ሶከር ሜዲካል | የሴት እግርኳስ ተጫዋቾች ጤና – ክፍል 1

ከእግርኳስ ጋር የተያያዙ ጉዳቶችን እና የህክምና መረጃዎችን በምናጋራበት በዚህ አምድ ለሚቀጥሉት ሳምንታት ከሴቶች እግርኳስ ጋር በተያያዘ ያሉትን የተለያዩ የህመም ዓይነቶች እና በዛ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ የመፍትሄ ሀሳቦችን ያካተቱ ፅሁፎች በዶክተር ብሩክ ገነነ አማካይነት ይቀርባሉ።

የሴቶች እግርኳስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና የተመልካቾቹም ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ በቅርብ የተደረገው የሴቶች ዓለም ዋንጫም ለዚህ ትክክለኛ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዞ የሴቶች እግርኳስ ላይ የህክምና ባለሙያዎች ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ እና ሴቶች በተፈጥሮ ከወንዶች የሚለያቸው ነገር በመኖሩ ህክምናውም ከዛ አንጻር መተግበር እንዳለበት ጥናቶች አስመልክተዋል፡፡ የእግርኳስ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነው ፊፋ ከዚህ ጋርም ተያይዞ በቅርቡ ጥናታዊ ጽሁፎችን ይፋ አድርጓል፡፡

ሴቶች የሚሰጣቸው የስፖርት ህክምና በወንዶች ላይ በተሰሩ ጥናቶች የተመሰረተ እና የሴቶችን የተለየ ተፈጥሯዊ ኡደት ያላገናዘበ ነው፡፡ ለምሳሌ ሴቶች በወር አበባ ወቅት በየወሩ በሰውነታቸው ላይ የሚከሰተው የሆርሞን ለውጥ እና የዛ ውጤቶች ግምት ውስጥ ሲገቡ አይስተዋልም፡፡ ከወር አበባ ጋርም ተያይዞ በሴት ተጫዋቾች ላይ ተመርኩዘው የተደረጉ ጥናቶች አናሳ የሚባሉ ናቸው፡፡

የወር አበባ በሴት ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር እና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ላይም ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ በአፍሪካ የእግርኳስ ተጫዋቾች ላይ በተደረገ ጥናት አማካይነት የተለያዩ የህመም ስሜቶች በወር አበባ ወቅት እንደሚያጋጥሟቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህም ምልክቶች የራስ ምታት ፣ የስሜት መለዋወጥ ፣ ቁርጠት ፣ የጡት ህመም ፣ ማስመለስ እና ማቅለሽለሽ ፣ የጀርባ ህመም ፣ ቁጡነት ፣ የሀዘን ስሜት እና እንቅልፍ ማብዛት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ተጫዋቾች የወሊድ መቆጣጠሪያን በመጠቀም እነዚህ ስሜቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ በወሊድ መቆጣጠሪያ አማካይነት በውድድር ወቅት የወር አበባ እንዳይከሰት ወይም እንዲዘገይ ያደርጋሉ፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ምልክቶች መካከል የጡት ፤ የጀርባ እና የሆድ ህመም የተጫዋቾቹን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በላቀ ሁኔታ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጡት ህመም በሚኖርበት ጊዜ እንደልብ መሮጥም ሆነ መጋጨት የሚያስቸግርበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ከዛ በተጨማሪም የጀርባ እና የሆድ ህመም ከፍተኛ በሆነ መልኩ የልምምድ ወቅትን ከባድ ያደርጋል፡፡

ከሥነ ልቦና ተጽዕኖዎች መካካል እንደ ቁጡነት እና የስሜት መለዋወጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ስሜቶች ለጉዳት ተጋላጭ የሚያደርጉ በመሆናቸው የህክምና ባለሙያዎች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ተጫዋቾቹን በምን ዓይነት መልኩ እንደሚመክሩ እና እንደሚያግዙ መመካከር አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንግግር ህክምና እና ምክር ከመድሃኒት የበለጠ ውጤታማ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ጥናቱ ከተደረገባቸው ተጫዋቾች መካከል 10 ፐርሰንት የሚሆኑት የወር አበባቸው በሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው እንደዚሁም በአጠቃላይ ህይወታቸው ላይ ተጽዕኖን ያሳድራል በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህንን ቁጥር በተመለከተ በሀገራችንም ምን ያህል ጫና እየደረሰ ነው የሚለው ጉዳይ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት የህመም ስሜቶች የእግር ኳስ ህይወታቸው ጫና ውስጥ እንዳይገባ የህክምና ባለሙያዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡

በሌላ ጥናት ማየት እንደተቻለው ከጨዋታዎች በፊት ተጫዋቾች ያነሰ የምግብ ፍላጎት እንደዚሁም በቂ ዕረፍትን ለማድረግ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ተጫዋቾች ምግቦችን በግድ እስከመመገብ የደረሱበት ሁኔታ ሲኖር ከዛ በተቃራኒ ደግሞ ጥሩ የማይባሉ ምግቦችን ለመመገብ የመፈለግ ስሜት ተስተውሎባቸዋል፡፡ ከተለያዩ የህመም ስሜቶች ጋር በተየያዘም እንቅልፍን ለማግኘት ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ ይህም ለጨዋታ የሚኖራቸው ዝግጅት ላይ የራሱ ተጽዕኖን አሳድሯል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የህመም ስሜቶች የእግርኳስ ህይወታቸው ጫና ውስጥ እንዳይገባ የህክምና ባለሙያዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የህክምና ባለሙያ የሆኑት እና ከሴት ተጫዋቾች ጋር በቅርበት የሚሰሩት ዶ/ር ቃልኪዳን ዘገየ ስለዚህ ጉዳይ ሃሳባቸውን ገልጸውልናል፡፡ እንደ ዶ/ር ቃልኪዳን አስተያየት ችግር ከሚፈጥሩ ነገሮች መካከል አንዱ በተጫዋቾች መሃል ስለየወር አበባ በቂ የሆነ ግንዛቤ አለመኖሩ ነው፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾች የወር አበባ ማየትን እንደ ነውር የሚታይበት ማህበረሰብ ውስጥ በማደጋቸው ምክንያት ተያያዥ ችግሮች በሚያጋጥሟቸው ወቅት በግልጽ መናገር እና እርዳታን ማግኘት ይቸገራሉ፡፡

ከቡድኖች በኩልም የንጽህና መጠበቂያዎች እንደትጥቅ ሁሉ ለተጫዋቾች መታደል እንዳለበት ዶ/ር ቃልኪዳን ይናገራሉ፡፡ ተጫዋቾች ምቾት ተሰምቷቸው ጨዋታቸውን ማድረግ እንዲችሉ እንዚህን ነገሮች ማሟላት ግድ ይላል፡፡ በወር አበባ ወቅት በሚኖር ህመም ምክንያት ልምምድ እና ወሳኝ የሚባሉ ጨዋታዎች እንደሚያመልጧቸው ዶ/ር ቃልኪዳን ያስረዳሉ፡፡ ተጫዋቾቹን ለመርዳት ቀርቦ ማናገር እና ግንዛቤን መፍጠር ወሳኙ ነገር እንደሆነ ዶ/ር ቃልኪዳን ይገልጻሉ፡፡ በወር አበባ ወቅት የሚኖረው ህመም የሚቆይበት ጊዜ ፣ መቼ ተፈጥሯዊ እና መቼ ከህመም ጋር የተያያዘ ነው እንደሚባል እንደሚወያዩበት አስረድተዋል፡፡

“ከተጫዋቾቹ ጋር በቅርበት ስለምንሰራ መቼ የወር አበባ እንደሚመጣ እና አስቀድመው ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው እናወራለን፡፡ መድሃኒት ማዘዝ ፣ ሙቅ ውሃ መስጠት ፣ ማሳጅ እና በቂ ዕረፍት እንዲያገኙ ማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከአሰልጣኞቹም በመነጋገር የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸው እና በቂ ፈሳሽ እንደዚሁም የሚመች አለባበስ እንዲያደርጉ እናደርጋለን፡፡ የተለየ በሽታ ካጋጠመ ደግሞ ወደ ማህጸን ስፔሻሊስት ሄደው እንዲታከሙ እናደርጋለን” በማለት አብራርተዋል፡፡ ጤና ከምንም ነገር በላይ ለተጫዋቾችም ሆነ ለቡድኖች ስኬታማነት ወሳኝ ስለሆነ የሚመለከተው አካል በሙሉ ተባብሮ በመስራት የራሱን አስተዋጽኦ መወጣት ይኖርበታል።