

በሁለተኛው ዙር

ለውጦች – ከቡድኑ የለቀቀ ተጫዋች የሌለ ሲሆን በክረምት ቡድኑን ለቆ ለሀዋሳ የፈረመው መክብብ ደገፉ ወደ ቡድኑ ተመልሷል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ – በድቻ ለውጦች የሌሉ በመሆናቸው በመጀመርያው ዙር በአመዛኙ የተጠቀሙነትን ቋሚ አሰላለፍ ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
image

ሲዳማ ቡና

ደረጃ – 5ኛ
ተጫወተ – 13 ፣ አሸነፈ – 4 ፣ አቻ – 7 ፣ ተሸነፈ – 2 ፣ አገባ -15 ገባበት – 17
የዲሲፕሊን ሪኮርድ – ቢጫ ካርድ – 22 ፣ ቀይ ካርድ- 1

ከወጣ ገባ የውድድር ዘመን ጅማሬ በኋላ በሂደት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ሆኖ አንደኛውን ዙር አጠናቋል፡፡ ባለፈው ካውድድር ዘመን 2ኛ ዙር የጀመረው የቁልቁለት መንገድ አብቅቶም ተሸሽሎ ቀርቧል፡፡

ጠንካራ ጎን – የሲዳማ ቡና ጥንካሬ የተደራጀ እቅስቃሴው ነው፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው 5 አማካዮችን የሚጠቀሙ ሲሆን የተከላካይ መስመሩም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ወደ ጠንካራነት ተመልሷል፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም የሲዳማ ሌላው ጠንካራ ጎን ናቸው፡፡ በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ተቸግሮ የነበረው ሲዳማ አሰልጣኙ ከተመለሱ በኋላ መሻሻል ችሏል፡፡

ደካማ ጎን – የአጥቂ መስመሩ ስል አይደለም፡፡ ኤሪክ ሙራንዳ ፣ አንዱአለም ንጉሴ እና በረከት አዲሱ የጫማ መስቀያ ጊዜያቸው በመቃረቡ ቀድሞ የነበራቸው ፍጥነት ፣ ጥንካሬ እና ግብ ፊት ያላቸው አስፈሪነት ከድቷቸል፡፡ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴም ከወራቤ ከተማ መጥቶ ሳይጠበቅ መጉላት የቻለው የቻለው አዲስ ግደይ ጥገኛ ነው፡፡

የቡድኑ ኮከቦች – የአዲስ ግደይ ድንቅ አቋም ለሲዳማ ቡና ውጤታማነት ቁልፉ ሰው ነው፡፡ ወሰኑ ማዜ ፣ አዲስ ፈራሚዎቹ ሙሉአለም መስፍን እና አንተነህ ተስፋዬም ጥሩ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡

በሁለተኛው ዙር
ለውጦች ፡ አዲ የገባ ተጫዋች የለም፡፡ እንዳለ ከበደ ወደ አርባምንጭ ከተማ ሲመለስ ከክለቡ ይሰናበታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው በረከት አዲሱ አሁንም በክለቡ እንዳለ ተነግሯል፡፡ አዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን ባለመቀላቀላቸው የአሰላለፍ ለውጦች ይኖራሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
image

ድሬዳዋ ከተማ

ደረጃ – 6ኛ

ተጫወተ -13 ፣ አሸነፈ – 5 ፣ አቻ – 3 ፣ ተሸነፈ – 5 ፣ አገባ – 11 ፣ ገባበት – 12
የዲሲሊን ሪኮርድ – ቢጫ ካርድ – 21 ፣ ቀይ ካርድ – 1

ከ3 የውድድር ዘመን በኋላ ወደ ፕሪሚር ሊግ የተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ መልካም የሚባል የውድድር አመት በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠንካራ ጎን ፡ የአማካይ መስመሩ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ ኳስን የሚቆጣጠር ቡድን ሲሆን አማካዮቹ ለግብ አመቻችተው የሚሰጧቸውን ኳሶች አጥቂዎቹ በተገቢው መንገድ ቢጠቀሙባቸው ኖሮ ድሬዳዋ ደረጃው ከዚህም ከፍ ይል ነበር፡፡

ደካማ ጎን – የአጥቂ መስመሩ እጅግ የሳሳ ነበር፡፡ አሰልጣኝ መሰረት በአጥቂዎች እጥረት ምክንያት የቀኝ ተከላካዩ ፍቃዱ ታሰን አጥቂ አድርጋ እስከ ማጫወት ደርሳ ነበር፡፡ ፍቃዱ ወርቁ እና በብሄራዊ ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው በላይ አባይነህ እንደተጠበቁት የአጥቂ መስመሩ ላይ ልዩነት መፍጠር አልቻሉም፡፡

የቡድኑ ኮከቦች – ይሁን እንዳሻው የቡድኑ የልብ ምት ነው፡፡ የማጥቃት እና የመከላከል ሚዛኑን ጠብቆ ለቡድኑ ድንቅ እንቅስቃሴ ማበርከት ችሏል፡፡ ተስፋዬ ዲባባ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሄኖክ አዱኛ ሌሎች ጥሩ እቅስቃሴ ያደረጉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በሁለተኛው ዙር

ለውጦች ፡ ፉአድ ኢብራሂም እና ዮርዳኖስ አባይ ቡድኑን ሲቀላቀሉ ፍቃዱ አለሙ ደግሞ ክለቡን ለቆ ለአአ ከተማ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ ፡ ሁለት አጥቂዎች ቡድኑን በመቀላቀላቸው የድሬዳዋ የፊት መስመር ላይ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ በምትመርጠው የ4-3-3 አሰላለፍ ፉአድ የመስመር አጥቂነቱን ፣ ዮርዳኖስ ደግሞ የመሀል አጥቂነቱን ቦታ ይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

image

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ደረጃ – 7ኛ

ተጫወተ – 13 ፣ አሸነፈ – 3 ፣ አቻ – 8 ፣ ተሸነፈ – 2 ፣ አገባ -10 ፣ ገባበት – 9
የዲሲፕሊን ሪኮርድ – ቢጫ ካርድ – 23 ፣ ቀይ ካርድ – 1

በአቻ ውጤቶች የተሞላው የንግድ ባንክ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ጉዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ እንዲመቀመጥ አሰገድዶታል፡፡

ጠንካራ ጎን ፡ የተከላካይ መስመሩ ከሌሎቹ ክፍሎች በንፅፅር ጠንካራው ነው፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል በሊጉ ጥቂት ግብ ያስተናገደው ንግድ ባንክ እንደ አጥቂ መስመሩ ደካማነት ባይሆን ኖሮ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ያለ ቦታ ላይ መቀመጥ ይችሉ ነበር፡፡

ደካማ ጎን ፡ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ደካማ ነው፡፡ ከተከላካይ አማካይ እስከ አጥቂው ክፍል ድረስ በሊጉ ደረጃ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ቢይዝም እንደቡድን ይህ ነው የሚባል የማጥቃት አጨዋወት የለውም፡፡ ሌላው የቡድኑ ችግር በየአመቱ አዲስ ቡድን መሆኑ ነው፡፡ ዘንድሮ ከ10 በላይ አዳዲስ ተጫዋች ያስፈረመው ባንክ አሁንም በሽግግር ውስጥ ለማለፍ ተገዷል፡፡

የቡድኑ ኮከቦች ፡ ኤፍሬም አሻሞ መልካም ውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴም በእሱ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ዘግይቶ ወደ ቡድኑ ቋሚ አሰላለፍ የገባው ቢንያም በላይ እና አቤል አበበ ሌሎች የሚጠቀሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በሁለተኛው ዙር
ለውጦች
፡ አዲስ የፈረመም ሆነ ቡድኑን የለቀቀ ተጫዋች የለም፡፡
image

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *