” ወደ  ጨዋታ ለመመለስ ጥሩ ዝግጅት አድርጌያለሁ ” ሳላዲን ሰኢድ 

ባለፉት 10 አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ድንቅ አጥቂዎች ግንባር ቀደሙ የሆነው ሳላዲን ሰኢድ በ2002 ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ በግብፅ ፣ ቤልጅየም እና አልጄርያ ክለቦች አሳልፎ ከወር በፊት ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል፡፡

ያለፉትን ወራት ከፈረሰኞቹ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው ሳላዲን አሁን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመሰለፍ ብቁ ሆኗል፡፡ ነገ 10 ቁጥር ማልያ በመልበስም አዳማ ከተማን ይገጥማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሳላ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አጠር ያለ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

ከ2002 በኋላ በሊጉ ጨዋታ አድርገህ አታውቅም፡፡ ከ5 የውድድር ዘመናት በኋላ ወደ ሊጉ በመመለስህ የሚፈጥርልህ የተለየ ስሜት አለ ?

አዎ፡፡ በሀገር ላይ ከቤተሰብህ ጋር ስትኖር የሚሰማህ ስሜትና ከሀገር ወጥተህ ስትጫወት ስሜቱ ይለያያል አሁን ሀገሬ ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ የምጫወት ስለሆነ ደስ ብሎኛል፡፡
(ሳላዲን ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነው)

በቅዱስ ጊዮርጊስ እየተላመድክ ነው?

ከሞላ ጎደል የቡድኑን አባላት ከዚህ በፊት አውቃቸዋለሁ፡፡ በብሄራዊ ቡድንም አብሬያቸው የተጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ከሜዳም ላይ ሆነ ከሜዳ ውጪ ለመግባባት ለመዋሀድ ምንም አላስቸግረኝም፡፡ ስለዚህ ጥሩ ውህደትና ህብረት አለን ብዬ አስባለው፡፡

በአካልም በአዕምሮም ዝግጁ እንዳልነበርክ በመግለፅ ከብሄራዊ ቡድን (ለአልጄሪያው ጨዋታ) ራስህን አግለህ ነበር፡፡ በእርግጥም ከጨዋታ ርቀሀል፡፡ ይህ መሆኑ ሊጉ ይፈትነኛል ብለህ ታስባለህ?

በቂ ዝግጅት አድርጌያለው፡፡  በቀን ሁለቴም ልምምድ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይም እራሴን ተመልክቻለው፡፡ ለጨዋታውም ጥሩ ዝግጅት አድርጌያለው

በሊጉ ያለህና የነበረህን ስምና ዝና ለማስጠበቅ ምን ያህል ተዘጋጅተሃል?

ሁሌም ቢሆን በክለብ ውስጥ ስትሆን ለቡድንህ የተቻለህን ለማድረግ ነው የምትሰራው፡፡ እኔ አሁን ይህን ሳይሆን የማስበው ሁሌም ለጨዋታው ብቁ ሆኜ ክለቤ ከኔ የሚፈለግብኝን ግልጋሎት መስጠት ፣ ማድረግ የምችለውን ለማድረግና ከጊዮርጊስ ጋር ከውጭም ከውስጥም ላሉበት ጨዋታ የሚጠበቅብኝ ለማድረግ ነው፡፡

ያንተን ወደ ሜዳ መመለስ በጉጉት ለሚጠብቁት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የምታስተላልፈው መልክት አለህ?

ደጋፊው ሁሌም ከቡድኑ ጎን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቡድኑን ይረዳል እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ እነሱን ለማስደሰት እንጥራለን፡፡  በሀገር ውስጥም በውጭ ስኬታማ ለመሆን እንሰራለን፡፡ ያው ዘንድሮ የሀገር ውስጥ ውድውር እንዳለቀ የሴካፋ የክለቦች ውድድር አለ፡፡ ይሄንንም (ሴካፋ) የፕሪሚየር ሊጉንም ዋንጫ ማንሳት እንፈልጋለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *